ኦሪት ዘፍጥረት 11
11
የባቢሎን ግንብ
1በመጀመሪያ የዓለም ሕዝቦች መነጋገሪያ ቋንቋ አንድ ብቻ ነበር፤ 2ሰዎች ከምሥራቅ ተነሥተው በተጓዙ ጊዜ በሰናዖር ምድር አንድ ሜዳ አገኙ፤ በዚያም ተቀመጡ። 3እርስ በርሳቸውም “ኑ! ጡብ እንሥራ፤ እንዲጠነክርም በእሳት እንተኲሰው” ተባባሉ፤ በዚህ ዐይነት የሚገነቡትን ጡብ አገኙ፤ በአንድነት የሚያጣብቁበትንም ቅጥራን አገኙ። 4እንዲህም አሉ፦ “ኑ አንድ ከተማ እንመሥርት፤ በዚያም ጫፉ እስከ ሰማይ የሚደርስ ግንብ እንሥራ፤ በምድር ላይ እንዳንበታተን ስማችንን እናስጠራ።”
5ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር ሰዎቹ ይሠሩአቸው የነበሩትን ከተማና ግንብ ለማየት ወረደ፤ 6እንዲህም አለ፤ “እነሆ፥ እነዚህ ሰዎች አንድ ወገን ናቸው፤ መነጋገሪያ ቋንቋቸውም አንድ ነው፤ ይህም ከሚሠሩት የመጀመሪያው ብቻ ነው፤ በዚህ ዐይነት ሊሠሩ ያቀዱትን ሁሉ ማድረግ አያቅታቸውም። 7ስለዚህ ኑ! እንውረድና እርስ በርሳቸው እንዳይግባቡ ቋንቋቸውን እንደበላልቀው።” 8ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር በምድር ሁሉ ላይ በተናቸው፤ ከተማውንም መሥራት አቆሙ፤ 9በዚያ እግዚአብሔር የሕዝቡን ቋንቋ ስለ ደበላለቀና እነርሱን በዓለም ዙሪያ ስለ በተናቸው የከተማውም ስም “ባቢሎን” ተባለ። #11፥9 ባቢሎን፦ በዕብራይስጥ “መደባለቅ” ማለት ነው።
ከሴም እስከ አብርሃም
(1ዜ.መ. 1፥24-27)
10የሴም ዘሮች የሚከተሉት ናቸው፦ ከጥፋት ውሃ በኋላ ሁለት ዓመት ቈይቶ ሴም 100 ዓመት በሆነው ጊዜ አርፋክስድ የተባለ ልጅ ወለደ፤ 11አርፋክስድን ከወለደ በኋላ 500 ዓመት ኖረ፤ ሌሎችንም ወንዶች ልጆችንና ሴቶችን ልጆች ወለደ።
12አርፋክስድም 35 ዓመት ሲሆነው ሳላሕን ወለደ። #11፥12 በዕብራይስጥ 35 ሲል በሰባ ሊቃናት 135 ይላል። 13ከዚህ በኋላ 403 ዓመት ኖረ፤ ሌሎችንም ወንዶች ልጆችና ሴቶች ልጆችን ወለደ።
14ሳላሕ 30 ዓመት ሲሆነው ዔቦርን ወለደ፤ #11፥14 በዕብራይስጥ 30 ሲል በሰባ ሊቃናት 130 ይላል። 15ከዚህ በኋላ 403 ዓመት ኖረ፤ ሌሎችንም ወንዶች ልጆችንና ሴቶች ልጆችን ወለደ።
16ዔቦር 34 ዓመት ሲሆነው ፋሌቅን ወለደ፤ #11፥16 በዕብራይስጥ 34 ሲል በሰባ ሊቃናት 134 ይላል። 17ከዚህ በኋላ 430 ዓመት ኖረ፤ ሌሎችንም ወንዶች ልጆችና ሴቶች ልጆችን ወለደ። 18ፋሌቅ 30 ዓመት ሲሆነው ረዑን ወለደ፤ #11፥18 በዕብራይስጥ 30 ሲል በሰባ ሊቃናት 130 ይላል። 19ከዚህ በኋላ 209 ዓመት ኖረ፤ ሌሎችንም ወንዶች ልጆችና ሴቶች ልጆችን ወለደ።
20ረዑ 32 ዓመት ሲሆነው ሰሩግን ወለደ፤ #11፥20 በዕብራይስጥ 32 ሲል በሰባ ሊቃናት 132 ይላል። 21ከዚህ በኋላ 207 ዓመት ኖረ፤ ሌሎችንም ወንዶች ልጆችና ሴቶች ልጆችን ወለደ።
22ሰሩግ 30 ዓመት ሲሆነው ናኮርን ወለደ፤ #11፥22 በዕብራይስጥ 30 ሲል በሰባ ሊቃናት 130 ይላል። 23ከዚህ በኋላ 200 ዓመት ኖረ፤ ሌሎችን ወንዶች ልጆችና ሴቶች ልጆችን ወለደ።
24ናኮር 29 ዓመት ሲሆነው ታራን ወለደ፤ #11፥24 በዕብራይስጥ 29 ሲል በሰባ ሊቃናት 109 ይላል። 25ከዚህ በኋላ 119 ዓመት ኖረ፤ ሌሎችንም ወንዶች ልጆችና ሴቶች ልጆችን ወለደ። #11፥25 በዕብራይስጥ 119 ሲል በሰባ ሊቃናት 129 ይላል።
26ታራ 70 ዓመት ከሆነው በኋላ አብራምን፥ ናኮርንና ሃራንን ወለደ።
የታራ ዘሮች
27የአብራም፥ የናኮርና የሃራን አባት የነበረው የታራ ዘሮች የሚከተሉት ናቸው፤ ሃራን ሎጥን ወለደ፤ 28ሃራን አባቱ ታራ ገና በሕይወት ሳለ በተወለደባት ከተማ በኡር ሞተ፤ ኡር የምትገኘው በከለዳውያን ምድር ነበር። 29አብራም ሣራይን አገባ፤ ናኮር ደግሞ ሚልካን አገባ፤ እርስዋም ዪስካንን የወለደ የሃራን ልጅ ናት። 30ሣራይ መኻን በመሆንዋ ልጅ አልወለደችም ነበር።
31ታራ ልጁን አብራምን፥ ከሃራን የተወለደውን የልጅ ልጁን ሎጥን፥ የአብራም ሚስት የሆነችውን ምራቱን ሣራይን ይዞ በባቢሎን የምትገኘውን የኡርን ከተማ በመተው ወደ ከነዓን ምድር ለመሄድ ተነሣ፤ ወደ ካራን ዘልቀው እዚያ ተቀመጡ። 32ታራ 205 ዓመት ሲሆነው በካራን ሞተ።
Одоогоор Сонгогдсон:
ኦሪት ዘፍጥረት 11: አማ05
Тодруулга
Хуваалцах
Хувилах
Тодруулсан зүйлсээ бүх төхөөрөмждөө хадгалмаар байна уу? Бүртгүүлэх эсвэл нэвтэрнэ үү
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997