ኦሪት ዘፍጥረት 9

9
የአዲሱ ዓለም ሥርዓት
1 # ዘፍ. 1፥28። እግዚአብሔርም ኖኅንና ልጆቹን ባረካቸው፥ እንዲህም አላቸው፦ “ብዙ ተባዙ፥ ምድርንም ሙሉአት። 2እንስሶች፥ ወፎች፥ በደረታቸው እየተሳቡ የሚንቀሳቀሱ ፍጥረቶችና ዓሣዎች ሁሉ እናንተን በመፍራትና በመደንገጥ ይኑሩ፤ ሁሉም በሥልጣናችሁ ሥር ይሁኑ። 3ከዚህ በፊት የአትክልት ዓይነቶችን ምግብ አድርጌ እንደሰጠኋችሁ እነዚህንም ተንቀሳቃሽ ፍጥረቶች ሁሉ ምግብ እንዲሆኑአችሁ ሰጥቻችኋለሁ። 4#ዘሌ. 7፥26፤27፤ 17፥10-14፤ 19፥26፤ ዘዳ. 12፥16፤23፤ 15፥23።ነገር ግን ደም ያለችበትን ሥጋ አትብሉ፥ ምክንያቱም በደም ውስጥ ሕይወት አለ። 5ነፍሳችሁ ያለችበትን ደማችሁን በእርግጥ እሻዋለሁ፥ ከአራዊት እና ከሰውም ሁሉ እጅ እሻዋለሁ፥ ከሰው ወንድም እጅ፥ የሰውን ነፍስ እሻለሁ። 6#ዘፀ. 20፥13፤ ዘፍ. 1፥26።ሰው የተፈጠረው በእግዚአብሔር አምሳያ ስለ ሆነ፥ ሰውን የሚገድል ሁሉ በሰው እጅ ይሞታል። 7#ዘፍ. 1፥28።እናንተ ፍሬያማ ሆናችሁ ተባዙ፤ ዘራችሁ በምድር ላይ ይብዛ።”
8ከዚህ በኋላ እግዚአብሔርም ለኖኅ፥ ከእርሱም ጋር ለልጆቹ እንዲህ ብሎ ተናገረ፦ 9“እነሆ፥ እኔም ቃል ኪዳኔን ከእናንተ ጋር፥ ከእናንተም በኋላ ከዘራችሁ ጋር እመሠርታለሁ፤ 10ይህም ከእናንተ ጋር ላሉትም ሕያው ነፍስ ላላቸው ሁሉ፥ ከእናንተ ጋር ከመርከብ ለወጡት አእዋፍ፥ ለእንስሳትም፥ ለምድር አራዊትም ሁሉ፥ ለየትኛውም የምድር አራዊት ሁሉ ይሆናል። 11ቃል ኪዳኔንም ለእናንተ እመሰርታለሁ፥ ሕያው ፍጥረት ሁሉ ዳግመኛ በጥፋት ውኃ አይጠፉም፥ ምድርንም ለማጥፋት ዳግመኛ የጥፋት ውኃ አይመጣም።” 12እንዲህም ሲል እግዚአብሔር ተናገረ፦ “በእኔና በእናንተ፥ ከእናንተም ጋር ባለው በሕያው ፍጥረት ሁሉ መካከል፥ ለዘለዓለም የማደርገው፥ የቃል ኪዳን ምልክት ይህ ነው፥ 13ቀስቴን በደመና አደርጋለሁ፥ ይህም በእኔና በምድር መካከል የቃል ኪዳን ምልክት ይሆናል። 14ምድር በደመና በምትሸፈንበት ቀስቲቱም በደመናው በምትታይበት ጊዜ፥ 15በእኔና በእናንተ፥ ሕያው ነፍስ ባለውም ፍጥረት መካከል ያለውን ቃል ኪዳኔን አስባለሁ፤ ውኃም ዳግመኛ ፍጥረትን ሁሉ ያጠፋ ዘንድ የውኃ ሙላት አይመጣም። 16ቀስቲቱም በደመና ስትሆን፥ አያታለሁም በእኔና በምድር ላይ በሚኖር ሥጋ ባለው በሕያው ፍጥረት ሁሉ መካከል ያለውን ዘላለማዊ ቃል ኪዳን አስታውሳለሁ።” 17እግዚአብሔርም ኖኅን፦ “ይህ በእኔና በምድር ላይ በሚኖሩ ሕይወት ባላቸው ፍጥረቶች መካከል ያቆምሁት የቃል ኪዳን ምልክት ነው” አለው።
ሐ. ከጥፋት ውሃ ወደ አብርሃም
ኖኅና ልጆቹ
18ከመርከቡ የወጡት የኖኅ ልጆች ሴም፥ ካምና ያፌት ናቸው፤ ካም የከነዓን አባት ነው። 19በምድር ሁሉ ላይ የተበተኑ የኖኅ ልጆች እነዚህ ሦስቱ ናቸው።
20ኖኅ ቀዳሚ ገበሬ ነበረ፤ የወይን ተክልንም ተከለ። 21ከዕለታት አንድ ቀን ከወይን ጠጁም ጠጣ፥ ሰከረም፥ በድንኳኑም ውስጥ እራቁቱን ተኛ። 22የከነዓን አባት፥ ካምም፥ የአባቱን ዕራቁቱን መሆን አየ፥ ወደ ውጭም ወጥቶ ለሁለቱ ወንድሞቹ ነገራቸው። 23ሴምና ያፌትም ልብስ በትከሻቸው ላይ አደረጉ፥ የኋሊትም ሄደው የአባታቸውን ዕራቁትነት አለበሱ፤ ፊታቸውም ወደ ኋላ ነበረ፥ የአባታቸውንም ዕራቁትነት አላዩም። 24ኖኅም ከወይን ጠጁ ስካር ሲነቃ፥ ታናሽ ልጁ ያደረገበትን አወቀ።
25እንዲህም አለ፦
“ከነዓን የተረገመ ይሁን!
ለወንድሞቹም የባርያዎች ባርያ ይሁን።”
26ደግሞም እንዲህ አለ፦
“የሴም ጌታ እግዚእብሔር ይባረክ!
ከነዓንም የሴም አገልጋይ ይሁን!
27“እግዚአብሔርም ያፌትን ያደርጀው!
በሴምም ድንኳን ይደር!
ከነዓንም የያፌት አገልጋይ ይሁን!”
28ከጥፋት ውኃ በኋላም ኖኅ ሦስት መቶ አምሳ ዓመት ኖረ። 29ኖኅም የኖረበት ዘመን በአጠቃላይ ዘጠኝ መቶ አምሳ ዓመት ሆነ፥ ሞተም።

Marker

Del

Kopier

None

Vil du ha høydepunktene lagret på alle enhetene dine? Registrer deg eller logg på

Video om ኦሪት ዘፍጥረት 9