ኦሪት ዘፍጥረት 12
12
እግዚአብሔር አብራምን እንደ ጠራው
1እግዚአብሔርም አብራምን አለው፥ “ከሀገርህ፥ ከዘመዶችህም፥ ከአባትህም ቤት ተለይተህ ውጣ፤ እኔ ወደማሳይህም ምድር ሂድ። 2ታላቅ ሕዝብም አደርግሃለሁ፤ እባርክሃለሁ፤ ስምህንም ከፍ ከፍ አደርጋለሁ፤ ቡሩክም ትሆናለህ፤ የሚባርኩህንም እባርካለሁ፤ 3የሚረግሙህንም እረግማለሁ፤ የምድር ነገዶችም ሁሉ በአንተ ይባረካሉ።” 4አብራምም እግዚአብሔር እንደ ነገረው ሄደ፤ ሎጥም ከእርሱ ጋር ሄደ፤ አብራምም ከካራን በወጣ ጊዜ ሰባ አምስት ዓመት ሆኖት ነበረ። 5አብራምም ሚስቱን ሦራንና የወንድሙን ልጅ ሎጥን፥ ያገኙትን ከብት ሁሉና በካራን ያገኙአቸውን ሰዎች ይዞ ወደ ከነዓን ምድር ለመሄድ ወጣ፤ ወደ ከነዓንም ምድር ገቡ። 6አብራምም እስከ ሴኬም ስፍራ እስከ ታላቁ ዛፍ#ዕብ. “እስከ ታላቁ የሞሬ ዛፍ” ይላል። ድረስ በዚያች ምድር አለፈ፤ የከነዓን ሰዎችም በዚያን ጊዜ በዚያች ምድር ነበሩ። 7እግዚአብሔርም ለአብራም ተገለጠለትና፥ “ይህችን ምድር ለዘርህ እሰጣለሁ” አለው። አብራምም ለእርሱ ለተገለጠለት ለእግዚአብሔር በዚያ መሠውያን ሠራ። 8ከዚያም በቤቴል ምሥራቅ ወዳለው ተራራ ወጣ፤ በዚያም ቤቴልን ወደ ምዕራብ፥ ጋይን ወደ ምሥራቅ አድርጎ ድንኳኑን ተከለ፤ በዚያም ለእግዚአብሔር መሠውያን ሠራ፤ የእግዚአብሔርንም ስም ጠራ። 9አብራምም ከዚያ ተነሣ፤ እየተጓዘም ወደ አዜብ ሄደ፤ በዚያም ኖረ።
የአብራም እንግድነት በግብፅ
10በምድርም ራብ ሆነ፤ አብራምም በዚያ በእንግድነት ይቀመጥ ዘንድ ወደ ግብፅ ወረደ፤ በምድር ራብ ጠንቶ ነበረና። 11እንዲህም ሆነ፤ አብራም ወደ ግብፅ ለመግባት በቀረበ ጊዜ ሚስቱን ሦራን እንዲህ አላት፥ “አንቺ መልከ መልካም ሴት እንደ ሆንሽ እነሆ እኔ አውቃለሁ፤ 12የግብፅ ሰዎች ያዩሽ እንደ ሆነ ሚስቱ ናት ይላሉ፤ እኔንም ይገድሉኛል፤ አንቺንም በሕይወት ይተዉሻል። 13እንግዲህ በአንቺ ምክንያት መልካም ይሆንልኝ ዘንድ፥ ስለ አንቺም ነፍሴ ትድን ዘንድ እኅቱ ነኝ በዪ።” 14እንዲህም ሆነ፤ አብራም ወደ ግብፅ በገባ ጊዜ የግብፅ ሰዎች ሴቲቱን እጅግ ውብ እንደ ሆነች አዩ፤ 15የፈርዖንም አለቆች አዩአት፤ በፈርዖንም ፊት አደነቁአት፤ ወደ ፈርዖን ቤትም ወሰዱአት። 16ለአብራምም ስለ እርስዋ መልካም አደረጉለት፤ ለእርሱ በጎችም፥ በሬዎችም፥ አህዮችም፥ በቅሎዎችም፥#“በቅሎዎችም” በዕብ. የለም። ወንዶችና ሴቶች ባሪያዎችም፥ ግመሎችም ነበሩት። 17እግዚአብሔርም በአብራም ሚስት በሦራ ምክንያት ፈርዖንንና የቤቱን ሰዎች በታላቅ መቅሠፍት መታ። 18ፈርዖንም አብራምን ጠርቶ አለው፥ “ይህ ያደረግህብኝ ምንድን ነው? እርስዋ ሚስትህ እንደ ሆነች ለምን አልገለጥህልኝም? 19ለምንስ ‘እኅቴ ናት’ አልህ? ለእኔ ሚስት ትሆነኝ ዘንድ ወስጃት ነበር። አሁንም እነኋት፥ ሚስትህ በፊትህ ናት፤ ይዘሃትም ሂድ።” 20ፈርዖንም ሰዎቹን ስለ አብራም አዘዘ፤ እርሱንም፥ ሚስቱንም፥ የነበረውንም#ግሪክ ሰባ. ሊ. “ሎጥንም” ይላል። ሁሉ ሸኙአቸው።
Արդեն Ընտրված.
ኦሪት ዘፍጥረት 12: አማ2000
Ընդգծել
Կիսվել
Պատճենել
Ցանկանու՞մ եք պահպանել ձեր նշումները ձեր բոլոր սարքերում: Գրանցվեք կամ մուտք գործեք