የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

2 ነገሥት 2:1-11

2 ነገሥት 2:1-11 NASV

እግዚአብሔር ኤልያስን በዐውሎ ነፋስ ወደ ሰማይ የሚወስድበት ጊዜ ሲደርስ፣ ኤልያስና ኤልሳዕ ከጌልገላ ተነሥተው ይጓዙ ነበር። ኤልያስም ኤልሳዕን፣ “እግዚአብሔር እኔን ወደ ቤቴል ልኮኛልና አንተ በዚሁ ቈይ” አለው። ኤልሳዕ ግን፣ “ሕያው እግዚአብሔርን፣ በሕያው ነፍስህም እምላለሁ፤ ከአንተ አልለይም” አለው። ስለዚህ ዐብረው ወደ ቤቴል ወረዱ። በቤቴል የነበሩ የነቢያት ማኅበር ወደ ኤልሳዕ ወጥተው፣ “እግዚአብሔር፣ ጌታህን ኤልያስን ዛሬ ከአንተ ነጥሎ እንደሚወስደው ዐውቀሃልን?” አሉት። ኤልሳዕም፣ “አዎን ዐውቄአለሁ፤ እናንተ ግን ዝም በሉ” አለ። ከዚያም ኤልያስ፣ “ኤልሳዕ ሆይ፤ እግዚአብሔር እኔን ወደ ኢያሪኮ ልኮኛልና አንተ በዚሁ ቈይ” አለው። እርሱም፤ “ሕያው እግዚአብሔርን፣ በሕያው ነፍስህም እምላለሁ፤ ከአንተ አልለይም” ሲል መለሰ። ስለዚህ ዐብረው ወደ ኢያሪኮ ሄዱ። በኢያሪኮ የነበሩትም የነቢያት ማኅበር ወደ ኤልሳዕ ወጥተው፣ “ለመሆኑ እግዚአብሔር፣ ጌታህን ኤልያስን ዛሬ ከአንተ ነጥሎ እንደሚወስደው ዐውቀሃልን?” አሉት። እርሱም፣ “አዎን ዐውቄአለሁ፤ እናንተ ግን ዝም በሉ” ሲል መለሰ። ከዚያም ኤልያስ፣ “እግዚአብሔር እኔን ወደ ዮርዳኖስ ልኮኛልና አንተ እዚሁ ቈይ” አለው። እርሱም፣ “ሕያው እግዚአብሔርን፤ በሕያው ነፍስህም እምላለሁ፤ ከአንተ አልለይም” ሲል መለሰ። ስለዚህ ሁለቱም ዐብረው ሄዱ። ከነቢያትም ማኅበር ዐምሳው ሄደው፣ ኤልያስና ኤልሳዕ ከቆሙበት ከዮርዳኖስ ትይዩ ራቅ ብለው ቆሙ። ኤልያስም ካባውን አውልቆ ጠቀለለውና ውሃውን መታበት፤ ከዚያም ውሃው ግራና ቀኝ ተከፈለ፤ ሁለቱም በደረቅ ምድር ተሻገሩ። ከተሻገሩ በኋላም ኤልያስ ኤልሳዕን፤ “ከአንተ ከመወሰዴ በፊት ምን ላደርግልህ እንደምትፈልግ ንገረኝ” አለው። ኤልሳዕም፣ “መንፈስህ በዕጥፍ እንዲያድርብኝ እለምንሃለሁ” ብሎ መለሰ። ኤልያስም፣ “አስቸጋሪ ነገር ጠይቀሃል፤ ይሁን እንጂ እኔ ከአንተ ስወሰድ ብታየኝ፣ እንዳልከው ይሆንልሃል፤ አለዚያ ግን አይሆንም” አለው። እያዘገሙም ሲነጋገሩ ሳለ፣ የእሳት ሠረገላና የእሳት ፈረሶች ድንገት በመካከላቸው ገብተው ሁለቱን ለዩአቸው፤ ኤልያስም በዐውሎ ነፋስ ወደ ሰማይ ዐረገ።