የሉቃስ ወንጌል 19
19
ስለ ቀራጩ ዘኬዎስ
1ጌታችን ኢየሱስም ወደ ኢያሪኮ ገብቶ በዚያ ያልፍ ነበር። 2እነሆ፥ የቀራጮች አለቃ ስሙ ዘኬዎስ የተባለ አንድ ሰው ነበር፤ እርሱም ባለጸጋ ነበር። 3ጌታችን ኢየሱስንም ያየው ዘንድ፥ ማን እንደ ሆነም ያውቅ ዘንድ ይሻ ነበር፤ የሰው ብዛትም ይከለክለው ነበር፤ ቁመቱ አጭር ነበርና። 4ወደ ፊቱም ሮጠ፤ ያየው ዘንድም በሾላ ላይ ወጣ፤ በዚያች መንገድ ያልፍ ዘንድ አለውና። 5ጌታችን ኢየሱስም ወደዚያ በደረሰ ጊዜ አሻቅቦ አየውና፥ “ዘኬዎስ ሆይ፥ ፈጥነህ ውረድ፤ ዛሬ በቤትህ እውል ዘንድ አለኝና” አለው። 6ፈጥኖም ወረደ፤ ደስ እያለውም ወደ ቤቱ ይዞት ገባ። 7ሁሉም አይተው “ወደ ኀጢኣተኛ ሰው ቤት ሊውል ገባ” ብለው አንጐራጐሩ። 8ዘኬዎስም ቆመና ጌታችንን እንዲህ አለው፥ “ጌታዬ ሆይ፥ አሁን የገንዘቤን እኩሌታ ለነዳያን እሰጣለሁ፤ የበደልሁትም ቢኖር ስለ አንድ ፋንታ አራት እጥፍ እከፍለዋለሁ።” 9ጌታችን ኢየሱስም እንዲህ አለው፥ “ዛሬ ለዚህ ቤት ሕይወት ሆነ፤ እርሱ የአብርሃም ልጅ ነውና። 10#ማቴ. 18፥11። የሰው ልጅ የጠፋውን ሊፈልግና ሊያድን መጥቶአልና።”
ዐሥር ምናን ስለ ተቀበሉት ሰዎች ምሳሌ
11 #
ማቴ. 25፥14-30። ይህንም ሲሰሙ፤ ምሳሌ መስሎ ነገራቸው፤ ወደ ኢየሩሳሌም ቀርቦ ነበርና፤ እነርሱም የእግዚአብሔር መንግሥት ወዲያውኑ የምትገለጥ መስሎአቸው ነበርና። 12እንዲህም አለ፥ “አንድ የከበረ ሰው መንግሥት ይዞ ሊመለስ ወደ ሩቅ ሀገር ሄደ። 13ዐሥሩን አገልጋዮቹንም ጠርቶ ዐሥር ምናን ሰጣቸውና፦ እንግዲህ እስክመለስ ድረስ ነግዱ አላቸው። 14የሀገሩ ሰዎች ግን ይጠሉት ነበርና፥ ይህ በእኛ ላይ ሊነግሥ አንሻም ብለው አከታትለው መልእክተኞችን ላኩ። 15ከዚህም በኋላ፤ መንግሥትን ይዞ በተመለሰ ጊዜ እንደ አተረፉ ያውቅ ዘንድ ምናን የሰጣቸውን ብላቴኖቹን እንዲያመጡአቸው አዘዘ። 16አንደኛውም መጥቶ፦ አቤቱ፥ ምናንህ ዐሥር ነበር፤ እነሆ ዐሥር ምናን አትርፌአለሁ አለው። 17ጌታውም፦ መልካም፥ አንተ በጎ አገልጋይ በጥቂት የታመንህ ስለሆንህ በብዙ ላይ እሾምሃለሁ፤#“በብዙ ላይ እሾምሃለሁ” የሚለው በግሪኩ የለም። በዐሥሩ ከተሞች ላይ ተሾም አለው። 18ሁለተኛውም መጥቶ፦ አቤቱ፥ ምናንህ አምስት ነበር፤#“ምናንህ አምስት ነበር” የሚለው በግሪኩ የለም። አምስት አትርፌአለሁ አለው። 19እርሱንም፦ አንተም በአምስት ከተሞች ተሾም አለው። 20ሦስተኛውም መጥቶ እንዲህ አለው፦ አቤቱ፥ በእኔ ዘንድ የነበረቺው ምናንህ እነኋት፤ በጨርቅ ጠቅልዬ አኑሬአት ነበር። 21አንተ ያላኖርኸውን የምትወስድ፥ ያልዘራኸውን የምታጭድ፥ ያልበተንኸውንም የምትሰበስብ#“ያልበተንኸውን የምትሰበስብ” የሚለው በግሪኩ የለም። ጨካኝ ሰው እንደ ሆንህ ስለማውቅህ ፈርቼሃለሁና። 22ጌታውም እንዲህ አለው፦ አንተ ክፉ ሰነፍ አገልጋይ፥ እኔ ያላስቀመጥሁትን የምወስድ፥ ያልዘራሁትን የማጭድ፥ ያልበተንሁትንም የምሰበስብ ጨካኝ ሰው እንደ ሆንሁ ታውቃለህን? እንደ ቃልህ እፈርድብሃለሁ። 23ለምን ገንዘቤን ወደ ለዋጮች አላስገባህም? እኔም መጥቼ ከትርፉ ጋር በወሰድሁት ነበር። 24ከዚያ የቆሙትንም፦ ይህን ምናን ከእርሱ ተቀብላችሁ ዐሥር ምናን ላለው ስጡት አላቸው። 25እነርሱም አቤቱ፥ ዐሥር ምናን ያለው አይደለምን? አሉት። 26#ማቴ. 13፥12፤ ማር. 4፥25፤ ሉቃ. 8፥18። እርሱም እንዲህ አላቸው፦ ላለው ሁሉ ይሰጡታል፤ ይጨምሩለታልም፤ የሌለውን ግን ያን ያለውንም ቢሆን ይወስዱበታል። 27ነገር ግን እነዚያን ልነግሥባቸው ያልወደዱትን ጠላቶችን ወደዚህ አምጡና በፊቴ ውጉአቸው።”
ወደ ኢየሩሳሌም ስለ መግባቱ
28ይህንም ተናግሮ ወደ ፊት ሄደ፤ ወደ ኢየሩሳሌምም ወጣ። 29ደብረ ዘይት ወደሚባል ተራራ አጠገብ ወዳሉት ወደ ቤተ ፋጌና ወደ ቢታንያ በቀረበ ጊዜ፥ ከደቀ መዛሙርቱ ሁለቱን ላከ። 30እንዲህም አላቸው፥ “በፊታችሁ ወደ አለችው መንደር ሂዱ፤ ገብታችሁም ሰው ያልተቀመጠበት የታሰረ ውርንጫ ታገኛላችሁ፤ ፈትታችሁም አምጡልኝ። 31ለምን ትፈቱታላችሁ? የሚላችሁ ቢኖር ጌታው ይሻዋል በሉ።” 32የተላኩትም ሄደው እንደ አላቸው አገኙ። 33ውርንጫውንም ሲፈቱ ባለቤቶቹ “ውርንጫውን ለምን ትፈቱታላችሁ?” አሉአቸው። 34እነርሱም “ጌታው ይሻዋል” አሉ። 35ይዘውም ወደ ጌታችን ኢየሱስ ወሰዱት፤ በውርንጫው ላይም ልብሳቸውን ጭነው ጌታችን ኢየሱስን በዚያ ላይ አስቀመጡት። 36ሲሄዱም በመንገድ ልብሳቸውን አነጠፉ። 37ወደ ደብረ ዘይት ዐቀበት መውረጃም በደረሱ ጊዜ፥ ደቀ መዛሙርቱ በሙሉ ስለ አዩት ኀይል ሁሉ ደስ ይላቸውና እግዚአብሔርን በታላቅ ቃል ያመሰግኑት ዘንድ ጀመሩ። 38#መዝ. 117፥26። እንዲህ እያሉ፥ “በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ ቡሩክ ነው፤ የእስራኤል ንጉሥ ቡሩክ ነው፤#“የእስራኤል ንጉሥ ቡሩክ ነው” የሚለው በግሪኩ የለም። ሰላም በምድር፥ በአርያምም ክብር ይሁን።” 39ከፈሪሳውያንም በሕዝቡ መካከል፥ “መምህር ሆይ፥ ደቀ መዛሙርትህን ገሥጻቸው” ያሉት ነበሩ። 40እርሱም መልሶ እንዲህ አላቸው፥ “እነዚህ ዝም ቢሉ እኒህ ድንጋዮች ይጮሀሉ።”
ስለ ኢየሩሳሌም መጥፋት
41በደረሰ ጊዜም ከተማዪቱን አይቶ አለቀሰላት። 42እንዲህም አላት፥ “አንቺስ ብታውቂ ሰላምሽ ዛሬ ነበረ፤ ከእንግዲህ ወዲህ ግን ከዐይኖችሽ ተሰወረ። 43ጠላቶችሽ አንቺን የሚከቡበት ቀን ይመጣል፤ ይከትሙብሻል፤ ያስጨንቁሻልም፤ በአራቱ ማዕዘንም ከብበው ይይዙሻል። 44አንቺን ይጥሉሻል፤ ልጆችሽንም ከአንቺ ጋር ይጥሉአቸዋል፤ ድንጋይንም በደንጋይ ላይ አይተዉልሽም፤ የይቅርታሽን ዘመን አላወቅሽምና።”
ጌታችን ገበያተኞቹን ከቤተ መቅደስ ስለ ማስወጣቱ
45ወደ ቤተ መቅደስም ገብቶ በዚያ የሚሸጡትንና የሚገዙትን ሁሉ አስወጣ፤ የለዋጮችንም መደርደሪያ፥ የርግብ ሻጮችንም ወንበር ገለበጠ።#“የለዋጮችንም መደርደሪያ የርግብ ሻጮንም ወንበር ገለበጠ” የሚለው በግሪኩ የለም። 46#ኢሳ. 56፥7፤ ኤር. 7፥11። “ቤቴ የጸሎት ቤት ይባላል የሚል ጽሑፍ አለ፤ እናንተ ግን የሌቦችና የቀማኞች ዋሻ አደረጋችሁት” አላቸው። 47#ሉቃ. 21፥37። ዘወትርም በመቅደስ ያስተምር ነበር፤ የካህናት አለቆች፥ ጻፎችና የሕዝብ ታላላቆችም ሊገድሉት ይሹ ነበር። 48ነገር ግን የሚያደርጉትን አጡ፤ ሕዝቡ ሁሉ ትምህርቱን በመስማት ይመሰጡ ነበርና።
Trenutno odabrano:
የሉቃስ ወንጌል 19: አማ2000
Istaknuto
Podijeli
Kopiraj
Želiš li svoje istaknute stihove spremiti na sve svoje uređaje? Prijavi se ili registriraj