ዮሐንስ 2

2
ኢየሱስ ውሃን የወይን ጠጅ አደረገ
1በሦስተኛው ቀን፣ በገሊላ አውራጃ፣ በቃና ከተማ ሰርግ ነበር፤ የኢየሱስም እናት በዚያ ነበረች፤ 2ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱም ወደ ሰርጉ ተጠርተው ነበር። 3የወይን ጠጅ ባለቀ ጊዜም የኢየሱስ እናት፣ “የወይን ጠጅ እኮ ዐለቀባቸው” አለችው።
4ኢየሱስም፣ “አንቺ ሴት ሆይ፤#2፥4 በግሪኩ ላይ እንደ ተመለከተው ይህ አጠራር ያለ ማክበርን የሚያሳይ አይደለም። ምን አድርግ ትይኛለሽ? ጊዜዬ ገና አልደረሰም” አላት።
5እናቱም በዚያ የነበሩትን አገልጋዮች፣ “የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ” አለቻቸው።
6በአይሁድ የመንጻት ሥርዐት መሠረት፣ ከሰባ ዐምስት እስከ አንድ መቶ ዐሥራ ዐምስት ሊትር የሚይዙ ከድንጋይ የተሠሩ ስድስት ጋኖች#2፥6 በግሪኩ ሁለት ወይም ሦስት እንስራ ወይንም ከ75–115 ሊትር ይሆናል። በዚያ ነበሩ።
7ኢየሱስ አገልጋዮቹን፣ “ጋኖቹን ውሃ ሙሏቸው” አላቸው፤ እነርሱም፣ ጋኖቹን እስከ አፋቸው ሞሏቸው።
8እርሱም፣ “ከላዩ ቀድታችሁ ለድግሱ ኀላፊ ስጡት” አላቸው።
እነርሱም እንዳዘዛቸው አደረጉ። 9የድግሱ ኀላፊም ወደ ወይን ጠጅ የተለወጠውን ውሃ ቀመሰ፤ ሆኖም ከየት እንደ መጣ አላወቀም፤ ውሃውን የቀዱት አገልጋዮች ግን ያውቁ ነበር። እርሱም ሙሽራውን ለብቻው ጠርቶ፣ 10“ሰው ሁሉ በመጀመሪያ የሚያቀርበው ጥሩውን የወይን ጠጅ ነው፤ እንግዶቹም ብዙ ከጠጡ በኋላ መናኛውን የወይን ጠጅ ያቀርባል፤ አንተ ግን ጥሩውን የወይን ጠጅ እስከ አሁን አቈይተሃል” አለው።
11ኢየሱስም ይህን የታምራዊ ምልክቶቹ መጀመሪያ በገሊላ አውራጃ በቃና ከተማ አደረገ፤ ክብሩንም ገለጠ፤ ደቀ መዛሙርቱም በርሱ አመኑ።
ኢየሱስ ቤተ መቅደስን አጠራ
2፥14-16 ተጓ ምብ – ማቴ 21፥12-13ማር 11፥15-17ሉቃ 19፥45-46
12ከዚህ በኋላ ከእናቱ፣ ከወንድሞቹና ከደቀ መዛሙርቱ ጋራ ወደ ቅፍርናሆም ወረደ፤ በዚያም ጥቂት ቀን ተቀመጡ።
13የአይሁድ ፋሲካም እንደ ተቃረበ፣ ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም ወጣ። 14በቤተ መቅደስ ውስጥ ከብቶችን፣ በጎችንና ርግቦችን የሚሸጡ እንዲሁም ተቀምጠው የገንዘብ ምንዛሪ የሚያከናውኑ ሰዎች አገኘ። 15የገመድ ጅራፍ አበጅቶ በጎችንና ከብቶችን ሁሉ ከቤተ መቅደሱ ግቢ አስወጣ፤ የገንዘብ ለዋጮችን ሳንቲም በተነ፤ ጠረጴዛዎቻቸውንም ገለበጠ። 16ርግብ ሻጮችንም፣ “እነዚህን ከዚህ አስወጧቸው፤ የአባቴን ቤት የንግድ ቤት አታድርጉት!” አላቸው። 17ደቀ መዛሙርቱም፣ “የቤትህ ቅናት ይበላኛል” ተብሎ የተጻፈው ትዝ አላቸው።
18አይሁድም፣ “ይህን ሁሉ ለማድረግ ሥልጣን እንዳለህ የሚያረጋግጥ ምን ታምራዊ ምልክት ታሳየናለህ?” አሉት።
19ኢየሱስም፣ “ይህን ቤተ መቅደስ አፍርሱት፤ እኔም በሦስት ቀን መልሼ አነሣዋለሁ” ብሎ መለሰላቸው።
20አይሁድም፣ “ይህን ቤተ መቅደስ ለመሥራት አርባ ስድስት ዓመት ፈጅቷል፤ ታዲያ አንተ እንዴት በሦስት ቀን መልሰህ ታነሣዋለህ?” አሉት። 21ቤተ መቅደስ ሲል ግን፣ ስለ ገዛ ሰውነቱ መናገሩ ነበር። 22ከሙታንም ከተነሣ በኋላ፣ ደቀ መዛሙርቱ ምን እንደ ተናገረ አስታወሱ፤ መጻሕፍትንና ኢየሱስ ያለውንም ቃል አመኑ።
23በፋሲካ በዓል በኢየሩሳሌም ሳለ፣ ብዙ ሰዎች ያደረገውን ታምራት አይተው በስሙ አመኑ፤#2፥23 ወይም በርሱም አመኑ 24ኢየሱስ ግን ሰውን ሁሉ ስለሚያውቅ፣ አይታመንባቸውም ነበር፤ 25በሰው ውስጥ ያለውን ያውቅ ስለ ነበር፣ ማንም ስለ ሰው እንዲመሰክርለት አላስፈለገውም።

Nu geselecteerd:

ዮሐንስ 2: NASV

Markering

Deel

Kopiëren

None

Wil je jouw markerkingen op al je apparaten opslaan? Meld je aan of log in