ኦሪት ዘፍጥረት 6
6
የሰዎች ክፋት
1እንዲህም ሆነ፤ ሰዎች በምድር ላይ መብዛት በጀመሩ ጊዜ መልከ መልካሞች ሴቶች ልጆች ተወለዱላቸው፤ 2የእግዚአብሔር ልጆችም የሰውን ሴቶች ልጆች መልካሞች እንደሆኑ አዩ፤ ከመረጡአቸውም ሁሉ ሚስቶችን ለራሳቸው ወሰዱ። 3እግዚአብሔርም፥ “መንፈሴ በሰው ላይ ለዘለዓለም አይኖርም፤ እነርሱ ሥጋ ናቸውና፤ ዘመናቸውም መቶ ሃያ ዓመት ይሆናል” አለ። 4በእነዚያም ወራት ረዓይት በምድር ላይ ነበሩ። ከዚያም በኋላ የእግዚአብሔር ልጆች ወደ ሰው ሴቶች ልጆች በገቡ ጊዜ ልጆችን ወለዱላቸው፤ እነርሱም በዱሮ ዘመን ስማቸውን ያስጠሩ ኀያላን ሰዎች ሆኑ።
5እግዚአብሔርም የሰዎች ክፉ ሥራ በምድር ላይ እንደበዛ፥ የልባቸው ዐሳብ ምኞትም ሁል ጊዜ ፈጽሞ ክፉ እንደሆነ አየ። 6እግዚአብሔርም ሰውን በምድር ላይ በመፍጠሩ ተጸጸተ፤ በልቡም አዘነ። 7እግዚአብሔርም፥ “የፈጠርሁትን ሰው ከምድር ላይ አጠፋለሁ፤ ከሰው እስከ እንስሳና አራዊት፥ እስከ ተንቀሳቃሽም፥ እስከ ሰማይ ወፍም ድረስ፤ ስለ ፈጠርኋቸው ተጸጽቻለሁና” አለ። 8ኖኅ ግን በእግዚአብሔር ፊት ሞገስን አገኘ።
ኖኅ
9የኖኅ ትውልድ እንዲህ ነው። ኖኅም በትውልዱ ጻድቅ፥ ፍጹምም ሰው ነበረ፤ ኖኅም እግዚአብሔርን ደስ አሰኘው።#ዕብ. “ኖኅም አካሄዱን ከእግዚአብሔር ጋር አደረገ” ይላል። 10ኖኅም ሦስት ልጆችን ሴምን፥ ካምን ያፌትንም ወለደ። 11ምድርም በእግዚአብሔር ፊት ተበላሸች፤ ምድርም ግፍን ተመላች። 12እግዚአብሔርም ምድርን እንደ ተበላሸች፥ ሥጋን የለበሱ ሁሉም በምድር ላይ መንገዳቸውን እንደ አበላሹ አየ።
13እግዚአብሔር አምላክም ኖኅን አለው፥ “የሰው ሁሉ ጊዜው በፊቴ ደርሶአል፤ ከእነርሱ የተነሣ ምድር በግፍ ተመልታለችና፤ እኔም እነሆ፥ ከምድር ጋር አጠፋቸዋለሁ። 14ባለ አራት መዓዝን የዕንጨት መርከብን ለአንተ ሥራ፤ በመርከቢቱም ክፍሎችን አድርግ፤ በውስጥም፥ በውጭም በቅጥራን ለቅልቃት። 15መርከብዋንም እንዲህ ታደርጋታለህ፤ የመርከቢቱ ርዝመት ሦስት መቶ ክንድ፥ ወርድዋ አምሳ ክንድ፥ ከፍታዋ ሠላሳ ክንድ ይሁን። 16ለመርከቢቱም መስኮትን ታደርጋለህ፤ ከቁመቷም ክንድ ሙሉ ትተህ ጨርሳት፤ የመርከቢቱንም በር በጎንዋ አድርግ፤ ታችኛውንም፥ ሁለተኛውንም፥ ሦስተኛውንም ደርብ ታደርግላታለህ። 17እኔም እነሆ፥ ከሰማይ በታች የሕይወት ነፍስ ያለውን ሥጋ ሁሉ ለማጥፋት በምድር ላይ የጥፋት ውኃን አመጣለሁ፤ በምድር ያለው ሁሉ ይጠፋል። 18ቃል ኪዳኔንም ከአንተ ጋር አጸናለሁ፤ ወደ መርከብም አንተ ልጆችህንና ሚስትህን፥ የልጆችህንም ሚስቶች ይዘህ ትገባለህ። 19ከእንስሳ ሁሉ፥ ከተንቀሳቃሽ አራዊትም ሁሉ፥ ሥጋ ካለው ሁሉ ከአንተ ጋር ትመግባቸው ዘንድ ከሁሉም ሁለት ሁለት ወደ መርከብ ታገባለህ፤ ተባትና እንስት ይሁን። 20ከወፎች ሁሉ በየወገናቸው፥ ከእንስሳም ሁሉ በየወገናቸው፥ በምድር ላይ ከሚሳቡ ተንቀሳቃሾች ሁሉ በየወገናቸው ከአንተ ጋር ይመገቡ ዘንድ ከሁሉም ሁለት ሁለት ወንድና ሴት እየሆኑ ወደ አንተ ይግቡ። 21ከሚበላውም የመብል ዓይነት ሁሉ ለአንተ ውሰድ፤ ወደ አንተ ትሰበስባለህ፤ እርሱም ለአንተ፥ ለእነርሱም መብል ይሆናል።” 22ኖኅም እግዚአብሔር አምላክ ያዘዘውን ሁሉ አደረገ፤ እንዲሁ አደረገ።
Àwon tá yàn lọ́wọ́lọ́wọ́ báyìí:
ኦሪት ዘፍጥረት 6: አማ2000
Ìsàmì-sí
Pín
Daako
Ṣé o fẹ́ fi àwọn ohun pàtàkì pamọ́ sórí gbogbo àwọn ẹ̀rọ rẹ? Wọlé pẹ̀lú àkántì tuntun tàbí wọlé pẹ̀lú àkántì tí tẹ́lẹ̀