ሐዋርያት ሥራ 7:51-60
ሐዋርያት ሥራ 7:51-60 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
“እናንተ አንገታችሁ የደነደነ፥ ልባችሁም የተደፈነ፥ ጆሮአችሁም የደነቈረ፥ እንደ አባቶቻችሁ መንፈስ ቅዱስን ዘወትር ትቃወማላችሁ። አባቶቻችሁ ከነቢያት ያላሳደዱት ማን አለ? ዛሬም እናንተ አሳልፋችሁ የሰጣችሁትንና የገደላችሁትን የጻድቁን መምጣት አስቀድመው የተናገሩትን ገደሉአቸው። በመላእክትም ሥርዐት ኦሪትን ተቀብላችሁ አልጠበቃችሁትም።” ይህንም ሰምተው ተበሳጩ፤ ልባቸውም ተናደደ፤ ጥርሳቸውንም አፋጩበት። በእስጢፋኖስም ላይ መንፈስ ቅዱስ መላ፤ ወደ ሰማይም ተመለከተ፤ የእግዚአብሔርን ክብር፥ ኢየሱስም በእግዚአብሔር ቀኝ ቆሞ አየ። “እነሆ ሰማይ ተከፍቶ፤ የሰው ልጅም በእግዚአብሔር ቀኝ ቆሞ አያለሁ” አለ። እነርሱም በታላቅ ቃል ጮኹ፤ ጆሮአቸውንም ደፈኑ፤ በአንድነትም ተነሥተው ከበቡት። ከከተማም ወደ ውጭ ጐትተው አውጥተው ወገሩት፤ የሚወግሩት ሰዎችም ልብሳቸውን ሳውል በሚባል ጐልማሳ እግር አጠገብ አስቀመጡ። እስጢፋኖስም፥ “ጌታዬ ኢየሱስ ሆይ፥ ነፍሴን ተቀበል” እያለ ሲጸልይ ይወግሩት ነበር። በጕልበቱም ተንበርክኮ፥ “አቤቱ፥ ይህን ኀጢአት አትቍጠርባቸው” ብሎ በታላቅ ድምፅ ጮኸ። ይህንም ብሎ ሞተ፤ ሳውልም በእስጢፋኖስ ሞት ተባባሪ ነበር።
ሐዋርያት ሥራ 7:51-60 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
“እናንት ልባችሁና ጆሯችሁ ያልተገረዘ፣ ዐንገተ ደንዳኖች ልክ እንደ አባቶቻችሁ መንፈስ ቅዱስን ሁልጊዜ ትቃወማላችሁ። ከነቢያት መካከል አባቶቻችሁ ያላሳደዱት ማን አለ? የጻድቁን መምጣት አስቀድመው የተናገሩትን እንኳ ገድለዋል፤ እናንተም አሁን አሳልፋችሁ ሰጣችሁት፤ ገደላችሁትም፤ በመላእክት አማካይነት የተሰጣችሁንም ሕግ ተቀበላችሁ እንጂ አልጠበቃችሁትም።” በሸንጎው ስብሰባ ላይ የነበሩትም ይህን በሰሙ ጊዜ እጅግ ተቈጡ፤ ጥርሳቸውንም አፏጩበት። እስጢፋኖስ ግን በመንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ ወደ ሰማይ ትኵር ብሎ ሲመለከት፣ የእግዚአብሔርን ክብር እንዲሁም ኢየሱስ በእግዚአብሔር ቀኝ ቆሞ አየና፣ “እነሆ፤ ሰማያት ተከፍተው፣ የሰው ልጅም በእግዚአብሔር ቀኝ ቆሞ አያለሁ” አለ። በዚህ ጊዜ በታላቅ ድምፅ እየጮኹ ጆሯቸውን ደፍነው እርሱ ወደ አለበት በአንድነት ሮጡ፤ ይዘውም ከከተማው ውጭ ጣሉት፤ በድንጋይም ይወግሩት ጀመር። ይህ በሚሆንበት ጊዜ በዚያ የነበሩ ምስክሮችም ልብሳቸውን ሳውል በተባለ ጕልማሳ እግር አጠገብ አስቀመጡ። እስጢፋኖስም እየወገሩት ሳለ፣ “ጌታ ኢየሱስ ሆይ፤ ነፍሴን ተቀበላት፤” ብሎ ጸለየ፤ ከዚያም ተንበርክኮ በታላቅ ድምፅ፣ “ጌታ ሆይ፤ ይህን ኀጢአት አትቍጠርባቸው!” ብሎ ጮኸ፤ ይህን ካለ በኋላም አንቀላፋ።
ሐዋርያት ሥራ 7:51-60 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
እናንተ አንገተ ደንዳኖች ልባችሁና ጆሮአችሁም ያልተገረዘ፥ እናንተ ሁልጊዜ መንፈስ ቅዱስን ትቃወማላችሁ፤ አባቶቻችሁ እንደ ተቃወሙት እናንተ ደግሞ። ከነቢያትስ አባቶቻችሁ ያላሳደዱት ማን ነው? የጻድቁንም መምጣት አስቀድሞ የተናገሩትን ገደሉአቸው፤ በመላእክት ሥርዓት ሕግን ተቀብላችሁ ያልጠበቃችሁት እናንተም አሁን እርሱን አሳልፋችሁ ሰጣችሁት ገደላችሁትም።” ይህንም በሰሙ ጊዜ በልባቸው በጣም ተቈጡ ጥርሳቸውንም አፋጩበት። መንፈስ ቅዱስንም ተሞልቶ ወደ ሰማይ ትኵር ብሎ ሲመለከት የእግዚአብሔርን ክብር ኢየሱስንም በእግዚአብሔር ቀኝ ቆሞ አየና፦ “እነሆ፥ ሰማያት ተከፍተው የሰው ልጅም በእግዚአብሔር ቀኝ ቆሞ አያለሁ” አለ። በታላቅ ድምፅም እየጮኹ ጆሮአቸውን ደፈኑ፥ በአንድ ልብ ሆነውም ወደ እርሱ ሮጡ፥ ከከተማም ወደ ውጭ አውጥተው ወገሩት። ምስክሮችም ልብሳቸውን ሳውል በሚሉት በአንድ ጎበዝ እግር አጠገብ አኖሩ። እስጢፋኖስም፦ “ጌታ ኢየሱስ ሆይ፥ ነፍሴን ተቀበል” ብሎ ሲጠራ ይወግሩት ነበር። ተንበርክኮም፦ “ጌታ ሆይ፥ ይህን ኃጢአት አትቍጠርባቸው ብሎ በታላቅ ድምፅ ጮኸ። ይህንም ብሎ አንቀላፋ። ሳውልም በእርሱ መገደል ተስማምቶ ነበር።
ሐዋርያት ሥራ 7:51-60 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
“እናንተ እልኸኞች ልባችሁ የተደፈነ! ጆሮአችሁም የማይሰማ! እናንተም ልክ እንዳባቶቻችሁ ሁልጊዜ መንፈስ ቅዱስን ትቃወማላችሁ። ከነቢያት መካከል አባቶቻችሁ ያላሳደዱት ማን አለ? እነርሱ የጻድቁን መምጣት አስቀድመው የተናገሩትን ገደሉአቸው፤ እናንተም አሁን ይህን ጻድቁን አሳልፋችሁ በመስጠት ገደላችሁት። እናንተ በመላእክት አማካይነት ሕግን ተቀብላችሁ ነበር፤ ነገር ግን አልጠበቃችሁትም።” የሸንጎ አባሎች ይህን በሰሙ ጊዜ ተናደዱ፤ በእስጢፋኖስ ላይም በቊጣ ጥርሳቸውን አፋጩ። እርሱ ግን በመንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ ወደ ሰማይ ትኲር ብሎ ሲመለከት የእግዚአብሔርን ክብር አየ፤ ኢየሱስንም በእግዚአብሔር ቀኝ ቆሞ አየው፤ ስለዚህ “እነሆ፥ ሰማይ ተከፍቶ የሰው ልጅ በእግዚአብሔር ቀኝ ቆሞ አያለሁ” አለ። በዚህ ጊዜ እነርሱ በታላቅ ድምፅ ጮኹ፤ ጆሮአቸውንም ደፍነው በአንድነት ወደ እርሱ ሮጡ። ከከተማ አወጡትና በድንጋይ ወገሩት፤ ምስክሮችም ልብሳቸውን ወስደው ሳውል የሚባል አንድ ጐልማሳ እንዲጠብቅላቸው በእግሩ ሥር አስቀመጡ። በድንጋይ ሲወግሩት ሳሉ እስጢፋኖስ፥ “ጌታ ኢየሱስ ሆይ! ነፍሴን ተቀበል!” ብሎ ጸለየ። ተንበርክኮም “ጌታ ሆይ! ይህን በደል አትቊጠርባቸው!” ብሎ በታላቅ ድምፅ ጮኸ፤ ይህንንም ብሎ ሞተ።
ሐዋርያት ሥራ 7:51-60 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
“እናንተ አንገተ ደንዳኖች ልባችሁና ጆሮአችሁም ያልተገረዘ፤ እናንተ ሁልጊዜ መንፈስ ቅዱስን ትቃወማላችሁ፤ አባቶቻችሁ እንደ ተቃወሙት እናንተ ደግሞ። ከነቢያትስ አባቶቻችሁ ያላሳደዱት ማን ነው? የጻድቁንም መምጣት አስቀድሞ የተናገሩትን ገደሉአቸው፤ በመላእክት ሥርዓት ሕግን ተቀብላችሁ ያልጠበቃችሁት እናንተም አሁን እርሱን አሳልፋችሁ ሰጣችሁት፤ ገደላችሁትም።” ይህንም በሰሙ ጊዜ በልባቸው በጣም ተቆጡ፤ ጥርሳቸውንም አፋጩበት። መንፈስ ቅዱስንም ተሞልቶ ወደ ሰማይ ትኩር ብሎ ሲመለከት የእግዚአብሔርን ክብር ኢየሱስንም በእግዚአብሔር ቀኝ ቆሞ አየና “እነሆ፥ ሰማያት ተከፍተው የሰው ልጅም በእግዚአብሔር ቀኝ ቆሞ አያለሁ፤” አለ። በታላቅ ድምፅም እየጮኹ ጆሮአቸውን ደፈኑ፤ በአንድ ልብ ሆነውም ወደ እርሱ ሮጡ፤ ከከተማም ወደ ውጭ አውጥተው ወገሩት። ምስክሮችም ልብሳቸውን ሳውል በሚሉት በአንድ ጎበዝ እግር አጠገብ አኖሩ። እስጢፋኖስም “ጌታ ኢየሱስ ሆይ! ነፍሴን ተቀበል፤” ብሎ ሲጠራ ይወግሩት ነበር። ተንበርክኮም “ጌታ ሆይ! ይህን ኃጢአት አትቁጠርባቸው፤” ብሎ በታላቅ ድምፅ ጮኸ። ይህንም ብሎ አንቀላፋ። ሳውልም በእርሱ መገደል ተስማምቶ ነበር።