የሉቃስ ወንጌል 23

23
ኢየሱስ በጲላጦስና በሄሮድስ ፊት እንደ ቆመ
(ማቴ. 27፥1-211-14ማር. 15፥1-5ዮሐ. 18፥28-38)
1የተሰበሰቡት በሙሉ ተነሥተው ወደ ጲላጦስ ወሰዱትና 2“ይህ ሕዝባችንን ሲያስት ለቄሣርም ግብር እንዳይሰጥ ሲከለክል፥ ደግሞም ‘እኔ ክርስቶስ ንጉሥ ነኝ፤’ ሲል አገኘነው” ብለው ይከሱት ጀመር። 3ጲላጦስም “አንተ የአይሁድ ንጉሥ ነህን?” ብሎ ጠየቀው። እርሱም መልሶ “አንተ አልህ፤” አለው። 4ጲላጦስም ለካህናት አለቆችና ለሕዝቡ “በዚህ ሰው ላይ ምንም በደል አላገኘሁበትም፤” አለ። 5እነርሱ ግን “ከገሊላ ጀምሮ እስከዚህ ድረስ በይሁዳ ሁሉ እያስተማረ ሕዝቡን ያውካል” በማለት አጥብቀው ተናገሩ።
6ጲላጦስም ይህንን ሰምቶ ሰውየው የገሊላ ሰው እንደሆነ ጠየቀ፤ 7ከሄሮድስም ግዛት እንደመጣ ሲያውቅ፥ በዚያን ጊዜ በኢየሩሳሌም ተገኝቶ ወደነበረው ወደ ሄሮድስ ላከው። 8ሄሮድስም ኢየሱስን ባየው ጊዜ እጅግ ደስ አለው፤ ስለ እርሱ ስለ ሰማ ከብዙ ጊዜ ጀምሮ ሊያየው ይመኝ ነበርና፤ ተአምር ሲሠራ ሊያይ ተስፋ ያደርግ ነበር። 9በብዙ ቃልም ጠየቀው፤ እርሱ ግን ምንም መልስ አልሰጠውም። 10የካህናት አለቆችና ጻፎችም በብርቱ እየከሰሱት ቆመው ነበር። 11ሄሮድስም ከሠራዊቱ ጋር ናቀው፤ አፌዘበትም፤ የጌጥ ልብስም አልብሶ ወደ ጲላጦስ መልሶ ላከው። 12ሄሮድስና ጲላጦስም በዚያን ቀን ወዳጆች ሆኑ፤ በፊት በመካከላቸው ጥል ነበረና።
በርባን እንደ ተፈታ እና ኢየሱስ የሞት ፍርድ እንደ ተፈረደበት
(ማቴ. 27፥15-26ማር. 15፥6-15ዮሐ. 18፥30-4019፥1-16)
13ጲላጦስም፥ የካህናትን አለቆችና መኳንንትን ሕዝቡንም በአንድነት ጠርቶ 14እንዲህ አላቸው፤ “‘ሕዝቡን ያስታል፤’ ብላችሁ ይህን ሰው ወደ እኔ አመጣችሁት፤ እነሆም፥ በፊታችሁ መርምሬ ከምትከሱበት ነገር አንድ በደል እንኳ በዚህ ሰው ላይ አላገኘሁም። 15ሄሮድስም በበኩሉ ምንም አላገኘም፤ ወደ እኛ መልሶታልና፤ እነሆም፥ ለሞት የሚያደርሰው ምንም አላደረገም፤ 16እንግዲያስ ቀጥቼ እፈታዋለሁ።” 17(በበዓሉ አንድ እስረኛ ለሕዝቡ ይፈታላቸው ዘንድ ግድ ነበረና።)
18ሁሉም በአንድነት “ይህን አስወግደው፤ በርባንንም ፍታልን፤” እያሉ ጮኹ፤ 19እርሱም ሁከትን በከተማ አስነሥቶ ሰውን ስለ ገደለ በወኅኒ ታስሮ ነበር። 20ጲላጦስም ኢየሱስን ሊፈታ ፈልጎ ዳግመኛ ተናገራቸው፤ 21ነገር ግን እነርሱ “ስቀለው! ስቀለው!” እያሉ ይጮኹ ነበር። 22ለሦስተኛ ጊዜም “ይህ ሰው ምን ክፉ ነገር ሠራ? ለሞት የሚያደርሰው በደል አላገኘሁበትም፤ ስለዚህ ቀጥቼ እፈታዋለሁ፤” አላቸው። 23እነርሱ ግን እንዲሰቀል በታላቅ ድምፅ አጥብቀው ለመኑት። የእነርሱ ጩኸትና የካህናት አለቆችም ድምፅ በረታ። 24ጲላጦስም ልመናቸው እንዲፈጸም ፈረደበት። 25ሁከት በመፍጠርና ሰውን በመግደል ምክንያት ታስሮ የነበረውን በጥያቄአቸው መሠረት አስፈታላቸው፤ ኢየሱስን ግን እንደ ፈቃዳቸው አሳልፎ ሰጠው።
የኢየሱስ ክርስቶስ መሰቀል
(ማቴ. 27፥32-44ማር. 15፥21-23ዮሐ. 19፥17-27)
26በወሰዱትም ጊዜ ስምዖን የተባለ የቀሬናን ሰው ከገጠር ሲመጣ አግኝተው ያዙትና መስቀሉን ጭነውበት ከኢየሱስ በኋላ እንዲሄድ አደረጉት። 27ከሕዝቡ እጅግ ብዙ ሰዎችና ደረታቸውን እየመቱ የሚያለቅሱለት ብዙ ሴቶች ተከተሉት። 28ኢየሱስ ግን ወደ እነርሱ ዘወር ብሎ እንዲህ አለ “እናንተ የኢየሩሳሌም ልጆች፥ ለእኔ አታልቅሱልኝ፤ ይልቁንም ለራሳችሁና ለልጆቻችሁ አልቅሱ። 29‘መካኖችና ያልወለዱ ማኅፀኖች፥ ያላጠቡ ጡቶችም ብፁዓን ናቸው፤’ የሚባልበት ጊዜ እነሆ ይመጣልና። 30#ሆሴዕ 10፥8፤ ራእ. 6፥16።በዚያን ጊዜ ተራራዎችን ‘በላያችን ውደቁ፤’ ኮረብቶችንም ‘ሰውሩን፤’ ማለት ይጀምራሉ፤ 31በእርጥብ እንጨት ላይ እንዲህ የሚያደርጉ ከሆኑ፥ በደረቀውስ ላይ እንዴት ይሆን?”
32ሌሎችም ሁለት ክፉ አድራጊዎችንም ከእርሱ ጋር ለመግደል ይዘው ሄዱ። 33ቀራንዮ ወደሚባል ስፍራ በደረሱ ጊዜ፥ እርሱን፥ ክፉ አድራጊዎቹንም አንዱን በቀኙ አንዱን በግራው በኩል ሰቀሉ። 34#መዝ. 22፥19።ኢየሱስም “አባት ሆይ! የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው፤” አለ። ልብሱንም ዕጣ ተጣጥለው ተካፈሉት። 35#መዝ. 21፥8።ሕዝቡም ቆመው ይመለከቱ ነበር። መኰንኖቹም “ሌሎችን አዳነ፤ እርሱ በእግዚአብሔር የተመረጠው ክርስቶስ ከሆነ፥ ራሱን ያድን፤” እያሉ ያፌዙበት ነበር። 36#መዝ. 68፥22።ወታደሮቹም ወደ እርሱ ቀርበው፥ ሆምጣጤም አምጥተው 37“አንተ የአሁድ ንጉሥ ከሆንህ፥ ራስህን አድን፤” እያሉ ይቀልዱበት ነበር። 38“ይህ የአይሁድ ንጉሥ ነው፤” የሚል በግሪክ፥ በሮማይስጥና በዕብራይስጥ ፊደል የተጻፈ ጽሕፈት ደግሞ በእርሱ ላይ ነበረ።
39ከተሰቀሉት ክፉ አድራጊዎችም አንዱ “አንተ ክርስቶስ አይደለህምን? ራስህንም እኛንም አድን፤” ብሎ ሰደበው። 40ሁለተኛው ግን መልሶ “አንተ እንደዚህ ባለ ፍርድ ሳለህ እግዚአብሔርን ከቶ አትፈራውምን? 41እኛ ስለ አደረግነው የሚገባንን እየተቀበልን ነው፤ በእኛ ላይ የተወሰነው ትክክለኛ ፍርድ ነው፤ ይህ ሰው ግን ምንም ክፋት አልሠራም፤” ብሎ ገሠጸው። 42ኢየሱስንም “ጌታ ሆይ! በመንግሥትህ ስትመጣ አስበኝ፤” አለው። 43ኢየሱስም “እውነት እልሃለሁ፤ ዛሬ ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ፤” አለው።
የኢየሱስ ክርስቶስ መሞት
(ማቴ. 27፥45-56ማር. 15፥33-41ዮሐ. 19፥28-30)
44 # ዘፀ. 26፥31-33። ስድስት ሰዓትም ያህል ነበረ፤ ጨለማም እስከ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ በምድር ሁሉ ላይ ሆነ፤ 45ፀሐይም ጨለመ፤ የቤተ መቅደስም መጋረጃ ከመካከሉ ተቀደደ። 46#መዝ. 30፥6።ኢየሱስም በታላቅ ድምፅ ጮኾ “አባት ሆይ! ነፍሴን በእጅህ አደራ እሰጣለሁ፤” አለ። ይህንንም ብሎ ሞተ። 47የመቶ አለቃውም የሆነውን ነገር ባየ ጊዜ “ይህ ሰው በእውነት ጻድቅ ነበረ፤” ብሎ እግዚአብሔርን አከበረ። 48ይህንም ለማየት ተሰብስበው የነበሩ ሰዎች በሙሉ፥ የሆነውን ባዩ ጊዜ፥ ደረታቸውን እየመቱ ተመለሱ። 49#ሉቃ. 8፥2፤3።እርሱን የሚያውቁት ሁሉ ግን ከገሊላ የተከተሉት ሴቶችም ጭምር በሩቅ ቆመው ይህን እያዩ ነበር።
የኢየሱስ ክርስቶስ መቀበር
(ማቴ. 27፥57-61ማር. 15፥42-47ዮሐ. 19፥28-30)
50እነሆም፥ በጎና ጻድቅ እንዲሁም የሸንጎ አማካሪ የሆነ ዮሴፍ የሚባል ሰው ነበረ፤ 51ይህም በምክራቸውና በሥራቸው አልተባበረም ነበር፤ አርማትያስም ከምትባል ከአይሁድ ከተማ ሆኖ እርሱ በበኩሉ የእግዚአብሔርን መንግሥት ይጠባበቅ ነበር። 52ይኽም ሰው ወደ ጲላጦስ ቀርቦ የኢየሱስን አስከሬን ለመነው፤ 53አውርዶም በቀጭን ሐር ልብስ ከፈነው፤ ማንም ገና ባልተቀበረበት ከዓለትም በተወቀረ መቃብር አኖረው። 54የመዘጋጀት ቀንም ነበረ፤ ሰንበትም እየጀመረ ነበረ። 55ከገሊላም ከእርሱ ጋር የመጡት ሴቶች ተከትለው መቃብሩን እንዲሁም አስከሬኑን እንዴት እንዳኖሩት አዩ። 56#ዘፀ. 20፥10፤ ዘዳ. 5፥14።ተመልሰውም ሽቱና ቅባት አዘጋጁ። በሰንበትም ዕለት ሕጉ እንዲሚያዘው ዐረፉ።

Айни замон обунашуда:

የሉቃስ ወንጌል 23: መቅካእኤ

Лаҳзаҳои махсус

Паҳн кунед

Нусха

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in