YouVersion logotips
Meklēt ikonu

ሉቃስ 23

23
1በዚያ የተሰበሰቡት በሙሉ ተነሥተው ኢየሱስን ወደ ጲላጦስ ወሰዱት፤ 2እንዲህም እያሉ ይከስሱት ጀመር፤ “ይህ ሰው ሕዝባችንን ሲያስት፣ ለቄሳር ግብር እንዳይከፈል ሲከለክል፣ ደግሞም፣ ‘እኔ ክርስቶስ#23፥2 ወይም መሲሕ፤ እንዲሁም 35 እና 39 ይመ ንጉሥ ነኝ’ ሲል አገኘነው።”
3ጲላጦስም፣ “አንተ የአይሁድ ንጉሥ ነህን?” ብሎ ጠየቀው።
ኢየሱስም፣ “አንተው አልህ” አለው።
4ጲላጦስም ለካህናት አለቆችና ለሕዝቡ፣ “እኔ በዚህ ሰው ላይ ምንም ወንጀል አላገኘሁበትም” አለ።
5እነርሱ ግን፣ “ይህ ሰው ከገሊላ ጀምሮ እዚህ ድረስ መላውን ይሁዳ ሳይቀር#23፥5 ወይም በመላው የአይሁድ ምድር እያወከ ነው” እያሉ አጽንተው ተናገሩ።
6ጲላጦስም ይህን ሲሰማ፣ ሰውየው የገሊላ ሰው መሆኑን ለማረጋገጥ ጠየቀ፤ 7ኢየሱስ ከሄድሮስ ግዛት የመጣ መሆኑን ጲላጦስ ባወቀ ጊዜ፣ ሄሮድስ በዚያን ወቅት በኢየሩሳሌም ስለ ነበረ ወደ እርሱ ላከው።
8ሄሮድስም ኢየሱስን ብዙ ጊዜ ሊያየው ይፈልግ ስለ ነበር፣ ባየው ጊዜ እጅግ ደስ አለው፤ ስለ እርሱ ሰምቶ ስለ ነበር፣ ታምራት ሲሠራ ለማየት ተስፋ ያደርግ ነበር። 9ብዙ ጥያቄዎችንም አቀረበለት፤ እርሱ ግን ምንም አልመለሰለትም። 10የካህናት አለቆችና ጸሐፍትም እዚያው ቆመው በብርቱ ይወነጅሉት ነበር። 11ሄሮድስም ከወታደሮቹ ጋር ናቀው፤ አፌዙበትም፤ የክብር ልብስ አልብሶም ወደ ጲላጦስ መልሶ ሰደደው። 12ሄሮድስና ጲላጦስም በዚሁ ዕለት ተወዳጁ፤ ቀደም ሲል ግን በመካከላቸው ጥል ነበረ።
13ጲላጦስም የካህናት አለቆችን፣ ገዥዎችንና ሕዝቡን በአንድነት ሰብስቦ፣ 14እንዲህ አላቸው፤ “ይህ ሰው ሕዝቡን ለዐመፅ ያነሣሣል ብላችሁ ወደ እኔ አምጥታችሁት ነበር፤ እኔም በእናንተው ፊት መርምሬው፣ ባቀረባችሁበት ክስ አንዳች ወንጀል አላገኘሁበትም። 15ደግሞም ሄሮድስ እንዲሁ ምንም ስላላገኘበት ወደ እኛ መልሶታል፤ እንደምታዩት ይህ ሰው ለሞት የሚያበቃ ምንም ነገር አልፈጸመም፤ 16ስለዚህ ቀጥቼ እፈታዋለሁ።” 17ይህን ያለው በበዓሉ አንድ እስረኛ እንዲፈታላቸው የግድ ያስፈልግ ስለ ነበረ ነው።#23፥17 አንዳንድ የጥንት ቅጆች ይህን ቍጥር አይጨምሩም።
18ሕዝቡም ሁሉ በአንድ ላይ፣ “ይህን ሰው ወዲያ አስወግደው! በርባንን ፍታልን!” እያሉ ጮኹ፤ 19በርባንም በከተማ ውስጥ የሕዝብ ዐመፅ በማነሣሣትና በነፍስ ግድያ የታሰረ ሰው ነበር።
20ጲላጦስም ኢየሱስን ሊፈታው ስለ ፈለገ፣ እንደ ገና ተናገራቸው፤ 21እነርሱ ግን፣ “ስቀለው! ስቀለው!” እያሉ ይጮኹ ነበር።
22ጲላጦስም ሦስተኛ ጊዜ፣ “ለምን? ይህ ሰው ምን የፈጸመው ወንጀል አለ? እኔ ለሞት የሚያበቃ ምንም በደል አላገኘሁበትም፤ ስለዚህ ቀጥቼ እፈታዋለሁ” አላቸው።
23እነርሱ ግን ድምፃቸውን ከፍ በማድረግ እንዲሰቀል አጥብቀው ለመኑት፤ ጩኸታቸውም በረታ። 24ስለዚህ ጲላጦስ የጠየቁት እንዲፈጸም ውሳኔ አስተላለፈ። 25የሕዝብ ዐመፅ በማነሣሣትና በነፍስ ግድያ ታስሮ የነበረውን፣ እንዲፈታላቸውም የለመኑትን ያን ሰው ፈታላቸው፤ ኢየሱስን ግን እንዳሻቸው እንዲያደርጉት አሳልፎ ሰጣቸው።
የኢየሱስ መስቀል
23፥33-43 ተጓ ምብ – ማቴ 27፥33-44ማር 15፥22-32ዮሐ 19፥17-24
26ኢየሱስንም ይዘው ሲወስዱት፣ ስምዖን የተባለውን የቀሬና ሰው ከገጠር ሲመጣ አግኝተው መስቀሉን አሸክመው ኢየሱስን ተከትሎ እንዲሄድ አስገደዱት። 27ብዙ ሕዝብና ደረታቸውን እየደቁ የሚያለቅሱለት ሴቶችም ከኋላው ይከተሉት ነበር። 28ኢየሱስ ግን ወደ እነርሱ ዘወር ብሎ እንዲህ አላቸው፤ “እናንት የኢየሩሳሌም ሴቶች፤ ለራሳችሁና ለልጆቻችሁ አልቅሱ እንጂ ለእኔ አታልቅሱ፤ 29እነሆ፤ ‘መካኖችና ያልወለዱ ማሕፀኖች፣ ያላጠቡ ጡቶችም ብፁዓን ናቸው’ የምትሉበት ጊዜ ይመጣልና። 30በዚያን ጊዜም፣
“ ‘ተራሮችን፣ “ውደቁብን!”
ኰረብቶችንም፣ “ሰውሩን!” ’ ይላሉ።
31 እንግዲህ በርጥብ ዕንጨት እንዲህ ካደረጉ፣ በደረቁ ምን ያደርጉ ይሆን?”
32ከእርሱ ጋር እንዲገደሉ ሌሎች ሁለት ወንጀለኞችን ወሰዷቸው። 33ቀራንዮ#23፥33 በግሪክ ቋንቋ የራስ ቅል ማለት ነው፤ በዕብራይስጥ ጎልጎታ ይባላል። የተባለ ቦታ በደረሱ ጊዜ ሰቀሉት፤ ወንጀለኞቹንም አንዱን በቀኙ፣ ሌላውን በግራው ሰቀሏቸው። 34ኢየሱስም፣ “አባት ሆይ፤ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው”#23፥34 አንዳንድ የጥንት ቅጆች፣ ይህ ዐረፍተ ነገር የላቸውም። አለ። እነርሱም ልብሱን በዕጣ ተከፋፈሉት።
35ሕዝቡም ቆመው ይመለከቱ ነበር። ገዦችም፣ “ሌሎችን አዳነ፤ በእግዚአብሔር የተመረጠው ክርስቶስ እርሱ ከሆነ፣ እስቲ ራሱን ያድን” እያሉ አፌዙበት።
36ወታደሮችም ቀርበው ያፌዙበት ነበር፤ የሖመጠጠ የወይን ጠጅ እየሰጡትም፣ 37“አንተ የአይሁድ ንጉሥ ከሆንህ፣ ራስህን አድን” ይሉት ነበር።
38ከራሱም በላይ፣ “ይህ የአይሁድ ንጉሥ ነው” የሚል ጽሑፍ ነበር።
39ከተሰቀሉት ወንጀለኞችም አንዱ እየተሳደበ፣ “አንተ ክርስቶስ አይደለህምን? እስቲ፣ ራስህንም እኛንም አድን” ይለው ነበር።
40ሌላኛው ወንጀለኛ ግን እንዲህ ሲል ገሠጸው፤ “ተመሳሳይ ፍርድ እየተቀበልህ ሳለህ፣ ከቶ እግዚአብሔርን አትፈራምን? 41እኛ ላደረግነው ነገር ቅጣት እየተቀበልን ስለሆነ፣ ተገቢ ፍርድ ላይ ነን፤ ይህ ሰው ግን አንዳች ክፉ ነገር አላደረገም።”
42ደግሞም፣ “ኢየሱስ ሆይ፤ በመንግሥትህ በመጣህ ጊዜ አስበኝ”#23፥42 አንዳንድ ቅጆች በንጉሥነት ሥልጣንህ ስትመጣ ይላሉ። አለው።
43ኢየሱስም፣ “እውነት እልሃለሁ፤ ዛሬ ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ” አለው።
የኢየሱስ መሞት
23፥44-49 ተጓ ምብ – ማቴ 27፥45-56ማር 15፥33-41
44ጊዜው ስድስት ሰዓት ያህል ነበር፤ እስከ ዘጠኝ ሰዓት ድረስም በምድር ሁሉ ላይ ጨለማ ሆነ፤ 45የፀሓይ ብርሃን ተከልክሏልና። የቤተ መቅደሱም መጋረጃ ተቀድዶ ለሁለት ተከፈለ። 46ኢየሱስም በታላቅ ድምፅ ጮኸ፣ “አባት ሆይ፤ መንፈሴን በእጅህ እሰጣለሁ” አለ፤ ይህንም ብሎ ሞተ።
47የመቶ አለቃውም የሆነውን ነገር ባየ ጊዜ፣ “ይህ ሰው በርግጥ ጻድቅ ነበር” ብሎ እግዚአብሔርን አመሰገነ። 48ይህንኑ ለማየት በስፍራው ተሰብስበው የነበሩ ሰዎችም ሁሉ የሆነውን ነገር በተመለከቱ ጊዜ ደረታቸውን እየደቁ ተመለሱ። 49ነገር ግን ኢየሱስን በቅርብ የሚያውቁት ሁሉ እንዲሁም ከገሊላ ጀምሮ የተከተሉት ሴቶች ይህን እየተመለከቱ ከሩቅ ቆመው ነበር።
የኢየሱስ መቀበር
23፥50-56 ተጓ ምብ – ማቴ 27፥57-61ማር 15፥42-47ዮሐ 19፥38-42
50የአይሁድ ሸንጎ አባል የሆነ፣ አንድ ዮሴፍ የሚባል በጎና ጻድቅ ሰው ነበር። 51ይህ ሰው በሸንጎው ምክርና ድርጊት አልተባበረም ነበር፤ እርሱም አርማትያስ የምትባል የአይሁድ ከተማ ሰው ሲሆን፣ የእግዚአብሔርን መንግሥት መምጣት ይጠባበቅ ነበር። 52ይህም ሰው ወደ ጲላጦስ ሄዶ የኢየሱስን ሥጋ ለመነው፤ 53በተፈቀደለትም ጊዜ፣ ሥጋውን አውርዶ በበፍታ ገነዘው፤ ከድንጋይ ተፈልፍሎ በተሠራና ገና ማንም ባልተቀበረበት መቃብር ውስጥ አስቀመጠው። 54ዕለቱ የመዘጋጃ ቀን ነበረ፤ ሰንበትም ሊገባ ነበር።
55ከገሊላ ጀምሮ ከኢየሱስ ጋር የመጡት ሴቶችም ተከትለው መቃብሩን አዩ፤ ሥጋውንም እንዴት እንዳስቀመጡት ተመለከቱ። 56ከዚያም ተመልሰው ሽቱና ቅባት አዘጋጁ፤ ሕጉ በሚያዝዘው መሠረት በሰንበት ቀን ዐረፉ።

Pašlaik izvēlēts:

ሉቃስ 23: NASV

Izceltais

Dalīties

Kopēt

None

Vai vēlies, lai tevis izceltie teksti tiktu saglabāti visās tavās ierīcēs? Reģistrējieties vai pierakstieties