1 ሳሙኤል 19:1-24
1 ሳሙኤል 19:1-24 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ሳኦልም ለልጁ ለዮናታንና ለብላቴኖቹ ሁሉ ዳዊትን ይገድሉ ዘንድ ነገራቸው። የሳኦል ልጅ ዮናታን ግን ዳዊትን እጅግ ይወድደው ነበር። ዮናታንም፥ “አባቴ ሳኦል ሊገድልህ ፈልጎአል፤ አሁን እንግዲህ ለነገው ተጠንቅቀህ ተሸሸግ፤ በስውርም ተቀመጥ። እኔም እወጣለሁ፤ አንተም ባለህበት እርሻ በአባቴ አጠገብ እቆማለሁ፤ ስለ አንተም ለአባቴ እነግረዋለሁ፤ የሆነውንም አይቼ እነግርሃለሁ” ብሎ ለዳዊት ነገረው። ዮናታንም ለአባቱ ለሳኦል ስለ ዳዊት መልካም ተናገረ እንዲህም አለው፥ “እርሱ አልበደለህምና፥ ሥራውም ለአንተ እጅግ መልካም ሆኖአልና ንጉሡ ባሪያውን ዳዊትን አይበድለው፤ ነፍሱንም በእጁ ጥሎ ፍልስጥኤማዊዉን ገደለ፤ እግዚአብሔርም በእርሱ ታላቅ መድኀኒት አደረገ፤ እስራኤልም ሁሉ አይተው ደስ አላቸው፤ በከንቱ ዳዊትን ትገድለው ዘንድ ስለምን በንጹሕ ደም ላይ ትበድላለህ?” ሳኦልም የዮናታንን ቃል ሰማ፤ ሳኦልም፥ “ሕያው እግዚአብሔርን! ዳዊት አይገደልም” ብሎ ማለ። ዮናታንም ዳዊትን ጠርቶ ይህን ነገር ሁሉ ነገረው፤ ዮናታንም ዳዊትን ወደ ሳኦል አመጣው፤ እንደ ቀድሞውም በፊቱ ነበረ። ደግሞም ጦርነት ሆነ፤ ዳዊትም ወጥቶ ከፍልስጥኤማውያን ጋር ተዋጋ፤ ታላቅ ግዳይም ገደላቸው፤ ከፊቱም ሸሹ። ሳኦልም ጦሩን ይዞ በቤቱ ተቀምጦ ሳለ ክፉ መንፈስ ከእግዚአብሔር ዘንድ ያዘው። ዳዊትም በእጁ በገና ይመታ ነበር። ሳኦልም ዳዊትን ከግንብ ጋር ያጣብቀው ዘንድ ጦሩን ወረወረ፤ ዳዊትም ከሳኦል ፊት ዘወር አለ፤ ጦሩም በግንቡ ውስጥ ተተከለ፤ በዚያም ሌሊት ዳዊት ሸሸቶ አመለጠ። ሳኦልም ዳዊትን ጠበቀው፤ በነጋው እንዲገድሉት መልእክተኞቹን ወደ ዳዊት ቤት ላከ፤ ሚስቱም ሜልኮል፥ “በዚህች ሌሊት ነፍስህን ካላዳንህ ነገ ትገደላለህ” ብላ ነገረችው። ሜልኮልም ዳዊትን በመስኮት አወረደችው፤ ሄደም፤ ሸሽቶም አመለጠ። ሜልኮልም ተራፊምን ወስዳ በአልጋ ላይ አኖረችው፤ በራስጌውም ጕንጕን የፍየል ጠጕር አደረገች፤ በልብስም ከደነችው። ሳኦልም ዳዊትን ይዘው እንዲያመጡት መልእክተኞችን ላከ፤ እርስዋም ታሞአል አለቻቸው። ሳኦልም፥ “እገድለው ዘንድ ዳዊትን ከነአልጋው” አምጡልኝ ብሎ መልእክተኞቹን ወደ ዳዊት ላከ። መልእክተኞቹም በገቡ ጊዜ እነሆ፥ ተራፊሙን በአልጋው ላይ አገኙ፤ በራስጌውም ጕንጕን የፍየል ጠጕር ነበረ። ሳኦልም ሜልኮልን አላት፥ “ስለምን እንዲህ አታለልሽኝ? ጠላቴን አስኰበለልሽ፤ እንዲያመልጥም አደረግሽው?” ሜልኮልም ለሳኦል፥ “እርሱ፦ አውጥተሽ ስደጂኝ፤ አለዚያ እገድልሻለሁ አለኝ” አለችው። ዳዊትም ሸሽቶ አመለጠ፤ ወደ አርማቴምም ወደ ሳሙኤል መጣ፤ ሳኦልም ያደረገበትን ሁሉ ነገረው፤ እርሱና ሳሙኤልም ሄዱ፤ በአውቴዘራማም ተቀመጡ። ለሳኦልም፥ “ዳዊት እነሆ፥ በአውቴዘራማ ተቀምጦአል” ብለው ነገሩት። ሳኦልም ዳዊትን ያመጡት ዘንድ መልእክተኞችን ላከ፤ የነቢያትንም ጉባኤ አገኙ፤ ሳሙኤልም አለቃቸው ሆኖ በመካከላቸው ቆሞ ነበረ፤ የእግዚአብሔርም መንፈስ በሳኦል መልእክተኞች ላይ ወረደ፤ እነርሱም ትንቢት ይናገሩ ጀመር። ለሳኦልም ይህን በነገሩት ጊዜ ሌሎች መልእክተኞችን ላከ፤ እነርሱም ደግሞ ትንቢት ተናገሩ። ሳኦልም እንደ ገና ሦስተኛ ጊዜ መልእክተኞችን ላከ፤ እነርሱም ደግሞ ትንቢት ተናገሩ። ሳኦልም እጅግ ተቈጣ፤ እርሱም ደግሞ ወደ አርማቴም መጣ፤ በመሴፋም አውድማ ወዳለው ወደ ታላቁ የውኃ ጕድጓድ ደረሰ። “ሳሙኤልና ዳዊት የት ናቸው?” ብሎ ጠየቀ፤ “እነሆ፥ በአውቴዘራማ ናቸው” አሉት። ወደ አውቴዘራማም ሄደ፤ የእግዚአብሔርም መንፈስ በእርሱ ደግሞ ወረደ፤ እርሱም ሄደ፤ ወደ አውቴዘራማም እስኪመጣ ድረስ ትንቢት ይናገር ነበር። ልብሱንም አወለቀ፤ በፊታቸውም ትንቢት ተናገረ፤ ራቁቱንም ወድቆ በዚያ ቀን ሁሉ በዚያም ሌሊት ሁሉ ተጋደመ። ስለዚህ፥ “ሳኦል ደግሞ ከነቢያት መካከል ነውን?” ይባባሉ ነበር።
1 ሳሙኤል 19:1-24 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ሳኦል ዳዊትን እንዲገድሉት ለልጁ ለዮናታንና ለባልሟሎቹ ነገራቸው። ዮናታን ግን ዳዊትን እጅግ ይወድደው ነበር፣ እንዲህ ሲል አስጠነቀቀው፤ “አባቴ ሳኦል ሊገድልህ አጋጣሚ እየፈለገ ነው፤ ነገ ጧት ተጠንቀቅ፤ ወደ አንድ መደበቂያ ቦታም ሂድ፤ በዚያም ቈይ። እኔም እወጣና አንተ ባለህበት ዕርሻ ከአባቴ አጠገብ እቆማለሁ፤ ስለ አንተም አነጋግረዋለሁ፤ የተረዳሁትንም እነግርሃለሁ።” ዮናታን ለአባቱ ለሳኦል ስለ ዳዊት እንዲህ ሲል መልካም ነገር ተናገረ፣ “ንጉሥ በአገልጋዩ በዳዊት ላይ ክፉ ነገር አያድርግ፤ እርሱ አልበደለህም፤ ያደረገውም ነገር በእጅጉ ጠቅሞሃል። ዳዊት ፍልስጥኤማዊውን የገደለው በገዛ ሕይወቱ ቈርጦ ነው። እግዚአብሔር ለመላው እስራኤል ታላቅ ድልን አቀዳጀ፤ አንተም አይተህ ደስ አለህ። ታዲያ እርሱን በከንቱ በመግደል ዳዊትን በመሰለ ንጹሕ ሰው ላይ ለምን በደል ትፈጽማለህ?” ሳኦልም ዮናታንን ካዳመጠው በኋላ፣ “ሕያው እግዚአብሔርን! ዳዊት አይገደልም” ብሎ ማለ። ስለዚህም ዮናታን ዳዊትን ጠርቶ የተባባሉትን ሁሉ ነገረው፤ ወደ ሳኦልም አመጣው፤ ዳዊትም እንደ ቀድሞው በፊቱ ቆመ። እንደ ገና ሌላ ጦርነት ተነሣ፤ ዳዊትም ወጥቶ ፍልስጥኤማውያንን ወጋቸው፤ ከፊቱም እስኪሸሹ ድረስ እጅግ መታቸው። ነገር ግን ሳኦል ጦሩን ይዞ በቤቱ ተቀምጦ ሳለ፣ ከእግዚአብሔር ዘንድ ክፉ መንፈስ መጣበት፤ ዳዊት በገናውን ይደረድር ነበር፣ ሳኦልም ከግድግዳው ጋር ሊያጣብቀው ጦሩን ወረወረበት፤ ነገር ግን ዳዊት ዘወር በማለቱ ሳኦል የወረወረው ጦር በግድግዳው ላይ ተሰካ። በዚያች ሌሊት ዳዊት ሸሽቶ አመለጠ። ሳኦልም የዳዊትን ቤት ከብበው በማለዳ እንዲገድሉት ሰዎችን ላከ። የዳዊት ሚስት ሜልኮል ግን፣ “ሕይወትህን ለማትረፍ በዚህች ሌሊት ካልሸሸህ፣ በነገው ቀን ትገደላለህ” ብላ አስጠነቀቀችው። ሜልኮልም ዳዊትን በመስኮት አሾልካ አወረደችው፣ እርሱም ሸሽቶ አመለጠ። ከዚያም ሜልኮል የጣዖት ምስል ወስዳ በዐልጋው ላይ አጋደመችው፤ በራስጌውም የፍየል ጠጕር አኖረች፤ በልብስም ሸፈነችው። ሳኦል ዳዊትን እንዲይዙት ሰዎች በላከ ጊዜ ሜልኮል፣ “እርሱ ታሟል” አለቻቸው። ሳኦልም ሰዎቹ ዳዊትን እንዲያዩት መልሶ ላካቸው፤ እርሱም፣ “እገድለው ዘንድ ከነዐልጋው አምጡልኝ” አላቸው። የተላኩትም ሰዎች በገቡ ጊዜ እነሆ፤ የጣዖት ምስሉ በዐልጋው ላይ ተጋድሞ በራስጌውም የፍየል ጠጕር ተደርጎለት ነበር። ሳኦልም ሜልኮልን፣ “እንዲህ አድርገሽ ያታለልሽኝ፣ ጠላቴ እንዲያመልጥ የሰደድሽው ለምንድን ነው?” ሲል ጠየቃት። ሜልኮልም፣ “ ‘እንዳመልጥ እርጂኝ፤ አለዚያ እገድልሻለሁ’ አለኝ” ብላ መለሰችለት። ዳዊት ሸሽቶ ካመለጠ በኋላ፣ ወደ አርማቴም ወደ ሳሙኤል ሄደ፣ ሳኦል ያደረገበትን ሁሉ ነገረው። ከዚያም እርሱና ሳሙኤል ወደ ነዋት ሄደው ተቀመጡ። ለሳኦልም፣ “እነሆ፤ ዳዊት በአርማቴም በምትገኘው በነዋት ተቀምጧል” ብለው ነገሩት። ስለዚህ ዳዊትን እንዲይዙ ሰዎችን ላከ፤ ይሁን እንጂ፣ የነቢያትም ጉባኤ በሳሙኤል መሪነት ትንቢት ሲናገሩ ባዩ ጊዜ፣ የእግዚአብሔር መንፈስ በሳኦል ሰዎች ላይ ወረደ፤ እነርሱም እንደዚሁ ትንቢት ተናገሩ። ሳኦልም ይህ በተነገረው ጊዜ ሌሎች ሰዎች ላከ፤ እነርሱም ትንቢት ተናገሩ፤ ሳኦል ለሦስተኛ ጊዜ ሰዎች ላከ፣ እነርሱም ደግሞ ትንቢት ተናገሩ። በመጨረሻም፣ እርሱ ራሱ ወደ አርማቴም ሄደ፤ ከዚያም በሤኩ ወዳለው ትልቅ የውሃ ማጠራቀሚያ ጕድጓድ እንደ ደረሰ፣ “ሳሙኤልና ዳዊት የት ናቸው?” ሲል ጠየቀ። አንድ ሰውም “በአርማቴም በምትገኘው በነዋት ዘራማ ናቸው” ብሎ ነገረው። ስለዚህ ሳኦል በአርማቴም ወደምትገኘው ወደ ነዋት ዘራማ ሄደ፤ የእግዚአብሔር መንፈስ በእርሱም ላይ ደግሞ ወረደ፤ ወደ ነዋት እስኪደርስ ድረስም ትንቢት እየተናገረ ተጓዘ። እርሱም ልብሱን አውልቆ፣ በሳሙኤልም ፊት ደግሞ ትንቢት ተናገረ፤ በዚህ ሁኔታም ቀኑንና ሌሊቱን በሙሉ ራቍቱን ተጋደመ። ሕዝቡ፣ “ሳኦልም ደግሞ ከነቢያት እንደ አንዱ ሆኖ ተቈጠረ?” ያለው በዚህ ምክንያት ነው።
1 ሳሙኤል 19:1-24 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ሳኦልም ለልጁ ለዮናታንና ለባሪያዎቹ ሁሉ ዳዊትን ይገድሉ ዘንድ ነገራቸው። የሳኦል ልጅ ዮናታን ግን ዳዊትን እጅግ ይወድድ ነበር። ዮናታንም፦ አባቴ ሳኦል ሊገድልህ ፈልጎአል፥ አሁን እንግዲህ ለነገው ተጠንቅቀህ ተሸሸግ፥ በስውርም ተቀመጥ፥ እኔም እወጣለሁ አንተም ባለህበት እርሻ በአባቴ አጠገብ እቆማለሁ፥ ስለ አንተም ከአባቴ ጋር እነጋገራለሁ፥ የሆነውንም አይቼ እነግርሃለሁ ብሎ ለዳዊት ነገረው። ዮናታንም ለአባቱ ለሳኦል፦ እርሱ አልበደለህምና፥ ሥራውም ለአንተ እጅግ መልካም ሆኖአልና ንጉሡ ባሪያውን ዳዊትን አይበድለው፥ ነፍሱንም በእጁ ጥሎ ፍልስጥኤማዊውን ገደለ፥ እግዚአብሔርም ለእስራኤል ሁሉ ታላቅ መድኃኒት አደረገ፥ አንተም አይተህ ደስ አለህ፥ በከንቱ ዳዊትን በመግደልህ ስለ ምን በንጹሕ ደም ላይ ትበድላለህ? ብሎ ስለ ዳዊት መልካም ተናገረ። ሳኦልም የዮናታንን ቃል ሰማ፥ ሳኦልም፦ ሕያው እግዚአብሔርን! ዳዊት አይገደልም ብሎ ማለ። ዮናታንም ዳዊትን ጠርቶ ይህን ነገር ሁሉ ነገረው፥ ዮናታንም ዳዊትን ወደ ሳኦል አመጣው፥ እንደ ቀድሞውም በፊቱ ነበረ። ዳግሞም ጦርነት ሆነ፥ ዳዊትም ወጥቶ ከፍልስጥኤማውያን ጋር ተዋጋ፥ ታላቅ ግዳይም ገደላቸው፥ ከፊቱም ሸሹ። ሳኦልም ጦሩን ይዞ በቤቱ ተቀምጦ ሳለ ክፉ መንፈስ ከእግዚአብሔር ዘንድ ያዘው። ዳዊትም በእጁ በገና ይመታ ነበር። ሳኦልም ዳዊትን ከግንብ ጋር ያጣብቀው ዘንድ ጦሩን ወረወረ፥ ዳዊትም ከሳኦል ፊት ዘወር አለ፥ ጦሩም በግንቡ ውስጥ ተተከለ፥ በዚያም ሌሊት ዳዊት ሸሽቶ አመለጠ። ሳኦልም ዳዊትን ጠብቀው በነጋው እንዲገድሉት መልእክተኞቹን ወደ ዳዊት ቤት ላከ፥ ሚስቱም ሜልኮል፦ በዚህች ሌሊት ነፍስህን ካላዳንህ ነገ ትገደላለህ ብላ ነገረችው። ሜልኮልም ዳዊትን በመስኮት አወረደችው፥ ሄደም፥ ሸሽቶም አመለጠ። ሜልኮልም ተራፊምን ወስዳ በአልጋ ላይ አኖረችው፥ በራስጌውም ጉንጉን የፍየል ጠጉር አደረገች፥ በልብስም ከደነችው። ሳኦልም ዳዊትን እንዲያመጡት መልእክተኞችን ላከ፥ እርስዋም፦ ታምሞአል አለቻቸው። ሳኦልም፦ እገድለው ዘንድ ዳዊትን ከነ አልጋው አምጡልኝ ብሎ መልእክተኞቹን ወደ ዳዊት ሰደደ። መልእክተኞቹም በገቡ ጊዜ እነሆ፥ ተራፊሙን በአልጋው ላይ አገኙ፥ በራስጌው ጕንጕን የፍየል ጠጉር ነበረ። ሳኦልም ሜልኮልን፦ ስለ ምን እንዲህ አድርገሽ አታለልሽኝ? ጠላቴን አስኮበለልሽው አላት። ሜልኮልም ለሳኦል፦ እርሱ፦ አውጥተሽ ስደጂኝ፥ አለዚያም እገድልሻለሁ አለኝ ብላ መለሰችለት። ዳዊትም ሸሽቶ አመለጠ፥ ወደ አርማቴምም ወደ ሳሙኤል መጣ፥ ሳኦልም ያደረገበትን ሁሉ ነገረው፥ እርሱና ሳሙኤልም ሄዱ በነዋትዘራማም ተቀመጡ። ሳኦልም፦ ዳዊት፥ እነሆ፥ በአርማቴም አገር በነዋትዘራማ ተቀምጦአል የሚል ወሬ ሰማ። ሳኦልም ዳዊትን ያመጡት ዘንድ መልእክተኞችን ሰደደ፥ የነቢያት ጉባኤ ትንቢት ሲናገሩ፥ ሳሙኤልም አለቃቸው ሆኖ ሲቆም ባዩ ጊዜ የእግዚአብሔር መንፈስ በሳኦል መልእክተኞች ላይ ወረደ፥ እነርሱም ትንቢት ይናገሩ ጀምር። ሳኦልም ያንን በሰማ ጊዜ ሌሎች መልእክተኞችን ሰደደ፥ እነርሱም ደግሞ ትንቢት ተናገሩ። ሳኦልም እንደ ገና ሦስተኛ ጊዜ መልእክተኞችን ሰደደ፥ እነርሱም ደግሞ ትንቢት ተናገሩ። የሳኦልም ቁጣ ነደደ፥ እርሱም ደግሞ ወደ አርማቴም መጣ፥ በሤኩም ወዳለው ወደ ታላቁ የውኃ ጕድጓድ ደረሰ። ሳሙኤልና ዳዊት የት ናቸው? ብሎ ጠየቀ፥ አንድ ሰውም፦ እነሆ፥ በአርማቴም አገር በነዋትዘራማ ናቸው አለው። ወደ አርማቴምም አገር ወደ ነዋትዘራማ ሄደ፥ የእግዚአብሔርም መንፈስ በእርሱ ደግሞ ወረደ፥ እርሱም ሄደ፥ ወደ አርማቴምም አገር ወደ ነዋትዘራማ እስኪመጣ ድረስ ትንቢት ይናገር ነበር። ልብሱንም አወለቀ፥ በሳሙኤልም ፊት ትንቢት ተናገረ፥ ራቁቱንም ወድቆ በዚያ ቀን ሁሉ በዚያም ሌሊት ሁሉ ተጋደመ። ስለዚህ፦ ሳኦል ደግሞ ከነቢያት መካከል ነውን? ይባባሉ ነበር።
1 ሳሙኤል 19:1-24 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ሳኦል ዳዊትን ሊገድለው ማቀዱን ለልጁ ለዮናታንና ባለሟሎቹ ለሆኑት ባለሥልጣኖች ሁሉ ነገረ፤ ነገር ግን ዮናታን ዳዊትን እጅግ ይወደው ነበር። በእርሱ ላይ የታቀደውን ነገር ሁሉ እንዲህ ሲል ነገረው፥ “አባቴ ሊገድልህ ዐቅዶአል፤ ስለዚህ እባክህ በነገው ማለዳ ይህ እንዳይደርስብህ ተጠንቀቅ፤ ስውር በሆነ ቦታ ተሸሽገህ ቈይ፤ አንተም ተደብቀህ ባለህበት እርሻ ወደ አባቴ ቀርቤ ስለ አንተ አነጋግረዋለሁ፤ የማገኘውንም መልስ እንድታውቀው አደርጋለሁ።” ዮናታንም ዳዊትን በማመስገን ለሳኦል እንዲህ ሲል ነገረው፤ “በአገልጋይህ በዳዊት ላይ ክፉ ነገር አታድርግ፤ እርሱ ምንም ነገር አልበደለህም፤ ይልቅስ እርሱ የሚያደርገው ነገር ሁሉ ታላቅ ጥቅም በማስገኘት ረድቶሃል፤ እርሱ ለሕይወቱ ሳይሳሳ በመጋፈጥ ጎልያድን ገደለ፤ እግዚአብሔርም ለእስራኤል ታላቅ ድልን አቀዳጀ፤ አንተም ይህን ባየህ ጊዜ ደስ ብሎህ ነበር፤ ታዲያ አሁን አንተ በንጹሕ ሰው ላይ በደል ለመሥራት ስለምን ታስባለህ? ምክንያት በሌለውስ ነገር ዳዊትን ለመግደል ስለምን ፈለግኽ?” ሳኦልም ዮናታን የተናገረውን ቃል በመስማት ዳዊትን እንደማይገድለው የእግዚአብሔርን ስም ጠርቶ በመማል አረጋገጠ፤ ስለዚህ ዮናታን ዳዊትን ጠርቶ ይህን ሁሉ ከነገረው በኋላ ወደ ሳኦል አቀረበው፤ ዳዊትም ከዚያ በፊት ያደርገው እንደ ነበር በንጉሡ ፊት እንደ ቀድሞው ማገልገሉን ቀጠለ። ከፍልስጥኤማውያን ጋር ይደረግ የነበረውም ጦርነት እንደገና አገረሸ፤ ሆኖም ዳዊት በእነርሱ ላይ ብርቱ አደጋ በመጣል ድል ስለ መታቸው ሸሽተው ሄዱ፤ አንድ ቀን ከእግዚአብሔር የተላከ ክፉ መንፈስ ሳኦልን ተቈራኘው፤ እርሱም ጦሩን በእጁ እንደ ያዘ በቤቱ ውስጥ ተቀምጦ ነበር፤ ዳዊትም በዚያው በገናውን ይደረድር ነበር፤ ሳኦል ዳዊትን ወግቶ ከግድግዳው ጋር ሊያጣብቀው በማሰብ ጦሩን ወረወረበት፤ ዳዊት ግን ዞር በማለቱ ጦሩ በግድግዳ ላይ ተተከለ፤ ዳዊትም ከዚያ ሸሽቶ አመለጠ። በዚያኑ ምሽት ሳኦል የዳዊትን ቤት ከበው ማለዳ እንዲገድሉት ሰዎችን ላከ፤ የዳዊት ሚስት ሜልኮል “ዛሬ ማታ ነፍስህን ካላዳንህ በቀር ነገ ጧት ትገደላለህ” ስትል አስጠነቀቀችው፤ እርስዋም በመስኮት አወረደችው፤ ሸሽቶም አመለጠ፤ ከዚህ በኋላ የቤተሰቡን ጣዖት ወስዳ በአልጋ ላይ አጋደመችው፤ ከፍየል ጠጒር የተሠራ ትራስም በራስጌው አኑራ በልብስ ሸፈነችው። የሳኦል ወታደሮች ዳዊትን ለመያዝ በመጡ ጊዜ ሜልኮል እርሱ ታሞ ተኝቶአል አለቻቸው። ሳኦል ግን “እኔው ራሴ እገድለው ዘንድ ከነአልጋው ተሸክማችሁ ወደዚህ አምጡት” ብሎ መልሶ ላካቸው። ወደ ቤትም ውስጥ ዘልቀው በገቡ ጊዜ ጣዖቱንና በራስጌው ያለውን ከፍየል ጠጒር የተሠራውን ትራስ ብቻ አገኙ። ሳኦልም ሜልኮልን “ጠላቴ የሚያመልጥበትን ተንኰል በመሥራት ስለምን እንዲህ አታለልሽኝ?” ሲል ጠየቃት። እርስዋም “እኔ ምን ላድርግ፥ ‘ማምለጥ እንድችል ካልረዳሽኝ እገድልሻለሁ’ አለኝ” ስትል መለሰችለት። ዳዊትም አምልጦ ሳሙኤል ወደነበረበት ወደ ራማ መጣ፤ ሳኦል ያደረገበትንም በደል ሁሉ ነገረው፤ ከዚህም በኋላ ሳሙኤልና ዳዊት በራማ ወደምትገኘው ወደ ናዮት ሄደው በዚያ ተቀመጡ፤ ዳዊት በራማ በምትገኘው በናዮት መኖሩን ሳኦል ሰማ፤ ስለዚህም ሳኦል ዳዊትን የሚይዙ ሰዎች ላከ፤ እነርሱም እዚያ በደረሱ ጊዜ፥ በሳሙኤል መሪነት የተሰበሰቡ ነቢያት በጉባኤ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ትንቢት ሲናገሩ አዩ፤ በዚህን ጊዜ የእግዚአብሔር መንፈስ በሳኦል ሰዎች ላይ ስለ ወረደ እነርሱም ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ትንቢት ተናገሩ። ሳኦል ይህን በሰማ ጊዜ ሌሎች መልእክተኞችን ላከ፤ እነርሱም እንደዚያው ትንቢት መናገር ቀጠሉ፤ ሳኦልም ለሦስተኛ ጊዜ ሌሎች መልእክተኞችን ቢልክ ያው ነገር በእነርሱም ላይ ተደገመ፤ ከዚህ በኋላ እርሱ ራሱ ወደ ራማ ለመሄድ ተነሣ፤ እዚያም ሴኩ በሚባለው ስፍራ ወደሚገኘው ወደ አንድ ታላቅ የውሃ ጒድጓድ በደረሰ ጊዜ “ሳሙኤልና ዳዊት የሚገኙት የት ነው?” ብሎ ቢጠይቅ፥ በናዮት መኖራቸው ተነገረው። ወደዚያም በማምራት ላይ ሳለ የእግዚአብሔር መንፈስ በእርሱም ላይ ወረደበት፤ እስከ ናዮት በሚያደርሰው መንገድ ሁሉ ትንቢት ይናገር ነበር፤ ወደ ሳሙኤልም ፊት ሲቀርብ ልብሱን አውልቆ ትንቢት እየተናገረ፤ ቀኑንም ሌሊቱንም ሁሉ ራቁቱን በዚያው ተጋድሞ ዋለ፤ “ሳኦልም ከነቢያት እንደ አንዱ ሆኖ ተቈጠርን?” የሚለው የምሳሌ አነጋገር የመነጨው ከዚህ የተነሣ ነው።
1 ሳሙኤል 19:1-24 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ሳኦል ዳዊትን እንዲገድሉት ለልጁ ለዮናታንና ለባለሟሎቹ ነገራቸው፤ ዮናታን ግን ዳዊትን እጅግ ይወደው ነበር። እንዲህ ሲልም አስጠነቀቀው፤ “አባቴ ሳኦል ሊገድልህ አጋጣሚ እየፈልገ ነው፤ ነገ ጠዋት ተጠንቀቅ፤ ወደ አንድ መደበቂያ ቦታም ሂድ፤ በዚያም ቆይ። እኔም እወጣና አንተ ባለህበት ከአባቴ እርሻ አጠገብ እቆማለሁ፤ ስለ አንተም አነጋግረዋለሁ፤ የተረዳሁትንም እነግርሃለሁ።” ዮናታን ለአባቱ ለሳኦል፥ ስለ ዳዊት እንዲህ ሲል መልካም ነገር ተናገረ፥ “ንጉሥ በአገልጋዩ በዳዊት ላይ ክፉ ነገር አያድርግ፤ እርሱ አልበደለህም፤ ያደረገውም ነገር በእጅጉ ጠቅሞሃል። ዳዊት ፍልስጥኤማዊውን የገደለው በገዛ ሕይወቱ ቆርጦ ነው። ጌታ ለመላው እስራኤል ታላቅ ድልን አቀዳጀ፤ አንተም አይተህ ደስ አለህ። ታዲያ እርሱን በከንቱ በመግደል ዳዊትን በመሰለ ንጹሕ ሰው ላይ ለምን በደል ትፈጽማለህ?” ሳኦልም ዮናታንን ካዳመጠው በኋላ፥ “በሕያው ጌታ እምላለሁ! ዳዊት አይገደልም” አለ። ስለዚህም ዮናታን ዳዊትን ጠርቶ የተባባሉትን ሁሉ ነገረው፤ ወደ ሳኦልም አመጣው፤ ዳዊትም እንደ ቀድሞው በፊቱ ቆመ። እንደገና ሌላ ጦርነት ተነሣ፤ ዳዊትም ወጥቶ ፍልስጥኤማውያንን ወጋቸው፤ ከፊቱም እስኪሸሹ ድረስ እጅግ መታቸው። ነገር ግን ሳኦል ጦሩን ይዞ በቤቱ ተቀምጦ ሳለ፥ ከጌታ ዘንድ ክፉ መንፈስ መጣበት፤ ያንጊዜ ዳዊት በገናውን ይደረድር ነበር። ሳኦልም ከግድግዳው ጋር ሊያጣብቀው ጦሩን ወረወረበት፤ ነገር ግን ዳዊት ዘወር በማለቱ ሳኦል የወረወረው ጦር እግድግዳው ላይ ተሰካ። በዚያች ሌሊት ዳዊት ሸሽቶ አመለጠ። ሳኦልም የዳዊትን ቤት ከበው በማለዳ እንዲገድሉት ሰዎችን ላከ። የዳዊት ሚስት ሜልኮል ግን፥ “ሕይወትህን ለማትረፍ በዚህች ሌሊት ካልሸሸህ፥ በነገው ቀን ትገደላለህ” ብላ አስጠነቀቀችው። ሜልኮልም ዳዊትን በመስኮት አሾልካ አወረደችው፥ እርሱም ሸሽቶ አመለጠ። ከዚያም ሜልኮል የጣዖት ምስል ወስዳ በአልጋው ላይ አጋደመችው፤ በራስጌውም የፍየል ጠጉር አኖረች፤ በልብስም ሸፈነችው። ሳኦል ዳዊትን እንዲይዙት ሰዎች በላከ ጊዜ ሜልኮል፥ “እርሱ ታሟል” አለቻቸው። ሳኦልም ሰዎቹ ዳዊትን እንዲያዩት መልሶ ላካቸው፤ እርሱም፥ “እገድለው ዘንድ ከነአልጋው አምጡልኝ” አላቸው። የተላኩትም ሰዎች በገቡ ጊዜ፥ እነሆ፥ የጣዖት ምስሉ በአልጋው ላይ ተጋድሞ በራስጌውም የፍየል ጠጉር ተደርጎለት ነበር። ሳኦልም ሜልኮልን፥ “እንዲህ አድርገሽ ለምን አታለልሽኝ? ጠላቴ እንዲያመልጥ የሰደድሽው ለምንድን ነው?” ሲል ጠየቃት። ሜልኮልም፥ “ ‘እንዳመልጥ እርጂኝ፤ ያለዚያ እገድልሻለሁ’ አለኝ” ብላ መለሰችለት። ዳዊት ሸሽቶ ካመለጠ በኋላ፥ ወደ ራማ ወደ ሳሙኤል ሄደ፥ ሳኦል ያደረገበትን ሁሉ ነገረው። ከዚያም እርሱና ሳሙኤል ወደ ናዮት ሄደው በዚያ ተቀመጡ። ለሳኦልም፥ “እነሆ፤ ዳዊት ራማ በምትገኘው በናዮት ተቀምጧል” ብለው ነገሩት። ስለዚህ ዳዊትን እንዲይዙ ሰዎችን ላከ፤ እነርሱም የነቢያትም ጉባኤ በሳሙኤል መሪነት ትንቢት ሲናገሩ ባዩ ጊዜ፥ የእግዚአብሔር መንፈስ በሳኦል ሰዎች ላይ ወረደ፤ እነርሱም እንደዚሁ ትንቢት ተናገሩ። ሳኦልም ይህ በተነገረው ጊዜ ሌሎች ሰዎች ላከ፤ እነርሱም ትንቢት ተናገሩ፤ ሳኦል ለሦስተኛ ጊዜ ሰዎች ላከ፥ እነርሱም ደግሞ ትንቢት ተናገሩ። በመጨረሻም፥ እርሱ ራሱ ወደ ራማ ሄደ፤ ከዚያም በሴኩ ወዳለው ትልቅ የውሃ ማጠራቀሚያ ጉድጓድ እንደ ደረሰ፥ “ሳሙኤልና ዳዊት የት ናቸው?” ሲል ጠየቀ። አንድ ሰውም “በራማ በምትገኘው የራማዋ ናዮት ናቸው” ብሎ ነገረው። ስለዚህ ሳኦል በራማ ወደምትገኘው ወደ የራማዋ ናዮት ሄደ፤ ሲሄድ ሳለም የእግዚአብሔር መንፈስ በእርሱም ላይ ደግሞ ወረደ፤ ወደ ናዮት እስኪደርስ ድረስም ትንቢት እየተናገረ ተጓዘ። እርሱም ልብሱን አውልቆ፥ በሳሙኤልም ፊት ደግሞ ትንቢት ተናገረ፤ በዚህ ሁኔታም ቀኑንና ሌሊቱን በሙሉ ራቁቱን ተጋደመ። ሕዝቡ፥ “ሳኦልም ደግሞ ከነቢያት እንደ አንዱ ሆኖ ተቆጠረ?” ካለው የተነሣ ነው።