የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ሐዋርያት ሥራ 5:17-26

ሐዋርያት ሥራ 5:17-26 NASV

ከዚህም የተነሣ ሊቀ ካህናቱና ዐብረውት የነበሩት የሰዱቃውያን ወገን ሁሉ በቅናት ተሞሉ፤ ሐዋርያትንም ይዘው ማረፊያ ቤት ከተቷቸው። ይሁን እንጂ የጌታ መልአክ በሌሊት የእስር ቤቱን ደጆች ከፍቶ አወጣቸውና፣ “ሂዱ፤ በቤተ መቅደሱም አደባባይ ቁሙ፤ የዚህንም ሕይወት ቃል ሁሉ ለሕዝብ ንገሩ” አላቸው። እንደ ነጋም፣ በተነገራቸው መሠረት ወደ ቤተ መቅደሱ አደባባይ ገብተው ሕዝቡን ማስተማር ጀመሩ። ሊቀ ካህናቱና ከርሱ ጋራ የነበሩት መጥተው የአይሁድን ሸንጎና የእስራኤልን ሽማግሌዎች ጉባኤ በሙሉ በአንድነት ሰበሰቡ፤ ሐዋርያትንም እንዲያመጡ ሰዎችን ወደ እስር ቤት ላኩ። አገልጋዮቹም ወደ እስር ቤቱ ሄደው በዚያ አላገኟቸውም፤ ተመልሰውም እንዲህ አሏቸው፤ “እስር ቤቱ በሚገባ ተቈልፎ፣ ጠባቂዎቹም በበሩ ላይ ቆመው አገኘን፤ ከፍተን ስንገባ ግን በውስጡ ማንም አልነበረም።” የቤተ መቅደሱ ጥበቃ ሹምና የካህናት አለቆችም ይህን በሰሙ ጊዜ በነገሩ ተገረሙ፤ ግራም ተጋቡ። በዚህ ጊዜ አንድ ሰው መጥቶ፣ “እነሆ፤ እስር ቤት ያስገባችኋቸው ሰዎች በቤተ መቅደሱ አደባባይ ቆመው ሕዝቡን እያስተማሩ ናቸው” አላቸው። የአገልጋዮቹ ሹሙም ከወታደሮቹ ጋራ ሄዶ፣ ይዞ አመጣቸው፤ ያመጧቸው ግን ሕዝቡ በድንጋይ እንዳይወግሯቸው ስለ ፈሩ በኀይል ሳያስገድዱ ነበር።