ሉቃስ 24
24
የኢየሱስ ትንሣኤ
24፥1-10 ተጓ ምብ – ማቴ 28፥1-8፤ ማር 16፥1-8፤ ዮሐ 20፥1-8
1በሳምንቱ መጀመሪያ ቀን ሴቶቹ ያዘጋጁትን ሽቱ ይዘው እጅግ ማለዳ ሳለ ወደ መቃብሩ ሄዱ። 2ድንጋዩም ከመቃብሩ ደጃፍ ተንከባልሎ አገኙት፤ 3ወደ ውስጥ ዘልቀው በገቡ ጊዜ ግን የጌታ ኢየሱስን ሥጋ አላገኙም። 4በሁኔታው ግራ ተጋብተው ሳሉ፣ እነሆ፤ እጅግ የሚያንጸባርቅ ልብስ የለበሱ ሁለት ሰዎች ድንገት አጠገባቸው ቆሙ። 5ሴቶቹም ከመፍራታቸው የተነሣ ወደ ምድር አቀርቅረው ሳሉ፣ ሰዎቹ እንዲህ አሏቸው፤ “ሕያው የሆነውን እርሱን ለምን ከሙታን መካከል ትፈልጋላችሁ? 6እርሱ ተነሥቷል! እዚህ የለም፤ ደግሞም በገሊላ በነበረ ጊዜ ምን እንዳላችሁ አስታውሱ፤ 7‘የሰው ልጅ በኀጢአተኞች እጅ ዐልፎ ሊሰጥ፣ ሊሰቀልና በሦስተኛውም ቀን ሊነሣ ይገባል’ ብሎ ነበርና።” 8ሴቶቹም በዚህ ጊዜ ቃሉን አስታወሱ።
9ሴቶቹ ከመቃብሩ ስፍራ ተመልሰው ይህን ሁሉ ነገር ለዐሥራ አንዱና ለተቀሩት ሁሉ ነገሯቸው። 10ይህን ለሐዋርያት የነገሯቸውም፣ መግደላዊት ማርያም፣ ዮሐና፣ የያዕቆብ እናት ማርያምና ከእነርሱ ጋር የነበሩት ሌሎች ሴቶች ነበሩ። 11እነርሱ ግን ሴቶቹ የተናገሩት ቃል መቀባዠር ስለ መሰላቸው አላመኗቸውም። 12ጴጥሮስ ግን ተነሥቶ ወደ መቃብሩ ሮጠ፤ እዚያ ደርሶም ጐንበስ ብሎ ወደ ውስጥ ሲመለከት፣ በፍታው እንዳለ ለብቻው ተቀምጦ አየ፤ በሆነውም ነገር እየተገረመ ወደ ቤቱ ተመለሰ።
በኤማሁስ መንገድ ላይ
13በዚሁ ቀን ከደቀ መዛሙርት ሁለቱ፣ ከኢየሩሳሌም ዐሥራ አንድ ኪሎ ሜትር#24፥13 ግሪኩ ስድሳ ምዕራፍ ይላል። ያህል ወደሚርቅ፣ ኤማሁስ ወደሚባል መንደር ይሄዱ ነበር፤ 14እነርሱም ስለ ሆነው ነገር ሁሉ እርስ በርስ ይነጋገሩ ነበር። 15እየተነጋገሩና እየተወያዩ ሳሉም ኢየሱስ ራሱ ቀርቦ ከእነርሱ ጋር ይሄድ ጀመር፤ 16ነገር ግን እንዳያውቁት ዐይናቸው ተይዞ ነበር።
17እርሱም፣ “እየሄዳችሁ፣ መንገድ ላይ እርስ በርስ እንዲህ የምትወያዩት ምንድን ነው?” አላቸው።
እነርሱም በሐዘን ክው ብለው ቆሙ። 18ከእነርሱም አንዱ፣ ቀለዮጳ የተባለው፣ “በእነዚህ ቀናት እዚህ በኢየሩሳሌም የሆነውን ነገር የማታውቅ፣ አንተ ብቻ ለአገሩ እንግዳ ነህን?” ሲል መለሰለት።
19እርሱም፣ “የሆነው ነገር ምንድን ነው?” አላቸው።
እነርሱም እንዲህ አሉት፤ “በእግዚአብሔርና በሰው ሁሉ ፊት በተግባርና በቃል ብርቱ ነቢይ ስለ ነበረው ስለ ናዝሬቱ ኢየሱስ ነው፤ 20እርሱን የካህናት አለቆችና ገዦቻችን ለሞት ፍርድ አሳልፈው ሰጡት፤ ሰቀሉትም። 21እኛ ግን እስራኤልን ይቤዣል ብለን ተስፋ ያደረግነው እርሱን ነበር፤ ከሁሉም በላይ ደግሞ፣ ይህ ከሆነ ዛሬ ሦስተኛው ቀን ነው። 22ደግሞም ከእኛው መካከል አንዳንድ ሴቶች አስገረሙን፤ እነርሱም ማልደው ወደ መቃብሩ ሄደው ነበር፤ 23ሥጋውንም ባጡ ጊዜ መጥተው እርሱ በሕይወት እንዳለ የነገሯቸውን መላእክት በራእይ እንዳዩ አወሩልን። 24ከእኛም መካከል አንዳንዶች ወደ መቃብሩ ሄደው፣ ልክ ሴቶቹ እንዳሉት ሆኖ አገኙት፤ እርሱን ግን አላዩትም።”
25እርሱም እንዲህ አላቸው፤ “እናንተ የማታስተውሉ ሰዎች፣ ልባችሁም ነቢያት የተናገሩትን ሁሉ ከማመን የዘገየ፣ 26ክርስቶስ#24፥26 ወይም መሲሕ እንዲሁም 46 ይመ ይህን መከራ መቀበልና ወደ ክብሩም መግባት አይገባውምን?” 27ከሙሴና ከነቢያት ሁሉ ጀምሮ በቅዱሳት መጻሕፍት ስለ እርሱ የተጻፈውን አስረዳቸው።
28ወደሚሄዱበትም መንደር በተቃረቡ ጊዜ፣ ኢየሱስ ዐልፎ የሚሄድ መሰለ። 29እነርሱ ግን፣ “ምሽት እየተቃረበ፣ ቀኑም እየተገባደደ ስለሆነ ከእኛ ጋር ዕደር” ብለው አጥብቀው ለመኑት፤ ስለዚህ ከእነርሱ ጋር ለማደር ገባ።
30አብሯቸውም በማእድ በተቀመጠ ጊዜ፣ እንጀራውን አንሥቶ ባረከ፤ ቈርሶም ሰጣቸው። 31በዚህ ጊዜ ዐይናቸው ተከፈተ፤ ዐወቁትም፤ እርሱም ከእነርሱ ተሰወረ። 32እነርሱም፣ “በመንገድ ሳለን፣ እያነጋገረን ቅዱሳት መጻሕፍትንም ገልጦ ሲያስረዳን፣ ልባችን ይቃጠልብን አልነበረምን?” ተባባሉ።
33በዚያኑም ሰዓት ተነሥተው ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ፤ ዐሥራ አንዱና ከእነርሱ ጋር የነበሩትም በዚያ በአንድነት ተሰብስበው አገኟቸው፤ 34“እነርሱም ጌታ በርግጥ ተነሥቷል! ለስምዖንም ታይቷል” ይባባሉ ነበር። 35ሁለቱ ደቀ መዛሙርትም በመንገድ ላይ የሆነውንና ኢየሱስ እንጀራውን በቈረሰ ጊዜ እንዴት እንዳወቁት ተረኩላቸው።
ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርት ተገለጠ
36ይህን እየተነጋገሩ ሳሉ፣ ኢየሱስ ራሱ በመካከላቸው ቆሞ፣ “ሰላም ለእናንተ ይሁን” አላቸው።
37እነርሱ ግን ደንግጠው በፍርሀት ተዋጡ፤ መንፈስም ያዩ መሰላቸው። 38እርሱም እንዲህ አላቸው፤ “ለምን ትጨነቃላችሁ? ለምንስ ጥርጣሬ በልባችሁ ይገባል? 39እጆቼንና እግሮቼን ተመልከቱ፤ እኔው ራሴ ነኝ። ደግሞም ንኩኝና እዩ፤ በእኔ እንደምታዩት መንፈስ ሥጋና ዐጥንት የለውምና።”
40ይህንም ብሎ እጆቹንና እግሮቹን አሳያቸው። 41እነርሱም ከመደሰትና ከመገረም የተነሣ ገና ሳያምኑ፣ “በዚያ ቦታ አንዳች የሚበላ ነገር አላችሁን?” አላቸው። 42እነርሱም ከተጠበሰ ዓሣ አንድ ቍራሽ ሰጡት፤ 43እርሱም ተቀብሎ በፊታቸው በላ።
44እርሱም፣ “ከእናንተ ጋር በነበርሁበት ጊዜ፣ ‘በሙሴ ሕግ፣ በነቢያትና በመዝሙር መጻሕፍት ስለ እኔ የተጻፈው ሁሉ ይፈጸም ዘንድ ይገባል’ ብዬ የነገርኋችሁ ቃሌ ይህ ነው” አላቸው።
45በዚህ ጊዜ ቅዱሳት መጻሕፍትን እንዲያስተውሉ አእምሯቸውን ከፈተላቸው፤ 46እንዲህም አላቸው፤ “ ‘እንዲህ ተብሎ ተጽፏል፤ ክርስቶስ መከራን ይቀበላል፤ በሦስተኛውም ቀን ከሙታን ይነሣል፤ 47ከኢየሩሳሌም ጀምሮ ለሕዝቦች ሁሉ ንስሓና የኀጢአት ስርየት በስሙ ይሰበካል፤’ 48እናንተም ለዚህ ምስክሮች ናችሁ። 49እኔም አባቴ የሰጠውን ተስፋ እልክላችኋለሁ፤ እናንተ ግን ከላይ ኀይል እስክትለብሱ ድረስ በኢየሩሳሌም ከተማ ቈዩ።”
የኢየሱስ ዕርገት
50ከዚህ በኋላ እስከ ቢታንያ ይዟቸው ወጣ፤ እጆቹንም አንሥቶ ባረካቸው። 51እየባረካቸውም ሳለ፣ ከእነርሱ ተለይቶ ወደ ሰማይ ዐረገ። 52እነርሱም ሰገዱለት፤ በታላቅ ደስታም ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ፤ 53እግዚአብሔርንም እያመሰገኑ ዘወትር በቤተ መቅደስ ነበሩ።
Šiuo metu pasirinkta:
ሉቃስ 24: NASV
Paryškinti
Dalintis
Kopijuoti
Norite, kad paryškinimai būtų įrašyti visuose jūsų įrenginiuose? Prisijunkite arba registruokitės
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጅ መብት © 2001 በ Biblica, Inc.
ፈቃድ የተገኘባቸው ናቸው። መብቱ በመላው ዓለም በሕግ የተጠበቀ።
Holy Bible, New Amharic Standard Version™ (Addisu Medebegna Tirgum™)
Copyright © 2001 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.