2 ዜና መዋዕል 35:1-15

2 ዜና መዋዕል 35:1-15 NASV

ኢዮስያስ በኢየሩሳሌም ለእግዚአብሔር ፋሲካን አደረገ፤ በመጀመሪያውም ወር በዐሥራ አራተኛው ቀን የፋሲካው በግ ታረደ። ካህናቱን በየአገልግሎታቸው መደበ፤ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ አገልግሎትም እንዲተጉ አበረታታቸው። እስራኤልን ሁሉ ያስተምሩ ለነበሩትና ራሳቸውን ለእግዚአብሔር ለቀደሱት ሌዋውያን እንዲህ አላቸው፤ “የእግዚአብሔርን ታቦት የእስራኤል ንጉሥ የዳዊት ልጅ ሰሎሞን ባሠራው ቤተ መቅደስ አኑሩ፤ በእናንተ ትከሻ አትሸከሙት፤ አሁንም አምላካችሁን እግዚአብሔርንና ሕዝቡን እስራኤልን አገልግሉ። በእስራኤል ንጉሥ በዳዊትና በልጁ በሰሎሞን በተጻፈው መመሪያ መሠረት፣ እንደየቤተ ሰባችሁ በክፍል በክፍላችሁ ራሳችሁን አዘጋጁ። “ሌዋውያን ባልሆኑ ወንድሞቻችሁ አንጻር እንደየቤተ ሰቡ ምድብ በተቀደሰው ስፍራ ቁሙ፤ ለእያንዳንዱም የቤተ ሰብ ምድብ ሌዋውያን ይኑሩት። ከዚያም የፋሲካውን በጎች ዕረዱ፤ ራሳችሁን ቀድሱ፤ እግዚአብሔር በሙሴ አማካይነት ባዘዘውም መሠረት ዕርዶቹን ለወንድሞቻችሁ አዘጋጁ።” ኢዮስያስም እዚያ ለነበሩት ሕዝብ ሁሉ ለፋሲካው መሥዋዕት እንዲሆኑ በአጠቃላይ ሠላሳ ሺሕ በግና ፍየል እንዲሁም ሦስት ሺሕ ወይፈን ከንጉሡ ሀብት ሰጠ። ሹማምቱም ለሕዝቡ፣ ለካህናቱና ለሌዋውያኑ በገዛ ፈቃዳቸው አዋጥተው ሰጡ። የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ አለቆች የሆኑት ኬልቅያስ፣ ዘካርያስና ይሒኤልም ለፋሲካ መሥዋዕት የሚቀርቡ ሁለት ሺሕ ስድስት መቶ በግ እንዲሁም ሦስት መቶ ወይፈን ሰጡ። ደግሞም ኮናንያ፣ ወንድሞቹ ሸማያና ናትናኤል እንደዚሁም የሌዋውያኑ መሪዎች ሐሸቢያ፣ ይዔኤልና ዮዛባት ለፋሲካ መሥዋዕት እንዲሆኑ ዐምስት ሺሕ በግና ፍየል ዐምስት መቶም በሬ ለሌዋውያኑ ሰጧቸው። የአገልግሎቱ ዝግጅት በተጠናቀቀ ጊዜ፣ ንጉሡ ባዘዘው መሠረት ካህናቱ በየክፍላቸው ከተመደቡት ሌዋውያን ጋራ ቦታ ቦታቸውን ይዘው ቆሙ። የፋሲካው በጎች ታረዱ፤ ካህናቱ የተቀበሉትን ደም ረጩ፤ ሌዋውያኑም የበጎቹን ቈዳ ገፈፉ። በሙሴ ሕግ እንደ ተጻፈው ለእግዚአብሔር እንዲያቀርቡም፣ እንደየቤተ ሰቡና እንደየምድቡ ለሕዝቡ ለመስጠት የሚቃጠለውን መሥዋዕት ለዩ፤ ወይፈኖቹንም እንደዚሁ አደረጉ። እነርሱም የፋሲካውን መሥዋዕት በሥርዐቱ መሠረት ጠበሱ፤ የተቀደሰውንም ቍርባን በምንቸት፣ በሰታቴና በድስት ቀቀሉ፤ ወዲያውኑም ለሕዝቡ አደሉ። ከዚህ በኋላ ለራሳቸውና ለካህናቱ ዝግጅት አደረጉ፤ ምክንያቱም ካህናቱ የአሮን ልጆች የሚቃጠለውን መሥዋዕትና ሥቡን እስከ ሌሊት ድረስ ያቀርቡ ስለ ነበር ነው። ስለዚህ ሌዋውያኑ ለራሳቸውና ለካህናቱ ለአሮን ልጆች ዝግጅት አደረጉ። መዘምራኑ የአሳፍ ዘሮች በዳዊት፣ በአሳፍ፣ በኤማንና በንጉሡ ባለራእይ በኤዶታም በተሰጠው መመሪያ መሠረት በቦታቸው ነበሩ። በእያንዳንዱ በር ላይ የነበሩት በር ጠባቂዎችም ሌዋውያን ወገኖቻቸው ስላዘጋጁላቸው፣ ከጥበቃ ቦታቸው መለየት አያስፈልጋቸውም ነበር።