ኦሪት ዘፍጥረት 2

2
1የሰማይና የምድር፥ በውስጣቸው ያሉትም ነገሮች ሁሉ አፈጣጠር በዚህ ሁኔታ ተፈጸመ።
2እግዚአብሔር ሥራውን ሁሉ ፈጽሞ በሰባተኛው ቀን ዐረፈ። #ዕብ. 4፥4፤10። 3እግዚአብሔር የመፍጠር ሥራውን ሁሉ ፈጽሞ ያረፈው በዚህ ቀን ስለ ሆነ፥ ሰባተኛውን ቀን ባረከው፤ ቀደሰውም። #ዘፀ. 20፥11። 4የሰማይና የምድር አፈጣጠር እንዲህ ነበር። እግዚአብሔር አምላክ ሰማይንና ምድርን በፈጠረ ጊዜ፥ 5ዝናብን ባለማዝነቡና ምድርንም የሚያለማ ሰው ባለመኖሩ፥ በምድር ላይ ምንም ዐይነት ተክል አልነበረም፤ ምንም ዐይነት ቡቃያ አልበቀለም። 6ይሁን እንጂ፥ ከምድር ውስጥ ምንጭ ፈልቆ የብሱን ሁሉ ያጠጣ ነበር።
አዳምና ሔዋን በዔደን ገነት
7ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር አምላክ ከመሬት ዐፈር ወስዶ፥ ሰውን ከዐፈር አበጀው፤ በአፍንጫውም ሕይወትን የሚሰጥ እስትንፋስ “እፍ” አለበት፤ ሰውም ሕያው ነፍስ ያለው ፍጡር ሆነ። #1ቆሮ. 15፥45።
8እግዚአብሔር አምላክ በስተምሥራቅ በኩል በዔደን የአትክልት ቦታን አዘጋጀ፤ የፈጠረውንም ሰው በዚያ እንዲኖር አደረገው። 9በዚያም ለዐይን የሚያስደስቱና ለምግብነት የሚጠቅሙ ልዩ ልዩ ዛፎች እንዲበቅሉ አደረገ፤ ደግሞም በአትክልቱ ቦታ መካከል ሕይወት የሚሰጥ ዛፍ ነበረ፤ እንዲሁም ደጉን ከክፉ ለመለየት የሚያስችል ዕውቀት የሚሰጥ ሌላ ዛፍ ነበረ። #ራዕ. 2፥7፤ 22፥2፤14።
10የአትክልት ቦታውን የሚያጠጣ ወንዝ ከዔደን ይፈስ ነበር፤ ይህም ወንዝ ከዔደን ከወጣ በኋላ በአራት ወንዞች ይከፈላል። 11የመጀመሪያው ወንዝ ፊሶን ይባላል፤ እርሱም ወርቅ በሚገኝበት ሐዊላ በሚባለው ምድር ሁሉ ላይ ይፈስሳል፤ 12የዚያ አገር ወርቅ ንጹሕ ነበር፤ በተጨማሪም በዚያ አገር ውድ የሆነ ሽቶና የከበሩ ድንጋዮች ይገኛሉ። 13ሁለተኛው ወንዝ ግዮን ይባላል፤ እርሱም ኢትዮጵያ በምትባል አገር ዙሪያ ይፈስሳል። 14ሦስተኛው ወንዝ ጤግሮስ ይባላል፤ እርሱም በአሦር በስተምሥራቅ ይፈስሳል፤ አራተኛው ወንዝ ኤፍራጥስ ይባላል።
15ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር አምላክ ሰውን በዔደን የአትክልት ቦታ አኖረው፤ ይህንንም ያደረገው ሰው የአትክልቱን ቦታ እንዲያለማና እንዲንከባከበው ነው። 16እግዚአብሔር አምላክ ሰውን እንዲህ ብሎ አዘዘው፦ “በአትክልቱ ቦታ ከሚገኙት ዛፎች ሁሉ ፍሬ ልትበላ ትችላለህ፤ 17ነገር ግን ከእርሱ በበላህበት ቀን በእርግጥ ስለምትሞት ደጉን ከክፉ ለመለየት የሚያስችል ዕውቀት ከሚሰጠው ዛፍ ፍሬ አትብላ።”
18ቀጥሎም እግዚአብሔር አምላክ “ሰው ብቻውን መኖሩ መልካም አይደለም፤ ስለዚህ ረዳት ጓደኛ እፈጥርለታለሁ” አለ።
19እግዚአብሔር አምላክ ከምድር ዐፈር ወስዶ እንስሶችንና ወፎችን ሁሉ ፈጠረ፤ ምን ዐይነት ስም እንደሚያወጣላቸው ለማየት ወደ አዳም አመጣቸው፤ አዳም ለእያንዳንዱ ሕያው ፍጡር ያወጣለት ስም መጠሪያው ሆነ። 20በዚህ ዐይነት አዳም ለወፎቹና ለእንስሶቹ ሁሉ ስም አወጣላቸው፤ ለእርሱ ግን ረዳት ጓደኛ አልተገኘለትም ነበር።
21ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር አምላክ አዳምን ከባድ እንቅልፍ እንዲወስደው አደረገ፤ አንቀላፍቶም ሳለ ከጐኑ አጥንቶች አንዱን ወሰደና ባዶውን ቦታ በሥጋ ሞላው፤ 22እግዚአብሔር አምላክ ከአዳም ጐን የወሰዳትን አጥንት ሴት አድርጎ ሠራት፤ ወደ አዳምም አመጣት። 23አዳምም፥
“እነሆ በመጨረሻ
እርስዋ ከአጥንቶቼ የተገኘች አጥንት ናት፤
ከሥጋዬም የተገኘች ሥጋ ናት፤
ከወንድ የተገኘች ስለ ሆነች ‘ሴት’ ትባል” አለ። #2፥23 በዕብራይስጥ “ኢሽ” ማለት ወንድ ሲሆን “ኢሻ” ማለት ሴት ነች።
24ስለዚህ ወንድ አባቱንና እናቱን ትቶ ከሚስቱ ጋር ይተባበራል፤ ሁለቱም አንድ አካል ይሆናሉ። #ማቴ. 19፥5፤ ማር. 10፥7-8፤ 1ቆሮ. 6፥16፤ ኤፌ. 5፥31።
25አዳምና ሚስቱ ራቊታቸውን ነበሩ፤ ይሁን እንጂ አያፍሩም ነበር።

ទើបបានជ្រើសរើសហើយ៖

ኦሪት ዘፍጥረት 2: አማ05

គំនូស​ចំណាំ

ចែក​រំលែក

ចម្លង

None

ចង់ឱ្យគំនូសពណ៌ដែលបានរក្សាទុករបស់អ្នក មាននៅលើគ្រប់ឧបករណ៍ទាំងអស់មែនទេ? ចុះឈ្មោះប្រើ ឬចុះឈ្មោះចូល