ኦሪት ዘፍጥረት 7

7
1ጌታም ኖኅን እንዲህ አለው፦ “በዚህ ዘመን ካለው ትውልድ መካከል ጻድቅ አንተ ሆነህ አይቼሃለሁና፥ አንተ ቤተሰቦችህን ሁሉ ይዘህ ወደ መርከብ ግባ። 2ከንጹሕ እንስሳ ሁሉ ሰባት ሰባት ተባዕትና እንስት፥ ንጹሕ ካልሆነ እንስሳም ሁለት ሁለት ተባዕትና እንስት፤ 3ከሰማይ ወፍ ደግሞ ሰባት ሰባት ተባዕትና እንስት እያደረግህ በምድር ላይ ለዘር ይቀር ዘንድ ለአንተ ትወስዳለህ። 4የፈጠርሁትንም ፍጥረት ሁሉ ከምድር ላይ ለማጥፋት ከሰባት ቀን በኋላ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት በምድር ላይ ዝናብ አዘንባለሁ።” 5ኖኅም እግዚአብሔር እንዳዘዘው ሁሉ አደረገ። 6የጥፋት ውኃ በምድር ላይ በመጣ ጊዜ የኖኅ ዕድሜ ስድስት መቶ ዓመት ነበረ።
7 # ማቴ. 24፥38፤39፤ ሉቃ. 17፥27። ኖኅ፥ ሚስቱ፥ ልጆቹና ሚስቶቻቸው ከጥፋት ውሃ ለማምለጥ ወደ መርከቡ ገቡ። 8ከንጹሕ እንስሳ ንጹሕም ካልሆነው እንስሳ፥ ከወፎችና በምድር ላይ ከሚንቀሳቀሰውም ሁሉ፥ 9ጥንድ ተባዕትና እንስት እየሆኑ፥ እግዚአብሔር ኖኅን ባዘዘውም መሠረት ወደ ኖኅ ወደ መርከቡ ገቡ። 10ከሰባት ቀንም በኋላ የጥፋት ውኃ በምድር ላይ መጣ። 11#2ጴጥ. 3፥6።ኖኅ ስድስት መቶ ዓመት በሆነው፥ በሁለተኛው ወር፥ ከወሩም በዓሥራ ሰባተኛው ቀን ላይ፥ ከምድር በታች ያለው የታላቁ ጥልቅ መፍለቂያዎች ሁሉ በድንገት ተነደሉ፥ የሰማያትም መስኮቶች ተከፈቱ፥ 12ዝናቡም አርባ ቀንና አርባ ሌሊት በምድር ላይ ዘነበ።
13በዚያውም ቀን ኖኅ፥ የኖኅ ልጆችም ሴም፥ ካም፥ ያፌትና የኖኅ ሚስት፥ ሦስቱም የልጆቹ ሚስቶች ከርሱ ጋር ወደ መርከብ ገቡ። 14ከእነርሱ ጋር፥ ከአራዊት፥ ከእንስሶች፥ በደረታቸው እየተሳቡ ከሚንቀሳቀሱ ፍጥረቶችና በሰማይ ከሚበርሩ ወፎች ከእያንዳንዱ ዓይነት አብረዋቸው ገቡ። 15በዚህ ዓይነት እስትንፋስ ካላቸው ፍጥረቶች ከእያንዳንዱ ዓይነት ሁለት ሁለት እየሆኑ ከኖኅ ጋር ወደ መርከቡ ገቡ፤ 16ፍጥረት ሁሉ ወንድና ሴት ሆነው ወደ መርከቡ የገቡት እግዚአብሔር እንዳዘዘው ገቡ፤ ጌታም በስተ ኋላው ዘጋበት።
የጥፋት ውሃ
17የጥፋትም ውኃ በምድር ላይ አርባ ቀን አላቋረጠም፥ ውኃውም በዛ፥ መርከቢቱንም አነሣ፥ ከምድርም በላይ ከፍ አለች። 18ውሃ በምድር ላይ እያደገና እየበረታ በሄደ መጠን መርከቡ በውሃው ላይ መንሳፈፍ ጀመረ። 19ውሃውም ከሰማይ በታች ያሉትን ታላላቅ ተራራዎችን እንኳ እስከሚሸፍን ድረስ ጥልቅ ሆነ። 20ውሃው ከተራሮች ጫፍ በላይ ሰባት ሜትር ያኽል ከፍ አለ። 21ወፎችና እንስሶች፥ አራዊት፥ ሰዎችም ሁሉ ሞቱ። በምድር ላይ ያሉት ተንቀሳቃሽ ፍጥረቶች ሁሉ ጠፉ። 22በምድር ላይ የሚኖር የሕይወት እስትንፋስ ያለው ሁሉ ሞተ። 23እግዚአብሔር በምድር ላይ ያለውን ሕያው ፍጥረት ሁሉ፥ ሰዎችንም፥ እንስሶችንም፥ ወፎችንም፥ በደረታቸው እየተሳቡ የሚንቀሳቀሱ ፍጥረቶች ሳይቀሩ ሁሉንም አጠፋ። ከሞት የተረፉት ኖኅና ከእርሱ ጋር በመርከቡ ውስጥ የነበሩት ብቻ ነበሩ። 24ውሃውም እስከ መቶ ኀምሳ ቀን አልጐደለም ነበር።

Kleurmerk

Deel

Kopieer

None

Wil jy jou kleurmerke oor al jou toestelle gestoor hê? Teken in of teken aan

Video vir ኦሪት ዘፍጥረት 7