ኦሪት ዘፍጥረት 7
7
የጥፋት ውሃ
1እግዚአብሔር ኖኅን እንዲህ አለው፤ “በዚህ ዘመን ካለው ትውልድ መካከል ጻድቅ አንተ ብቻ ሆነህ ስላገኘሁህ፥ ከመላው ቤተሰብህ ጋር ወደ መርከቡ ግባ። #7፥1 ጻድቅ፦ እውነተኛ፥ ቀጥተኛ፥ የእግዚአብሔርን ፈቃድ ፈጻሚ 2ንጹሕ ከሆኑት ወንዶችና ሴቶች እንስሶች ሁሉ ሰባት ወንድ፥ ሰባት ሴት ከአንተ ጋር ወደ መርከቡ አስገባ፤ ንጹሕ ካልሆኑት ወንዶችና ሴቶች እንስሶች ሁሉ ግን፥ አንድ ወንድ አንድ ሴት አስገባ። #7፥2 ንጹሕ የሆነና ንጹሕ ያልሆነ፦ ዘሌ. ም. 11 እና ዘዳ. ም. 14፥3-21 ተመልከት። 3ከያንዳንዱ ዐይነት ወፍ ወንድና ሴት ሰባት ወንድ ሰባት ሴት አስገባ፤ ይህንንም የምታደርገው እያንዳንዱ ዐይነት እንስሳና ወፍ በሕይወት እንዲኖርና በምድር ላይ ለዘር እንዲተርፍ ነው። 4የፈጠርኩትን ሕያው ፍጡር ሁሉ ከምድር ገጽ ላይ ለማጥፋት ከሰባት ቀን በኋላ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ሙሉ ዝናብ አዘንባለሁ።” 5ኖኅም እግዚአብሔር ያዘዘውን ሁሉ አደረገ።
6የጥፋት ውሃ በምድር ላይ በመጣ ጊዜ የኖኅ ዕድሜ 600 ዓመት ነበር። 7ኖኅ፥ ሚስቱ፥ ልጆቹና ሚስቶቻቸው ከጥፋት ውሃ ለማምለጥ ወደ መርከቡ ገቡ። #ማቴ. 24፥38-39፤ ሉቃ. 17፥27። 8ንጹሕ ከሆኑትና ካልሆኑት ከያንዳንዱ ዐይነት እንስሶች ወፎች፥ በደረታቸው እየተሳቡ ከሚንቀሳቀሱ ፍጥረቶች ሁሉ 9ጥንድ ወንድና ሴት እየሆኑ፥ እግዚአብሔር ኖኅን ባዘዘውም መሠረት ወደ ኖኅ ወደ መርከቡ ገቡ። 10ከሰባትም ቀን በኋላ የጥፋት ውሃ በምድር ላይ መጣ።
11ኖኅ 600 ዓመት በሆነው ጊዜ፥ በሁለተኛው ወር በዐሥራ ሰባተኛው ቀን ላይ ከምድር በታች ያለው የታላቁ ውሃ ምንጮች ሁሉ በድንገት ተነደሉ፤ በሰማይ ያሉት የውሃ መስኮቶች ሁሉ ተከፈቱ። #2ጴጥ. 3፥6። 12ዝናብም አርባ ቀንና አርባ ሌሊት በምድር ላይ ዘነበ። 13ዝናቡ መዝነብ በጀመረበት ቀን፥ ኖኅና ሚስቱ ከልጆቻቸው ከሴም፥ ከካም፥ ከያፌትና ከሦስቱም ልጆቻቸው ሚስቶች ጋር ወደ መርከቡ ገቡ። 14ከአራዊት፥ ከእንስሶች፥ በደረታቸው እየተሳቡ ከሚንቀሳቀሱ ፍጥረቶችና በሰማይ ከሚበርሩ ወፎች ከእያንዳንዱ ዐይነት አብረዋቸው ገቡ። 15በዚህ ዐይነት እስትንፋስ ካላቸው ፍጥረቶች ከእያንዳንዱ ዐይነት ሁለት ሁለት እየሆኑ ከኖኅ ጋር ወደ መርከቡ ገቡ፤ 16ፍጥረት ሁሉ ወንድና ሴት ሆነው ወደ መርከቡ የገቡት እግዚአብሔር ባዘዘው መሠረት ነው፤ ከዚህ ቀጥሎ እግዚአብሔር ከኖኅ በስተኋላ የመርከቡን በር ዘጋ።
17የጥፋት ውሃ አርባ ቀን ድረስ በመዝነብ እየበረታ ሄደ፤ የውሃውም ጥልቀት እየጨመረ ስለ ሄደ መርከቡን ከምድር በላይ ከፍ አደረገው፤ 18ውሃ በምድር ላይ እያደገና እየበረታ በሄደ መጠን መርከቡ በውሃው ላይ መንሳፈፍ ጀመረ። 19ውሃውም ከሰማይ በታች ያሉትን ታላላቅ ተራራዎችን እንኳ እስከሚሸፍን ድረስ ጥልቅ ሆነ። 20ውሃው ከተራሮች ጫፍ በላይ ሰባት ሜትር ያኽል ከፍ አለ። 21ወፎችና እንስሶች፥ አራዊት፥ ሰዎችም ሁሉ ሳይቀሩ ሞቱ። በምድር ላይ ያሉት ተንቀሳቃሽ ፍጥረቶች ሁሉ ጠፉ። 22በምድር ላይ የሚኖር እስትንፋስ ያለው ነገር ሁሉ ሞተ። 23እግዚአብሔር በምድር ላይ ያለውን ሕያው ፍጥረት ሁሉ፥ ሰዎችንም፥ እንስሶችንም፥ ወፎችንም፥ በደረታቸው እየተሳቡ የሚንቀሳቀሱ ፍጥረቶች ሳይቀሩ ሁሉንም አጠፋ። ከሞት የተረፉት ኖኅና ከእርሱ ጋር በመርከቡ ውስጥ የነበሩት ብቻ ነበሩ። 24ውሃው እስከ መቶ ኀምሳ ቀን አልጐደለም ነበር።
Tans Gekies:
ኦሪት ዘፍጥረት 7: አማ05
Kleurmerk
Deel
Kopieer
Wil jy jou kleurmerke oor al jou toestelle gestoor hê? Teken in of teken aan
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997