የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

1 ሳሙኤል 19:1-24

1 ሳሙኤል 19:1-24 NASV

ሳኦል ዳዊትን እንዲገድሉት ለልጁ ለዮናታንና ለባልሟሎቹ ነገራቸው። ዮናታን ግን ዳዊትን እጅግ ይወድደው ነበር፣ እንዲህ ሲል አስጠነቀቀው፤ “አባቴ ሳኦል ሊገድልህ አጋጣሚ እየፈለገ ነው፤ ነገ ጧት ተጠንቀቅ፤ ወደ አንድ መደበቂያ ቦታም ሂድ፤ በዚያም ቈይ። እኔም እወጣና አንተ ባለህበት ዕርሻ ከአባቴ አጠገብ እቆማለሁ፤ ስለ አንተም አነጋግረዋለሁ፤ የተረዳሁትንም እነግርሃለሁ።” ዮናታን ለአባቱ ለሳኦል ስለ ዳዊት እንዲህ ሲል መልካም ነገር ተናገረ፣ “ንጉሥ በአገልጋዩ በዳዊት ላይ ክፉ ነገር አያድርግ፤ እርሱ አልበደለህም፤ ያደረገውም ነገር በእጅጉ ጠቅሞሃል። ዳዊት ፍልስጥኤማዊውን የገደለው በገዛ ሕይወቱ ቈርጦ ነው። እግዚአብሔር ለመላው እስራኤል ታላቅ ድልን አቀዳጀ፤ አንተም አይተህ ደስ አለህ። ታዲያ እርሱን በከንቱ በመግደል ዳዊትን በመሰለ ንጹሕ ሰው ላይ ለምን በደል ትፈጽማለህ?” ሳኦልም ዮናታንን ካዳመጠው በኋላ፣ “ሕያው እግዚአብሔርን! ዳዊት አይገደልም” ብሎ ማለ። ስለዚህም ዮናታን ዳዊትን ጠርቶ የተባባሉትን ሁሉ ነገረው፤ ወደ ሳኦልም አመጣው፤ ዳዊትም እንደ ቀድሞው በፊቱ ቆመ። እንደ ገና ሌላ ጦርነት ተነሣ፤ ዳዊትም ወጥቶ ፍልስጥኤማውያንን ወጋቸው፤ ከፊቱም እስኪሸሹ ድረስ እጅግ መታቸው። ነገር ግን ሳኦል ጦሩን ይዞ በቤቱ ተቀምጦ ሳለ፣ ከእግዚአብሔር ዘንድ ክፉ መንፈስ መጣበት፤ ዳዊት በገናውን ይደረድር ነበር፣ ሳኦልም ከግድግዳው ጋር ሊያጣብቀው ጦሩን ወረወረበት፤ ነገር ግን ዳዊት ዘወር በማለቱ ሳኦል የወረወረው ጦር በግድግዳው ላይ ተሰካ። በዚያች ሌሊት ዳዊት ሸሽቶ አመለጠ። ሳኦልም የዳዊትን ቤት ከብበው በማለዳ እንዲገድሉት ሰዎችን ላከ። የዳዊት ሚስት ሜልኮል ግን፣ “ሕይወትህን ለማትረፍ በዚህች ሌሊት ካልሸሸህ፣ በነገው ቀን ትገደላለህ” ብላ አስጠነቀቀችው። ሜልኮልም ዳዊትን በመስኮት አሾልካ አወረደችው፣ እርሱም ሸሽቶ አመለጠ። ከዚያም ሜልኮል የጣዖት ምስል ወስዳ በዐልጋው ላይ አጋደመችው፤ በራስጌውም የፍየል ጠጕር አኖረች፤ በልብስም ሸፈነችው። ሳኦል ዳዊትን እንዲይዙት ሰዎች በላከ ጊዜ ሜልኮል፣ “እርሱ ታሟል” አለቻቸው። ሳኦልም ሰዎቹ ዳዊትን እንዲያዩት መልሶ ላካቸው፤ እርሱም፣ “እገድለው ዘንድ ከነዐልጋው አምጡልኝ” አላቸው። የተላኩትም ሰዎች በገቡ ጊዜ እነሆ፤ የጣዖት ምስሉ በዐልጋው ላይ ተጋድሞ በራስጌውም የፍየል ጠጕር ተደርጎለት ነበር። ሳኦልም ሜልኮልን፣ “እንዲህ አድርገሽ ያታለልሽኝ፣ ጠላቴ እንዲያመልጥ የሰደድሽው ለምንድን ነው?” ሲል ጠየቃት። ሜልኮልም፣ “ ‘እንዳመልጥ እርጂኝ፤ አለዚያ እገድልሻለሁ’ አለኝ” ብላ መለሰችለት። ዳዊት ሸሽቶ ካመለጠ በኋላ፣ ወደ አርማቴም ወደ ሳሙኤል ሄደ፣ ሳኦል ያደረገበትን ሁሉ ነገረው። ከዚያም እርሱና ሳሙኤል ወደ ነዋት ሄደው ተቀመጡ። ለሳኦልም፣ “እነሆ፤ ዳዊት በአርማቴም በምትገኘው በነዋት ተቀምጧል” ብለው ነገሩት። ስለዚህ ዳዊትን እንዲይዙ ሰዎችን ላከ፤ ይሁን እንጂ፣ የነቢያትም ጉባኤ በሳሙኤል መሪነት ትንቢት ሲናገሩ ባዩ ጊዜ፣ የእግዚአብሔር መንፈስ በሳኦል ሰዎች ላይ ወረደ፤ እነርሱም እንደዚሁ ትንቢት ተናገሩ። ሳኦልም ይህ በተነገረው ጊዜ ሌሎች ሰዎች ላከ፤ እነርሱም ትንቢት ተናገሩ፤ ሳኦል ለሦስተኛ ጊዜ ሰዎች ላከ፣ እነርሱም ደግሞ ትንቢት ተናገሩ። በመጨረሻም፣ እርሱ ራሱ ወደ አርማቴም ሄደ፤ ከዚያም በሤኩ ወዳለው ትልቅ የውሃ ማጠራቀሚያ ጕድጓድ እንደ ደረሰ፣ “ሳሙኤልና ዳዊት የት ናቸው?” ሲል ጠየቀ። አንድ ሰውም “በአርማቴም በምትገኘው በነዋት ዘራማ ናቸው” ብሎ ነገረው። ስለዚህ ሳኦል በአርማቴም ወደምትገኘው ወደ ነዋት ዘራማ ሄደ፤ የእግዚአብሔር መንፈስ በእርሱም ላይ ደግሞ ወረደ፤ ወደ ነዋት እስኪደርስ ድረስም ትንቢት እየተናገረ ተጓዘ። እርሱም ልብሱን አውልቆ፣ በሳሙኤልም ፊት ደግሞ ትንቢት ተናገረ፤ በዚህ ሁኔታም ቀኑንና ሌሊቱን በሙሉ ራቍቱን ተጋደመ። ሕዝቡ፣ “ሳኦልም ደግሞ ከነቢያት እንደ አንዱ ሆኖ ተቈጠረ?” ያለው በዚህ ምክንያት ነው።