የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ሐዋርያት ሥራ 7:17-29

ሐዋርያት ሥራ 7:17-29 NASV

“እግዚአብሔር ለአብርሃም የገባው ቃል የሚፈጸምበት ጊዜ ሲቃረብም፣ በግብጽ የነበረው የሕዝባችን ቍጥር እየበዛ ሄደ። ከዚያ በኋላ ‘ስለ ዮሴፍ የማያውቅ አዲስ ንጉሥ በግብጽ ነገሠ።’ እርሱም ሕዝባችንን በተንኰሉ አስጨነቀ፤ ገና የተወለዱ ሕፃናታቸውም ይሞቱ ዘንድ ወደ ውጭ አውጥተው እንዲጥሏቸው አስገደዳቸው። “በዚህ ጊዜ ሙሴ ተወለደ፤ እርሱም በእግዚአብሔር ፊት ሞገስን ያገኘ ውብ ሕፃን ነበር። በአባቱም ቤት ሦስት ወር በእንክብካቤ አደገ። ወደ ውጭ በተጣለም ጊዜ የፈርዖን ልጅ አግኝታ ወሰደችው፤ እንደ ራሷ ልጅ አድርጋም አሳደገችው። ሙሴም የግብፆችን ጥበብ ሁሉ ተማረ፤ በንግግሩና በተግባሩም ብርቱ ሆነ። “ሙሴ አርባ ዓመት በሆነው ጊዜ፣ ወንድሞቹን የእስራኤልን ልጆች ሊጐበኝ በልቡ ዐሰበ። እርሱም፣ አንድ ግብጻዊ ከወገኖቹ አንዱን በደል ሲያደርስበት አይቶ ግብጻዊውንም ገደለ፤ ለተገፋው ወገኑም ተበቀለ። ወገኖቹም እግዚአብሔር በርሱ እጅ ነጻ እንደሚያወጣቸው የሚያስተውሉ መስሎት ነበር፤ እነርሱ ግን አላስተዋሉም። በማግስቱም ደግሞ ሁለት እስራኤላውያን ሲጣሉ ደረሰ፤ ሊያስታርቃቸውም ፈልጎ፣ ‘ሰዎች፤ እናንተ እኮ ወንድማማቾች ናችሁ፤ እንዴት እርስ በርሳችሁ ትጐዳዳላችሁ?’ አላቸው። “በባልንጀራው ላይ በደል ሲያደርስ የነበረው ሰው ግን፣ ሙሴን ገፈተረውና እንዲህ አለ፤ ‘አንተን በእኛ ላይ ገዥና ዳኛ አድርጎ የሾመህ ማን ነው? ትናንት ግብጻዊውን እንደ ገደልኸው እኔንም ልትገድለኝ ትፈልጋልህን?’ ሙሴም ይህን እንደ ሰማ ሸሽቶ በምድያም አገር መጻተኛ ሆኖ ተቀመጠ፤ በዚያም ሁለት ወንዶች ልጆች ወለደ።