ኦሪት ዘፍጥረት 6

6
የእግዚአብሔር ልጆች እና ሴቶች
1 # ኢዮብ 1፥6፤ 2፥1። የሰው ዘር በምድር ላይ እየበዛ በሄደ ጊዜ ሴቶች ልጆች ተወለዱ፥ 2የእግዚአብሔር ልጆችም የሰውን ሴቶች ልጆች መልካሞች እንደ ሆኑ አዩ፥ ከመረጡአቸውም ሁሉ ሚስቶችን ለራሳቸው ወሰዱ። 3ጌታም፦ “መንፈሴ በሰው ላይ ለዘለዓለም አይኖርም፥ እርሱ ሥጋ ነውና፥ እድሜውም መቶ ሃያ ዓመት ይሆናል” አለ። 4#ዘኍ. 13፥33፤ ሲራ. 16፥7፤ ባሮክ 3፥26።በዚያን ዘመን ኔፊሊም በምድር ላይ ነበሩ፥ እና ከዚያም በኋላ የእግዚአብሔር ልጆች የሰውን ሴቶች ልጆች ባገቡ ጊዜ ልጆችን ወለዱላቸው፥ እነርሱም በዱሮ ዘመን፥ ስማቸው የታወቀ፥ ኃያላን ሆኑ።
ለ. የጥፋት ውሃ
የሰዎች ክፋት
5 # ማቴ. 24፥37፤ ሉቃ. 17፥26፤ 1ጴጥ. 3፥20። ጌታም የሰው ክፋት በምድር ላይ እንደ በዛ፥ የልቡ አሳብ ምኞትም ሁልጊዜ ፈጽሞ ክፉ እንደሆነ አየ። 6ሰውን በምድር ላይ በመፍጠሩም ጌታ ተጸጸተ፥ በልቡም አዘነ። 7በዚህ ምክንያት ጌታ፥ “ከምድር ላይ የፈጠርኩትን ሰው ከምድር ላይ አጠፋለሁ፥ ሰው እና አራዊትን፥ በደረታቸው እየተሳቡ የሚንቀሳቀሱ ፍጥረቶችን እና የሰማይ አእዋፍንም፥ ስለ ፈጠርኳቸው ተጸጽቼአለሁና” አለ። 8ይሁን እንጂ ኖኅ ግን በእግዚአብሔር ፊት ሞገስን አገኘ።
9 # ሲራ. 44፥17፤18፤ 2ጴጥ. 2፥5። የኖኅ ትውልድ እንደሚከተለው ነው። ኖኅም ጻድቅ፥ በትውልዱም በደል ያልተገኘበት ሰው ነበረ፥ ኖኅም እግዚአብሔርን ደስ አሰኘው። 10ሴም፥ ካምና ያፌት የሚባሉትን ሦስት ወንዶች ልጆች ወለደ። 11በዚያን ጊዜ ምድር በእግዚአብሔር ፊት የተበላሸች ነበረች፥ ምድርም ግፍን ተሞላች። 12እግዚአብሔርም ምድርን አየ፥ እነሆም፥ ሥጋ ለባሽ ሁሉ በምድር ላይ መንገዳቸውን አበላሽተው ነበርና፥ ምድር የተበላሸች ነበረች።
ለጥፋት ውሃ ዝግጅት
13እግዚእብሔርም ኖኅን አለው፦ “የሥጋ ሁሉ ፍጻሜ በፊቴ ደርሶአል፥ ከእነርሱ የተነሣ ምድር በግፍ ተሞልታለችና፥ እኔም እነሆ ከምድር ጋር አጠፋቸዋለሁ። 14ለአንተ ከጎፈር እንጨት መርከብን ሥራ፥ በመርከቢቱም ክፍሎችን አድርግ፥ በውስጥም፥ በውጭም በቅጥራን ለቅልቃት። 15የመርከቢቱ ርዝመት ሦስት መቶ ክንድ፥ ወርድዋ አምሳ ክንድ፥ ከፍታዋ ሠላሳ ክንድ አድርግ፤ 16ለመርከቢቱም ጣራን አብጅለት፤ ከቁመትዋም አርባ አራት ሳንቲ ሜትር ትተህ ጨርሳት፥ መርከቡ ባለ ሦስት ፎቅ እንዲሆን አድርግ፤ በጎኑም በኩል በር አድርግለት። 17እነሆ፥ እኔ ከሰማይ በታች የሕይወት እስትንፋስ ያለውን ሥጋ ሁሉ ለማጥፋት፥ በምድር ላይ የጥፋት ውኃን አመጣለሁ፥ በምድር ያለ ሁሉ ይጠፋል። 18ከአንተ ጋር ግን ቃል ኪዳን እገባለሁ፤ አንተና ሚስትህ፥ ልጆችህና የልጆችህ ሚስቶች ይዘህ ወደ መርከቡ ትገባለህ። 19ከአንተ ጋር በሕይወት ይኖሩ ዘንድ ሥጋ ካለው ከሕያው ሁሉ ሁለት ሁለት እያደረግህ ወደ መርከብ ታስገባለህ፥ ተባዕትና እንስት ይሁኑ፤ 20ከወፍ እንደ ወገኑ፥ ከእንስሳም እንደ ወገኑ፥ ከምድር ተንቀሳቃሽም ሁሉ እንደ ወገኑ በሕይወት ይኖሩ ዘንድ ሁለት ሁለት እየሆኑ ወደ አንተ ይግቡ። 21እንዲሁም ለአንተና ለእነዚህ ፍጥረቶች ሁሉ የሚበቃ ልዩ ልዩ ዓይነት ምግብ በመርከቡ ውስጥ አከማች።” 22#ዕብ. 11፥7።ኖኅም እንዲሁ አደረገ፥ እግዚአብሔር ያዘዘውን ሁሉ አደረገ።

Kleurmerk

Deel

Kopieer

None

Wil jy jou kleurmerke oor al jou toestelle gestoor hê? Teken in of teken aan

Video vir ኦሪት ዘፍጥረት 6