የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

1 ሳሙኤል 2:12-36

1 ሳሙኤል 2:12-36 NASV

የዔሊ ልጆች ምናምንቴ ሰዎች ነበሩ፤ እግዚአብሔርንም አይፈሩም ነበር። በዚያ ጊዜ ካህናቱ ከሕዝቡ ጋራ ባላቸው ግንኙነት የሚፈጽሙት ወግ ነበር፤ ይኸውም ማንም ሰው መሥዋዕት በሚያቀርብበት ጊዜ፣ ሥጋው እየተቀቀለ ሳለ የካህኑ አገልጋይ ሦስት ጣት ያለውን ሜንጦ ይዞ ይመጣል፤ ወደ ድስቱ ወይም ወደ ቶፋው ወይም ወደ አፍላሉ፣ ወይም ወደ ምንቸቱ ይሰደዋል። ከዚያም ካህኑ ሜንጦው ያወጣውን ማንኛውንም ሥጋ ለራሱ ይወስደዋል። ወደ ሴሎ የሚመጡትን እስራኤላውያን ሁሉ የሚያስተናግዱት በዚህ ዐይነት ነበር። ነገር ግን ሥቡ ገና ከመቃጠሉ በፊት የካህኑ አገልጋይ መጥቶ መሥዋዕት የሚያቀርበውን ሰው፣ “ካህኑ ጥሬውን እንጂ የተቀቀለውን ሥጋ ከአንተ ስለማይቀበል፣ ለካህኑ የሚጠበስ ሥጋ ስጠኝ” ይለው ነበር። ሰውየውም፣ “በመጀመሪያ ሥቡ ይቃጠል፤ ከዚያ በኋላ የምትፈልገውን ትወስዳለህ” ቢለው እንኳ አገልጋዩ፣ “አይሆንም፤ አሁኑኑ ስጠኝ፤ አለዚያ በግድ እወስዳለሁ” ይለው ነበር። ለእግዚአብሔር የሚቀርበውን መሥዋዕት ይንቁ ስለ ነበር፣ ይህ የወጣቶቹ ኀጢአት በእግዚአብሔር ፊት እጅግ ታላቅ ነበረ። ብላቴናው ሳሙኤል ግን ከበፍታ የተሠራ ኤፉድ ለብሶ በእግዚአብሔር ፊት ያገለግል ነበር። እናቱም ከባሏ ጋራ ዓመታዊ መሥዋዕት ለማቅረብ በምትሄድበት ጊዜ ሁሉ ትንሽ መደረቢያ እየሠራች ይዛለት ትሄድ ነበር። ዔሊም፣ “በጸሎት ባገኘችውና ለእግዚአብሔር በሰጠችው ልጅ ምትክ እግዚአብሔር ከዚህችው ሴት ዘር ይስጥህ” እያለ ሕልቃናንና ሚስቱን ይመርቃቸው ነበር፤ ከዚያ በኋላ ወደ ቤታቸው ይመለሱ ነበር። እግዚአብሔርም ሐናን ዐሰባት፤ ፀነሰችም፤ ሦስት ወንዶች፣ ሁለት ሴቶች ልጆችም ወለደች። ብላቴናውም ሳሙኤል በእግዚአብሔር ፊት አደገ። በዚህ ጊዜ ዔሊ እጅግ አርጅቶ ነበር፤ ልጆቹም በመላው እስራኤል ያደርጉ የነበረውን፣ በመገናኛውም ድንኳን ደጃፍ ከሚያገለግሉ ሴቶች ጋራ ዝሙት መፈጸማቸውን ሰማ። ስለዚህም እንዲህ አላቸው፤ “ስለምትፈጽሙት ክፉ ድርጊት ከመላው ሕዝብ እሰማለሁ፤ ለምን እንዲህ ያለ ነገር ታደርጋላችሁ? ልጆቼ ሆይ፤ ትክክል አይደላችሁም፤ በእግዚአብሔር ሕዝብ መካከል ተሠራጭቶ የምሰማባችሁ ወሬ ጥሩ አይደለም። አንድ ሰው ሌላውን ቢበድል፣ እግዚአብሔር ጣልቃ ገብቶ ይፈርዳል፤ ነገር ግን ሰው እግዚአብሔርን ቢበድል፣ ማን ይማልድለታል?” ይሁን እንጂ እግዚአብሔር ሊያጠፋቸው ስለ ፈለገ፣ ልጆቹ የአባታቸውን ተግሣጽ አልሰሙም። ብላቴናውም ሳሙኤል በአካልና በሞገስ በእግዚአብሔርና በሰው ፊት እያደገ ሄደ። በዚህ ጊዜ አንድ የእግዚአብሔር ሰው ወደ ዔሊ መጥቶ እንዲህ አለው፤ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘የአባትህ ቤት በግብጽ ምድር በፈርዖን እጅ በነበረ ጊዜ ራሴን ገለጥሁለት? የእኔ ካህን እንዲሆን፣ ወደ መሠዊያዬ እንዲወጣ፣ ዕጣን እንዲያጥን፣ በፊቴም ኤፉድ እንዲለብስ ከእስራኤል ነገዶች ሁሉ አባትህን መረጥሁት። ደግሞም እስራኤላውያን በእሳት የሚያቀርቡትን ቍርባን ሁሉ ለአባትህ ቤት ሰጠሁ። ታዲያ በማደሪያዬ እንዲቀርብ ያዘዝሁትን መሥዋዕትና ቍርባን የናቃችሁ ለምንድን ነው? አንተና ልጆችህ ሕዝቤ እስራኤል ካቀረበው ቍርባን ሁሉ ምርጥ ምርጡን በልታችሁ ራሳችሁን በማወፈር ከእኔ ይልቅ ልጆችህን የምታከብራቸው ስለ ምንድን ነው?’ “ስለዚህ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ቤትህና የአባትህ ቤት በፊቴ ለዘላለም ያገለግሉኝ ዘንድ ተስፋ ሰጥቼ ነበር፤’ አሁን ግን እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ይህን ከእንግዲህ አላደርገውም፤ የሚያከብሩኝን አከብራለሁ፤ የሚንቁኝም ፈጽሞ ይናቃሉ። እነሆ፤ በዘርህ ሽማግሌ እንዳይገኝ ያንተን ኀይልና የአባትህን ቤተ ሰብ ኀይል የምሰብርበት ጊዜ ይመጣል፤ በማደሪያዬም መከራ ታያለህ፤ ምንም እንኳ ለእስራኤል በጎ ነገር ቢደረግም፣ በቤተ ሰብህ ውስጥ ሽማግሌ ፈጽሞ አይገኝም። ከመሠዊያዬ የማላስወግዳቸው ዘሮችህ በሕይወት የሚተርፉትም ዐይኖችህን በእንባ ለማፍዘዝ፣ ልብህን በሐዘን ለማደንዘዝ ብቻ ነው፣ ሌሎቹ ዘሮችህ ግን በሙሉ በለጋነታቸው በዐጭር ይቀጫሉ። “ ‘በሁለቱ ልጆችህ በአፍኒንና በፊንሐስ ላይ የሚደርሰው ላንተ ምልክት ይሆንሃል፣ ሁለቱም በአንድ ቀን ይሞታሉ። እንደ ልቤና እንደ አሳቤ የሚያገለግል የታመነ ካህን ለራሴ አስነሣለሁ፤ ቤቱን አጽንቼ አቆማለሁ፣ እርሱም በቀባሁት ፊት ለዘላለም ያገለግላል። ከዘሮችህም መካከል የተረፈው ማንኛውም ሰው፣ ለአንዲት ጥሬ ብርና ለቍራሽ እንጀራ ሲል በፊቱ ወድቆ ይሰግዳል፤ “የዕለት ጕርሴን እንዳገኝ እባክህ በማንኛውም የክህነት ሥራ ላይ መድበኝ” በማለት ይለምናል።’ ”