ኦሪት ዘፍጥረት 3

3
የሰው አለመታዘዝ
1እግዚአብሔር አምላክ ከፈጠራቸው አራዊት ሁሉ፥ እባብ እጅግ ተንኰለኛ ነበረ፤ ስለዚህ እባብ “በአትክልቱ ቦታ ካሉት ዛፎች ሁሉ ፍሬ እንዳትበሉ በእርግጥ እግዚአብሔር አዞአችኋልን?” ሲል ሴቲቱን ጠየቃት። #ራዕ. 12፥9፤ 20፥2።
2ሴቲቱም “በአትክልት ቦታ ካሉት ዛፎች ፍሬ ልንበላ እንችላለን፤ 3ነገር ግን እግዚአብሔር ‘በአትክልቱ ቦታ መካከል ካለው ዛፍ ፍሬ አትብሉ፤ በእጃችሁም አትንኩት፤ ይህን ብታደርጉ ትሞታላችሁ’ ብሎ አስጠንቅቆናል” ስትል መለሰችለት።
4እባቡም እንዲህ አላት፦ “በፍጹም አትሞቱም፤ 5እግዚአብሔር ይህን ያዘዛችሁ ከዚያ ዛፍ ፍሬ በበላችሁ ጊዜ እንደ እግዚአብሔር እንደምትሆኑና ደጉን ከክፉ ለይታችሁ እንደምታውቁ ስለሚያውቅ ነው”፤
6ሴቲቱም ዛፉ የሚያምር፥ ፍሬውም ለመብላት የሚያስጐመዥና ጥበብን የሚያስገኝ እንደ ሆነ ባየች ጊዜ ከፍሬው ወስዳ በላች፤ ለባሏም ከፍሬው ሰጠችው፤ እርሱም በላ። 7የሁለቱም ዐይኖች ተከፍተው እራቁታቸውን እንደ ሆኑ ተገነዘቡ፤ ስለዚህ የበለስ ቅጠሎችን አገናኝተው ሰፉና በማገልደም እርቃናቸውን ሸፈኑ። #3፥7 በለስ፦ በኢትዮጵያ በአንዳንድ ቦታ እንደሚታወቀው “ሾላን” የሚመስል ቅጠሉ እሾኽ የሌለው፥ ፍሬው ጣፋጭ የሆነ ዛፍ ነው።
8በመሸ ጊዜ፥ እግዚአብሔር አምላክ በአትክልቱ ቦታ ውስጥ ሲመላለስ ድምፁን ሰሙ፤ አዳምና ሚስቱ እግዚአብሔር አምላክ እንዳያያቸው በዛፎች መካከል ተደበቁ። 9ነገር ግን እግዚአብሔር አምላክ አዳምን ጠርቶ “የት ነው ያለኸው?” ሲል ጠየቀው።
10አዳምም “በአትክልቱ ቦታ ውስጥ የአንተን ድምፅ ሰማሁ፤ እራቁቴንም ስለ ሆንኩ በመፍራት ተደበቅሁ” አለ።
11እግዚአብሔርም “እራቁትህን እንደ ሆንክ ማን ነገረህ? አትብላ ካልኩህ ዛፍ ፍሬ ወስደህ በላህን?” አለው።
12አዳምም “ይህች አብራኝ እንድትኖር የሰጠኸኝ ሴት ፍሬውን ከዛፉ ወስዳ ሰጠችኝና በላሁ” አለ።
13እግዚአብሔር አምላክም ሴቲቱን “ይህ ያደረግሽው ምንድን ነው?” ብሎ ጠየቃት።
እርስዋም “እባብ አታለለኝና በላሁ” አለች። #2ቆሮ. 11፥3፤ 1ጢሞ. 2፥14።
የእግዚአብሔር ፍርድ
14ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር አምላክ እባቡን እንዲህ አለው፦
“ይህን በማድረግህ ከእንስሶችና ከአራዊት ሁሉ ተለይተህ የተረገምክ ሁን፤
ከዛሬ ጀምሮ በደረትህ እየተሳብክ ሂድ፤
ዕድሜህን ሙሉ ዐፈር ብላ፤
15በአንተና በሴቲቱ መካከል፥ በአንተ ዘርና በእርስዋ ዘር መካከል ጠላትነት እንዲኖር አደርጋለሁ።
የእርስዋ ዘር የአንተን ራስ ይቀጠቅጣል፤
አንተም የእርስዋን ዘር ተረከዝ ትነክሳለህ።” #ራዕ. 12፥17።
16ሴቲቱንም፥
“በእርግዝናሽ ወራት ጭንቀትሽን፥
በምትወልጂበትም ጊዜ የምጥ ሥቃይሽን አበዛሁ፤
ይህም ሁሉ ሆኖ ፍላጎትሽ ለባልሽ ይሆናል።
ለእርሱም ታዛዥ ትሆኚአለሽ” አላት።
17አዳምንም እንዲህ አለው፥
“የሚስትህን ቃል ሰምተህ ‘አትብላ’ ያልኩህን ፍሬ ከዛፉ ወስደህ ስለ በላህ፥
አንተ በፈጸምከው ክፉ ሥራ ምክንያት ምድር የተረገመች ትሁን፤
በሕይወት ዘመንህ ሁሉ ምግብህን ከእርስዋ የምትበላው
በብርቱ ድካም ነው።
18ምድር እሾኽና አሜከላ ታበቅላለች፤
አንተም የዱር ተክሎችን ትበላለህ። #ዕብ. 6፥8።
19ወደ መጣህበት ወደ መሬት እስክትመለስ ድረስ፥
እንጀራህን በግንባርህ ላብ ትበላለህ።”
ዐፈር ነህና፥
ወደ ዐፈርም ትመለሳለህ።
20አዳምም ሚስቱ ሕይወት ላላቸው ሰብአዊ ፍጡሮች ሁሉ እናት ስለ ሆነች “ሔዋን” የሚል ስም አወጣላት። 21እግዚአብሔር አምላክም ለአዳምና ለሔዋን ከቆዳ ልብስ ሠርቶ አለበሳቸው።
የአዳምና የሔዋን ከገነት መባረር
22እግዚአብሔር አምላክም እንዲህ አለ፦ “እነሆ፥ አዳም ክፉንና ደግን በማወቅ ከእኛ እንደ አንዱ ሆነ፤ አሁንም እጁን ዘርግቶ ከሕይወት ዛፍ ወስዶ በመብላት ለዘለዓለም እንዲኖር አይገባውም።” #ራዕ. 22፥14። 23በዚህ ምክንያት እግዚአብሔር አምላክ አዳምን ከዔደን የአትክልት ቦታ አስወጣው፤ የተገኘበትንም ምድር እንዲያለማ አደረገው። 24አዳምንም ካስወጣው በኋላ ከዔደን የአትክልት ቦታ በስተ ምሥራቅ በኩል ኪሩቤል የተባሉትን መላእክትንና በየአቅጣጫው እየተገለባበጠ እንደ እሳት የሚንበለበለውን ሰይፍ አኖረ፤ ይህንንም ያደረገው ማንም ወደ ሕይወት ዛፍ እንዳይጠጋ ነው።

ទើបបានជ្រើសរើសហើយ៖

ኦሪት ዘፍጥረት 3: አማ05

គំនូស​ចំណាំ

ចែក​រំលែក

ចម្លង

None

ចង់ឱ្យគំនូសពណ៌ដែលបានរក្សាទុករបស់អ្នក មាននៅលើគ្រប់ឧបករណ៍ទាំងអស់មែនទេ? ចុះឈ្មោះប្រើ ឬចុះឈ្មោះចូល