ኦሪት ዘፍጥረት 25
25
ሌሎች የአብርሃም ዘሮች
(1ዜ.መ. 1፥32-33)
1አብርሃም ቀጡራ የምትባል ሌላ ሚስት አገባ፤ 2እርስዋም ዚምራንን፥ ዮቅሻንን፥ መዳንን፥ ምድያምን፥ ዩሽባቅንና ሹሐን ወለደችለት። 3ዮቅሻንም ሳባንና ደዳንን ወለደ፤ የደዳንም ዘሮች አሹራውያን፥ ሌጡሻውያንና ሌኡማውያን ናቸው። 4የምድያምም ልጆች ዔፋ፥ ዔፈር፥ ሐኖክ፥ አቢዳዕና ኤልዳዓ ናቸው፤ እነዚህ ሁሉ የቀጡራ ዘሮች ናቸው።
5አብርሃም ያለውን ሀብት ሁሉ ለይስሐቅ አወረሰው፤ 6ከሌሎች ሴቶች ለተወለዱትም ልጆች ገና በሕይወት ሳለ ስጦታ ሰጣቸው፤ ከዚህ በኋላ እነዚህ ሌሎች ልጆች ከይስሐቅ ርቀው ወደ ምሥራቅ አገር እንዲሄዱ አደረጋቸው።
የአብርሃም መሞት
7የአብርሃም ዕድሜ በአጠቃላይ መቶ ሰባ አምስት ዓመት ነበር፤ 8በዚህም ዐይነት አብርሃም በቂ ዕድሜ አግኝቶ ካረጀ በኋላ ሞተ፤ 9ልጆቹ ይስሐቅና እስማኤል ማክፌላ በተባለ ዋሻ ቀበሩት፤ ይህም ዋሻ ከመምሬ በስተምሥራቅ በሒታዊው በጾሐር ልጅ በዔፍሮን እርሻ ውስጥ የሚገኘው ነው፤ 10እርሱም አብርሃም ከሒታውያን ላይ የገዛው የመቃብር ቦታ ነው፤ በዚህ ዐይነት አብርሃም ሚስቱ ሣራ በተቀበረችበት ዋሻ ተቀበረ። #ዘፍ. 23፥3-16። 11አብርሃም ከሞተ በኋላ ልጁን ይስሐቅን እግዚአብሔር ባረከው፤ ይስሐቅም “ብኤርላሐይ ሮኢ ወይም የሚያየኝ ሕያው አምላክ” ተብሎ በሚጠራው ኲሬ አጠገብ ይኖር ነበር።
የእስማኤል ዘሮች
(1ዜ.መ. 1፥28-31)
12የሣራ አገልጋይ ግብጻዊትዋ አጋር ለአብርሃም የወለደችለት እስማኤል፥ 13ከዚህ በታች በዕድሜአቸው ቅደም ተከተል ተራ የተዘረዘሩትን ልጆች ወለደ፤ እነርሱም፦ ነባዮት፥ ቄዳር፥ አድብኤል፥ ሚብሣም፥ 14ሚሽማዕ፥ ዱማ፥ ማሣ፥ 15ሐዳድ፥ ቴማ፥ ይጡር፥ ናፊሽ እና ቄድማ ናቸው። 16እነዚህ የእስማኤል ልጆች ለዐሥራ ሁለት ነገዶች ቅድመ አያቶች ነበሩ፤ ስማቸውም በኖሩባቸው ከተሞችና ስፍራዎች ሲጠራ ይኖራል። 17እስማኤል መቶ ሠላሳ ሰባት ዓመት ሲሆነው ሞተ፤ 18የእስማኤል ዘሮች ከግብጽ በስተምሥራቅ ወደ አሦር በምትወስደው መንገድ በሐዊላና በሹር መካከል ይኖሩ ነበር፤ የኖሩትም ከሌሎቹ የአብርሃም ዘሮች ጋር በጥላቻ ተራርቀው ነበር።
የዔሳውና የያዕቆብ መወለድ
19የአብርሃም ልጅ የይስሐቅ ታሪክ ይህ ነው፤ አብርሃም ይስሐቅን ወለደ። 20ይስሐቅ የባቱኤልን ልጅ ርብቃን ሲያገባ አርባ ዓመት ሆኖት ነበር፤ የርብቃ አባት ባቱኤልና ወንድምዋ ላባ በመስጴጦምያ የሚኖሩ ሶርያውያን ነበሩ፤ 21ርብቃ መኻን ስለ ነበረች ይስሐቅ ስለ እርስዋ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ፤ እግዚአብሔርም ጸሎቱን ስለ ሰማ ርብቃ ፀነሰች፤ 22የተፀነሱትም መንትያዎች ስለ ነበሩ እርስ በርሳቸው በማሕፀንዋ ውስጥ ይገፋፉ ነበር፤ እርስዋም “ይህን ዐይነት ነገር ለምን ደረሰብኝ?” በማለት ወደ እግዚአብሔር ለመጸለይ ተነሣሣች። 23እግዚአብሔርም፥
“በማሕፀንሽ ያሉት ሁለት ሕዝቦች ናቸው፤
እርስ በርሳቸው የማይስማሙ ሁለት ወገኖች ትወልጃለሽ፤
አንዱም ከሌላው የበረታ ይሆናል፤
ታላቁም ለታናሹ አገልጋይ ይሆናል” አላት። #ሮም 9፥12።
24የመውለጃዋም ሰዓት በደረሰ ጊዜ ሁለት ወንዶች ልጆች ወለደች። 25የመጀመሪያው ልጅ መልኩ ቀይ፥ ሰውነቱ ጠጒራም ነበር፤ ስለዚህ ዔሳው ተባለ። #25፥25 ዔሳው፦ በዕብራይስጥ “ጠጒራም” ማለት ሊሆን ይችላል። 26ሁለተኛው ልጅ ሲወለድ የዔሳውን ተረከዝ ይዞ በመውጣቱ ያዕቆብ ተባለ፤ ልጆቹ በተወለዱ ጊዜ ይስሐቅ ሥልሳ ዓመት ሆኖት ነበር። #25፥26 ያዕቆብ፦ በዕብራይስጥ “ተረከዝ የሚይዝ፥ አሰናካይ” ማለት ነው።
ዔሳው ብኲርናውን መሸጡ
27ሁለቱም ልጆች አደጉ፤ ዔሳው በዱር መዋል የሚወድ ብልኅ አዳኝ ሆነ፤ ያዕቆብ ግን በቤት መዋል የሚወድ ጭምት ሰው ነበር። 28ዔሳው እያደነ ሥጋ ያበላው ስለ ነበረ ይስሐቅ ዔሳውን ይወድ ነበር። ርብቃ ግን ያዕቆብን ትወድ ነበር።
29ከዕለታት አንድ ቀን ያዕቆብ ቀይ የምስር ወጥ በመሥራት ላይ እንዳለ ዔሳው ከአደን መጣ፤ በጣም እርቦት ነበር፤ 30ስለዚህም ያዕቆብን “ከዚህ ከቀይ ወጥ ስጠኝ” አለው። ኤዶም የተባለውም በዚህ ምክንያት ነበር። #25፥30 ኤዶም፦ “ቀይ” ማለት ሲሆን ዔሳው የተሠየመበት ስም ነው።
31ያዕቆብም “መጀመሪያ ብኲርናህን ሽጥልኝ” አለው።
32ዔሳውም “እኔ በራብ መሞቴ ነው፤ ታዲያ ብኲርና ምን ያደርግልኛል?” አለው።
33ያዕቆብም “እንግዲያውስ ብኲርናህን እንደምትሸጥልኝ መጀመሪያ ማልልኝ” አለው። ስለዚህ ዔሳው ምሎ ብኲርናውን ለያዕቆብ ሸጠ። #ዕብ. 12፥16።
34ከዚህ በኋላ ያዕቆብ የምስሩን ወጥ በእንጀራ አድርጎ ሰጠው፤ ዔሳውም ከበላና ከጠጣ በኋላ ተነሥቶ ሄደ፤ በዚህ ዐይነት ዔሳው ብኲርናውን በመናቅ አቃለላት።
Voafantina amin'izao fotoana izao:
ኦሪት ዘፍጥረት 25: አማ05
Asongadina
Hizara
Dika mitovy
Tianao hovoatahiry amin'ireo fitaovana ampiasainao rehetra ve ireo nasongadina? Hisoratra na Hiditra
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997