Logótipo YouVersion
Ícone de pesquisa

ሉቃስ 21

21
መበለቷ የሰጠችው መባ
21፥1-4 ተጓ ምብ – ማር 12፥41-44
1ኢየሱስ ቀና ብሎ ሲመለከት ሀብታሞች በቤተ መቅደሱ መባ መሰብሰቢያ ውስጥ መባቸውን ሲጨምሩ አየ። 2ደግሞም አንዲት ድኻ መበለት ሁለት ትንንሽ የናስ ሳንቲሞች በዚያ ስትጨምር ተመለከተ። 3እንዲህም አለ፤ “እውነት እላችኋለሁ፤ ከሁሉም ይልቅ ይህች ድኻ መበለት የበለጠ ሰጥታለች። 4እነዚህ ሰዎች የሰጡት ከትርፋቸው ላይ ሲሆን፣ እርሷ ግን የሰጠችው በድኻ ዐቅሟ ያላትን መተዳደሪያ በሙሉ ነው።”
የዘመኑ መጨረሻ ምልክቶች
21፥5-36 ተጓ ምብ – ማቴ 24ማር 13
21፥12-17 ተጓ ምብ – ማቴ 10፥17-22
5ከደቀ መዛሙርት አንዳንዶች ቤተ መቅደሱ በውብ ድንጋዮችና በስእለት ስጦታዎች እንዳማረ ሲነጋገሩ፣ ኢየሱስ እንዲህ አለ፤ 6“ይህ የምታዩት ሁሉ ሳይፈርስ ድንጋይ በድንጋይ ላይ እንደ ተካበ የማይቀርበት ጊዜ ይመጣል።”
7እነርሱም፣ “መምህር ሆይ፤ እንግዲህ ይህ ሁሉ የሚሆነው መቼ ነው? ደግሞም ይህ እንደሚሆን ምልክቱ ምንድን ነው?” ብለው ጠየቁት።
8እርሱም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “እንዳትስቱ ተጠንቀቁ፤ ብዙዎች፣ ‘እኔ እርሱ ነኝ’ በማለት፣ ደግሞም፣ ‘ጊዜው ቀርቧል’ እያሉ በስሜ ይመጣሉና፤ እናንተ ግን እነርሱን አትከተሏቸው። 9ስለ ጦርነትና ስለ ሕዝብ ዐመፅ ስትሰሙ አትደንግጡ፤ ይህ አስቀድሞ መሆን የሚገባው ነውና፤ መጨረሻው ግን ወዲያውኑ አይሆንም።”
10ቀጥሎም እንዲህ አላቸው፤ “ሕዝብ በሕዝብ ላይ፣ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣል፤ 11ታላቅ የመሬት መናወጥ ይሆናል፤ ራብና ቸነፈር በተለያየ ስፍራ ይከሠታል፤ አስፈሪ ነገር እንዲሁም ከሰማይ ታላቅ ምልክት ይሆናል።
12 “ይህ ሁሉ ከመሆኑ በፊት ግን ሰዎች ይይዟችኋል፤ ያሳድዷችኋል፤ ወደ ምኵራብና ወደ ወህኒ ቤት ያስገቧችኋል፤ በነገሥታትና በገዥዎች ፊት ያቀርቧችኋል፤ ይህም ሁሉ በስሜ ምክንያት ይደርስባችኋል። 13ይህም ለመመስከር ጥሩ ዕድል ይሆንላችኋል። 14ስለዚህ ምን መልስ እንሰጣለን በማለት አስቀድማችሁ እንዳትጨነቁ ይህን ልብ በሉ፤ 15ተቃዋሚዎቻችሁ ሁሉ ሊቋቋሙትና ሊያስተባብሉት የማይችሉትን ቃልና ጥበብ እሰጣችኋለሁና። 16ወላጆቻችሁ፣ ወንድሞቻችሁ፣ ዘመዶቻችሁና ጓደኞቻችሁ እንኳ ሳይቀሩ አሳልፈው ይሰጧችኋል፤ ከእናንተም አንዳንዶቹን ይገድላሉ፤ 17ስለ ስሜም በሰዎች ሁሉ ዘንድ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ። 18ነገር ግን ከራሳችሁ ጠጕር አንዷ እንኳ አትጠፋም፤ 19ጸንታችሁም በመቆም ነፍሳችሁን ታተርፋላችሁ።
20 “ኢየሩሳሌም በጦር ሰራዊት ተከብባ በምታዩበት ጊዜ፣ ጥፋቷ መቃረቡን ዕወቁ። 21በዚያን ጊዜ በይሁዳ ያሉ ወደ ተራሮች ይሽሹ፤ በከተማ ያሉትም ከዚያ ይውጡ፤ በገጠር ያሉትም ወደ ከተማዪቱ አይግቡ፤ 22የተጻፈው ሁሉ ይፈጸም ዘንድ ይህ የበቀል ጊዜ ነውና። 23በምድሪቱ ላይ ታላቅ መከራ ይሆናል፤ በዚህም ሕዝብ ላይ ቍጣ ይመጣል፤ ስለዚህ በዚያን ወቅት ለነፍሰ ጡሮችና ለሚያጠቡ እናቶች ወዮላቸው! 24በሰይፍ ይወድቃሉ፤ ወደ አሕዛብም ሁሉ በምርኮ ይወሰዳሉ፤ ኢየሩሳሌምም የአሕዛብ ዘመን እስኪፈጸም ድረስ በአሕዛብ የተረገጠች ትሆናለች።
25 “በፀሓይ፣ በጨረቃና በከዋክብት ላይ ምልክት ይሆናል፤ ከባሕሩና ከሞገድ ድምፅ የተነሣ፣ በምድር ላይ ያሉ ሕዝቦች ይጨነቃሉ፤ ይታወካሉም። 26የሰማያት ኀይላት ስለሚናወጡ፣ ሰዎች በፍርሀትና በዓለም ላይ ምን ይመጣ ይሆን እያሉ በመጠባበቅ ይዝላሉ። 27በዚያን ጊዜ የሰው ልጅ በኀይልና በታላቅ ክብር በደመና ሲመጣ ያዩታል። 28እናንተም እነዚህ ነገሮች መፈጸም ሲጀምሩ፣ መዳናችሁ ስለ ተቃረበ ቀጥ ብላችሁ ቁሙ፤ ራሳችሁንም ወደ ላይ ቀና አድርጉ።”
29ቀጥሎም እንዲህ ሲል ይህን ምሳሌ ነገራቸው፤ “በለስንና ዛፎችን ሁሉ ተመልከቱ፤ 30ቅጠሎቻቸው አቈጥቍጠው ስታዩ፣ በዚያን ጊዜ በጋ መቃረቡን ራሳችሁ ታውቃላችሁ። 31እንዲሁ ደግሞ እነዚህ ነገሮች መፈጸማቸውን ስታዩ፣ የእግዚአብሔር መንግሥት እንደ ቀረበች ዕወቁ።
32 “እውነት እላችኋለሁ፤ ይህ ሁሉ እስኪፈጸም ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም። # 21፥32 ወይም ዘር 33ሰማይና ምድር ያልፋሉ፤ ቃሌ ግን አያልፍም።
34 “እንግዲህ በገደብ የለሽ ሕይወት፣ በመጠጥ ብዛትና ስለ ኑሮ በመጨነቅ ልባችሁ እንዳይዝልና ያ ቀን እንደ ወጥመድ ድንገት እንዳይደርስባችሁ ተጠንቀቁ፤ 35ይህ በመላው ምድር በሚኖሩት ሁሉ ላይ ይደርሳልና። 36ስለዚህ ከሚመጣው ሁሉ እንድታመልጡና በሰው ልጅ ፊት መቆም እንድትችሉ ሁልጊዜ ተግታችሁ ጸልዩ።”
37ኢየሱስም ቀን ቀን በቤተ መቅደስ እያስተማረ፣ ሌሊት ግን ደብረ ዘይት ወደ ተባለ ተራራ ወጥቶ ያድር ነበር። 38ሕዝቡም ሁሉ ሊሰሙት ማልደው ወደ ቤተ መቅደስ ወደ እርሱ ይመጡ ነበር።

Atualmente selecionado:

ሉቃስ 21: NASV

Destaque

Partilhar

Copiar

None

Quer salvar os seus destaques em todos os seus dispositivos? Faça o seu registo ou inicie sessão