የሉቃስ ወንጌል 18
18
ያለ መሰልቸት ስለ መጸለይ ምሳሌ
1ዘወትር እንዲጸልዩ፥ እንዳይሰለቹም በምሳሌ ነገራቸው። 2እንዲህም አላቸው፥ “በአንዲት ከተማ እግዚአብሔርን የማይፈራ፥ ሰውንም የማያፍር አንድ ዳኛ ነበር። 3በዚያችም ከተማ አንዲት መበለት ነበረች፤ ዕለት ዕለትም#“ዕለት ዕለትም” የሚለው በግሪኩ እና በአንዳንድ የግእዝ ዘርዕ የለም። ወደ እርሱ እየመጣች ከባለጋራዬ ፍረድልኝ ትለው ነበር። 4እንቢ ብሎም አዘገያት። ከዚህም በኋላ በልቡ ዐስቦ እንዲህ አለ፦ ‘ምንም እግዚአብሔርን ባልፈራ፥ ሰውንም ባላፍር 5ይህቺ ሴት እንዳትዘበዝበኝ፥ ዘወትርም እየመጣች እንዳታታክተኝ እፈርድላታለሁ’።” 6ጌታችንም እንዲህ አላቸው፥ “ዐመፀኛው ዳኛ ያለውን ስሙ። 7እንግዲህ እግዚአብሔር በመዓልትና በሌሊት ወደ እርሱ ለሚጮኹ ለወዳጆቹ አይፈርድምን? ወይስ ቸል ይላቸዋልን? 8እላችኋለሁ ፈጥኖ ይፈርድላቸዋል፤ ነገር ግን የሰው ልጅ በመጣ ጊዜ በምድር ላይ እምነትን ያገኝ ይሆን?”
ስለ ፈሪሳዊዉና ስለ ቀራጩ
9ራሳቸውን ለሚያመጻድቁና ባልንጀራቸውን ለሚንቁ እንዲህ ብሎ መሰለላቸው። 10“ሁለት ሰዎች ሊጸልዩ ወደ ቤተ መቅደስ ወጡ፤ አንዱ ፈሪሳዊ፥ ሁለተኛውም ቀራጭ ነበር። 11ፈሪሳዊውም ቆመና እንዲህ ብሎ ጸለየ፦ ‘አቤቱ እንደ ሌሎች ሰዎች፥ እንደ ቀማኞችና እንደ ዐመፀኞች፥ እንደ አመንዝሮችም፥ ወይም እንደዚህ ቀራጭ ያላደረግኸኝ#በግሪኩ “ስላልሆንሁ” ይላል። አመሰግንሃለሁ። 12እኔ በየሳምንቱ ሁለት ቀን እጾማለሁ፤ ከማገኘውም ሁሉ ከዐሥር አንድ እሰጣለሁ።’ 13ቀራጩ ግን ራቅ ብሎ ቆመ፤ ዐይኖቹንም ወደ ላይ ወደ ሰማይ ሊያነሣ አልወደደም፤ ደረቱንም እየመታ፦ ‘አቤቱ፥ እኔን ኀጢኣተኛውን ይቅር በለኝ’ አለ። 14#ማቴ. 23፥12፤ ሉቃ. 14፥11። እላችኋለሁ፥ ከዚያ ይልቅ ይህ ጻድቅ ሆኖ ወደ ቤቱ ተመለሰ፤ ራሱን ከፍ ከፍ የሚያደርግ ሁሉ ይዋረዳልና፤ ራሱንም የሚያዋርድ ይከብራልና።”
ጌታችን ሕፃናትን ስለ መባረኩ
15ይባርካቸውም ዘንድ ሕፃናትን ወደ እርሱ አመጡአቸው፤ ደቀ መዛሙርቱም አይተው ገሠጹአቸው። 16ጌታችን ኢየሱስም ጠራቸው፤#በግሪኩ “ሕፃናትን ጠርቶ አለ” ይላል። እንዲህም አላቸው፥ “ሕፃናትን ወደ እኔ ይመጡ ዘንድ ተዉአቸው፥ አትከልክሉአቸውም፤ የእግዚአብሔር መንግሥት እንደ እነዚህ ላሉት ናትና። 17እውነት እላችኋለሁ፥ የእግዚአብሔርን መንግሥት እንደ ሕፃናት ያልተቀበላት አይገባባትም።”
ስለ ሕይወት ጥያቄ
18አንድ አለቃም፥ “ቸር መምህር፥ ምን ሥራ ሠርቼ የዘለዓለም ሕይወትን እወርሳለሁ?” አለው። 19ጌታችን ኢየሱስም እንዲህ አለው፥ “ለምን ቸር ትለኛለህ? ከአንዱ ከእግዚአብሔር በቀር ቸር የለም። 20#ዘፀ. 20፥12-16፤ ዘዳ. 5፥16-20። ትእዛዛቱን አንተ ራስህ ታውቃለህ፤ ‘አትግደል፤ አታመንዝር፤ አትስረቅ፤ በሐሰት አትመስክር፤ አባትህንና እናትህንም አክብር።’ 21እርሱም፦ ‘ይህንስ ሁሉ ከልጅነቴ ጀምሬ እስከ ዛሬ ጠብቄአለሁ’።” አለው። 22ጌታችን ኢየሱስም ይህን ሰምቶ እንዲህ አለው፥ “አንዲት ቀርታሃለች፤ ሂድና ያለህን ሁሉ ሸጠህ ለነዳያን ስጥ፤ በሰማይም መዝገብ ታገኛለህ፤ መጥተህም ተከተለኝ።” 23እርሱ ግን ይህን ሰምቶ በጣም አዘነ፤ እርሱ እጅግ ባለጸጋ ነበርና። 24ጌታችን ኢየሱስም እጅግ ሲያዝን አይቶ እንዲህ አለ፥ “ገንዘብ ላላቸው ሰዎች ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት እንዴት ጭንቅ ነው! 25ባለጸጋ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ከሚገባ ይልቅ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ሊያልፍ ይቀላል።” 26የሰሙትም፥ “እንግዲህ ማን ሊድን ይችላል?” አሉ። 27እርሱ ግን “በሰው ዘንድ የማይቻለው በእግዚአብሔር ዘንድ ይቻላል” አላቸው።
የጴጥሮስ ጥያቄ
28ጴጥሮስም፥ “እነሆ፥ እኛ ሁሉን ትተን ተከትለንሃል፤ እንግዲህ ምን እናገኛለን?”#“እንግዲህ ምን እናንገኛለን” የሚለውን ግሪኩ እና አንዳንድ የግእዝ ዘርዕ አይጽፍም። አለው። 29እርሱም እንዲህ አላቸው፥ “እውነት እላችኋለሁ፥ ቤቱንና ዘመዶቹን፥ ወንድሞቹንና ሚስቱን፥ ልጆቹንም ስለ እግዚአብሔር መንግሥት የሚተው፥ 30በዚህ ዓለም መቶ እጥፍ#በግሪኩ እና በአንዳንድ የግእዝ ዘርዕ “ብዙ ዕጥፍ” ይላል። ዋጋ፥ በሚመጣውም ዓለም የዘለዓለም ሕይወትን የማይቀበል ማንም የለም።”
ስለ ሕማሙና ስለ ሞቱ
31ዐሥራ ሁለቱንም ወሰዳቸው፤ እንዲህም አላቸው፥ “እነሆ፥ ወደ ኢየሩሳሌም እንወጣለን፤ በነቢያትም የተጻፈው ሁሉ በሰው ልጅ ላይ ይፈጸማል። 32ለአሕዛብ አሳልፈው ይሰጡታል፤ ይዘብቱበታልም፤ ይሰድቡታልም፤ ይተፉበታልም። 33ይገርፉታል፤ ይገድሉታልም፤ በሦስተኛዪቱም ቀን ይነሣል።” 34እነርሱ ግን፤ ከተናገራቸው ያስተዋሉት የለም፤ ይህ ነገር ከእነርሱ የተሰወረ ነበርና፤ የተናገረውንም አያውቁም ነበርና።
በኢያሪኮ ስለ ነበረው ዕውር
35ከዚህም በኋላ ኢያሪኮ በደረሱ ጊዜ አንድ ዕውር በጎዳና ተቀምጦ ይለምን ነበር። 36የሚያልፈውንም ሰው ድምፅ ሰምቶ፥ “ይህ የምሰማው ምንድን ነው?” አለ። 37እነርሱም፥ “የናዝሬቱ ኢየሱስ ያልፋል” ብለው ነገሩት። 38ድምፁንም ከፍ አድርጎ፥ “የዳዊት ልጅ ኢየሱስ ሆይ፥ ማረኝ” አለ። 39የሚመሩትም ዝም እንዲል ገሠጹት፤ እርሱ ግን በጣም ጮኾ፥ “የዳዊት ልጅ ሆይ፥ ማረኝ” አለ። 40ጌታችን ኢየሱስም ቆመና ወደ እርሱ እንዲያመጡት አዘዘ። 41ወደ እርሱም በደረሰ ጊዜ፥ “ምን ላደርግልህ ትወዳለህ?” ብሎ ጠየቀው፤ እርሱም፥ “ጌታ ሆይ፥ ዐይኖች እንዲያዩ ነው” አለው። 42ጌታችን ኢየሱስም፥ “እይ፤ እምነትህ አዳነችህ” አለው። 43በዚያን ጊዜም አየ፤ እግዚአብሔርንም አመሰገነ፤ ተከተለውም፤ ሕዝቡም ሁሉ አይተው እግዚአብሔርን አመሰገኑት።
Markert nå:
የሉቃስ ወንጌል 18: አማ2000
Marker
Del
Kopier
Vil du ha høydepunktene lagret på alle enhetene dine? Registrer deg eller logg på