ሉቃስ 22

22
ይሁዳ ጌታን አሳልፎ ለመስጠት ተስማማ
22፥12 ተጓ ምብ – ማቴ 26፥2-5ማር 14፥121011
1በዚህ ጊዜ ፋሲካ የተባለው የቂጣ በዓል ተቃርቦ ነበር። 2የካህናት አለቆችና ጸሐፍትም ሕዝቡን ይፈሩ ስለ ነበር፣ እንዴት አድርገው ኢየሱስን እንደሚያስወግዱት መንገድ ይፈልጉ ነበር። 3ሰይጣንም ከዐሥራ ሁለቱ ጋር በተቈጠረው የአስቆሮቱ ይሁዳ በተባለው ገባበት፤ 4ይሁዳም ወደ ካህናት አለቆችና ወደ ቤተ መቅደሱ ሹሞች ሄዶ ኢየሱስን እንዴት አሳልፎ እንደሚሰጣቸው ተነጋገረ። 5እነርሱም በዚህ ደስ ተሰኝተው፣ ገንዘብ ሊሰጡት ተዋዋሉ። 6እርሱም በነገሩ ተስማማ፤ አሳልፎ ሊሰጣቸውም ሕዝብ የማይገኝበትን ምቹ ጊዜ ይጠብቅ ጀመር።
የመጨረሻው እራት
22፥7-13 ተጓ ምብ – ማቴ 26፥17-19ማር 14፥12-16
22፥17-20 ተጓ ምብ – ማቴ 26፥26-29ማር 14፥22-251ቆሮ 11፥23-25
22፥21-23 ተጓ ምብ – ማቴ 26፥21-24ማር 14፥18-21ዮሐ 13፥21-30
22፥25-27 ተጓ ምብ – ማቴ 20፥25-28ማር 10፥42-45
22፥3334 ተጓ ምብ – ማቴ 26፥33-35ማር 14፥29-31ዮሐ 13፥3738
7ከዚህ በኋላ የፋሲካ በግ የሚታረድበት የቂጣ በዓል ደረሰ። 8ኢየሱስም፣ “የፋሲካን እራት እንድንበላ ሄዳችሁ አዘጋጁልን” ብሎ ጴጥሮስንና ዮሐንስን ላካቸው።
9እነርሱም፣ “የት እንድናሰናዳ ትፈልጋለህ?” አሉት።
10እርሱም እንዲህ አላቸው፤ “እነሆ፤ ወደ ከተማ ስትገቡ የውሃ እንስራ የተሸከመ ሰው ያገኛችኋል፤ እርሱ ወደሚገባበት ቤት ድረስ ተከተሉት፤ 11ለቤቱም ባለቤት፣ ‘መምህሩ፣ ከደቀ መዛሙርቴ ጋር የፋሲካን እራት የምበላበት የእንግዳ ክፍል ወዴት ነው? ይልሃል’ በሉት። 12እርሱም በሰገነት ላይ ያለውን ተነጥፎ የተዘጋጀ ሰፊ አዳራሽ ያሳያችኋል፤ በዚያም አሰናዱልን።”
13እነርሱም ሄደው ልክ ኢየሱስ እንደ ነገራቸው ሆኖ አገኙት፤ ፋሲካንም በዚያ አዘጋጁ።
14ሰዓቱም በደረሰ ጊዜ ኢየሱስ ከሐዋርያቱ ጋር በማእድ ተቀመጠ፤ 15እንዲህም አላቸው፤ “መከራ ከመቀበሌ በፊት ይህን ፋሲካ አብሬያችሁ ለመብላት በጣም ስመኝ ነበር፤ 16እላችኋለሁ፤ በእግዚአብሔር መንግሥት የዚህ ትርጕም እስኪፈጸም ድረስ ይህን ፋሲካ ዳግመኛ አልበላም።”
17ጽዋውን ተቀብሎ ካመሰገነ በኋላ እንዲህ አላቸው፤ “ዕንካችሁ፤ ሁላችሁ ከዚህ ተካፈሉ፤ 18እላችኋለሁና፤ ከአሁን ጀምሮ የእግዚአብሔር መንግሥት እስከምትመጣ ድረስ ከዚህ ወይን ፍሬ አልጠጣም።”
19እንጀራንም አንሥቶ አመሰገነ፤ ቈርሶም ሰጣቸውና፣ “ይህ ስለ እናንተ የሚሰጥ ሥጋዬ ነው፤ ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት” አለ።
20እንደዚሁም ከእራት በኋላ ጽዋውን አንሥቶ እንዲህ አለ፤ “ይህ ጽዋ ስለ እናንተ በሚፈስሰው ደሜ የሚመሠረት አዲስ ኪዳን ነው። 21ነገር ግን አሳልፎ የሚሰጠኝ ሰው እጅ በማእድ ከእኔ ጋር ናት። 22የሰው ልጅስ አስቀድሞ በተወሰነው መሠረት ይሄዳል፤ ነገር ግን እርሱን አሳልፎ ለሚሰጠው ለዚያ ሰው ወዮለት።” 23እነርሱም ከመካከላቸው ይህን የሚያደርግ ማን ሊሆን እንደሚችል እርስ በርሳቸው ይጠያየቁ ጀመር።
24ደግሞም ከመካከላቸው ማን እንደሚበልጥ በእነርሱ ዘንድ ክርክር ተነሣ። 25ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፤ “የአሕዛብ ነገሥታት ሕዝቦቻቸውን በኀይል ይገዛሉ፤ በእነርሱ ላይ ሥልጣን ያላቸውም በጎ አድራጊዎች ተብለው ይጠራሉ። 26በእናንተ ዘንድ ግን እንዲህ አይሁን፤ ይልቁን ከእናንተ ታላቅ የሆነ እንደ ታናሽ፣ ገዥ የሆነም እንደ አገልጋይ ይሁን። 27ለመሆኑ፣ በማእድ ከተቀመጠና ቆሞ ከሚያስተናግድ ማን ይበልጣል? በማእድ የተቀመጠው አይደለምን? እኔ ግን በመካከላችሁ ያለሁት እንደ አንድ አገልጋይ ነው። 28እናንተም ሳትለዩኝ በመከራዬ ጊዜ በአጠገቤ የቆማችሁ ናችሁ፤ 29አባቴ እኔን እንደ ሾመኝ እኔም ደግሞ በመንግሥቴ እሾማችኋለሁ፤ 30ይኸውም በመንግሥቴ ከማእዴ እንድትበሉና እንድትጠጡ ደግሞም በዙፋን ላይ ተቀምጣችሁ በዐሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገድ ላይ እንድትፈርዱ ነው።”
31ደግሞም ኢየሱስ እንዲህ አለ፤ “ስምዖን፣ ስምዖን ሆይ፤ እነሆ፤ ሰይጣን እንደ ስንዴ ሊያበጥራችሁ ለመነ፤ 32እኔ ግን እምነትህ እንዳይጠፋ ስለ አንተ ጸለይሁ፤ አንተም በተመለስህ ጊዜ ወንድሞችህን አበርታ።”
33ስምዖንም፣ “ጌታ ሆይ፤ እኔ ከአንተ ጋር ወህኒ ለመውረድም፣ ለመሞትም ዝግጁ ነኝ” አለው።
34ኢየሱስም፣ “ጴጥሮስ ሆይ፤ እልሃለሁ፤ ዛሬ ዶሮ ሳይጮኽ፣ አላውቀውም ብለህ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ” አለው።
35ከዚያም ኢየሱስ፣ “ያለ ኰረጆ፣ ያለ ከረጢትና ያለ ጫማ በላክኋችሁ ጊዜ የጐደለባችሁ ነገር ነበርን?” ብሎ ጠየቃቸው።
እነርሱም፣ “ምንም አልጐደለብንም” አሉ።
36እርሱም እንዲህ አላቸው፤ “አሁን ግን ኰረጆም፣ ከረጢትም ያለው ሰው ይያዝ፤ ሰይፍ የሌለውም ልብሱን ሽጦ ይግዛ። 37እላችኋለሁና፤ ‘ከዐመፀኞች ጋር ተቈጠረ’ ተብሎ የተጻፈው በእኔ መፈጸም አለበት፤ ስለ እኔ የተጻፈው ፍጻሜው በርግጥ ደርሷል።”
38ደቀ መዛሙርቱም፣ “ጌታ ሆይ፤ እነሆ፤ ሁለት ሰይፎች እዚህ አሉ” አሉት።
እርሱም፣ “ይበቃል” አላቸው።
ኢየሱስ በደብረ ዘይት ተራራ ጸለየ
22፥40-46 ተጓ ምብ – ማቴ 26፥36-46ማር 14፥32-42
39ኢየሱስ እንደ ልማዱ ወጥቶ ወደ ደብረ ዘይት ተራራ ሄደ፤ ደቀ መዛሙርቱም ተከተሉት። 40እዚያም በደረሱ ጊዜ፣ “ወደ ፈተና እንዳትገቡ ጸልዩ” አላቸው። 41ከእነርሱም የድንጋይ ውርወራ ያህል ርቆ ተንበርክኮ ጸለየ፤ 42እንዲህም አለ፤ “አባት ሆይ፤ ፈቃድህ ከሆነ፣ ይህችን ጽዋ ከእኔ ውሰድ፤ ነገር ግን የእኔ ፈቃድ ሳይሆን የአንተ ፈቃድ ይፈጸም።” 43መልአክም ከሰማይ ተገልጦለት አበረታታው። 44እጅግ ተጨንቆም በብርቱ ይጸልይ ነበር፤ ላቡም እንደ ደም ነጠብጣብ ወደ ምድር#22፥44 አንዳንድ የጥንት ቅጆች ቍጥር 43 እና 44 የላቸውም። ይፈስስ ነበር።
45ከጸሎትም ተነሥቶ ወደ ደቀ መዛሙርቱ መጣ፤ እነርሱም ከሐዘን የተነሣ ተኝተው አገኛቸውና፣ 46“ለምን ትተኛላችሁ? ወደ ፈተና እንዳትገቡ ተነሥታችሁ ጸልዩ” አላቸው።
ኢየሱስ ተያዘ
22፥47-53 ተጓ ምብ – ማቴ 26፥47-56ማር 14፥43-50ዮሐ 18፥3-11
47እርሱም ገና እየተነጋገረ ሳለ፣ ብዙ ሰዎች መጡ፤ ከዐሥራ ሁለቱ አንዱ ይሁዳ የተባለውም ሰው ይመራቸው ነበር፤ ሊስመውም ወደ ኢየሱስ ተጠጋ። 48ኢየሱስ ግን፣ “ይሁዳ ሆይ፤ የሰውን ልጅ በመሳም አሳልፈህ ትሰጣለህን?” አለው።
49በኢየሱስ ዙሪያ የነበሩ ሰዎችም ሁኔታውን ተመልክተው “ጌታ ሆይ፤ በሰይፍ እንምታቸውን?” አሉት። 50ከእነርሱም አንዱ የሊቀ ካህናቱን አገልጋይ መትቶ ቀኝ ጆሮውን ቈረጠው።
51ኢየሱስ ግን፣ “ተው! እዚህ ድረስም ፍቀዱ” አለ፤ የሰውየውንም ጆሮ ዳስሶ ፈወሰው።
52ከዚያም ኢየሱስ ሊይዙት የመጡትን የካህናት አለቆች፣ የቤተ መቅደስ ሹሞችና ሽማግሌዎችን እንዲህ አላቸው፤ “ወንበዴ እንደሚይዝ ሰው፣ ሰይፍና ቈመጥ ይዛችሁ ወጣችሁን? 53በየዕለቱ በቤተ መቅደስ ከእናንተ ጋር በነበርሁ ጊዜ እጃችሁን አላነሣችሁብኝም፤ ይህ ግን ጨለማ የነገሠበት ጊዜያችሁ ነው።”
ጴጥሮስ ኢየሱስን ካደ
22፥55-62 ተጓ ምብ – ማቴ 26፥69-75ማር 14፥66-72ዮሐ 18፥16-1825-27
54ከዚህ በኋላ ኢየሱስን ይዘው ወሰዱት፤ ወደ ሊቀ ካህናቱም ግቢ አስገቡት፤ ጴጥሮስም በርቀት ይከተለው ነበር። 55ሰዎቹ በሊቀ ካህናቱ ግቢ ውስጥ እሳት አንድደው በአንድነት ተቀምጠው ሳለ፣ ጴጥሮስም ከእነርሱ ጋር ተቀምጦ ነበር። 56አንዲት የቤት ሠራተኛም ጴጥሮስ እሳቱ አጠገብ ተቀምጦ አየችውና ትኵር ብላ በመመልከት፣ “ይህ ሰው ደግሞ ከእርሱ ጋር ነበረ” አለች።
57እርሱ ግን፣ “አንቺ ሴት፤ እኔ ዐላውቀውም” ብሎ ካደ።
58ከጥቂት ጊዜ በኋላም አንድ ሌላ ሰው አይቶት፣ “አንተም ደግሞ ከእነርሱ አንዱ ነህ” አለው።
ጴጥሮስ ግን፣ “አንተ ሰው፤ እኔ አይደለሁም” አለ።
59አንድ ሰዓት ያህል ቈይቶም፣ ሌላ ሰው በርግጠኝነት፣ “ይህ ሰው ከገሊላ ስለሆነ ያለ ጥርጥር ከእርሱ ጋር ነበረ” አለ።
60ጴጥሮስ ግን፣ “አንተ ሰው፤ የምትለውን እኔ አላውቅም” አለ፤ ይህንም ተናግሮ ገና ሳይጨርስ ዶሮ ጮኸ። 61ጌታም መለስ ብሎ ጴጥሮስን ተመለከተው፤ ጴጥሮስም፣ “ዛሬ ዶሮ ሳይጮኽ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ” ብሎ ጌታ የተናገረው ቃል ትዝ አለው። 62ጴጥሮስም ወደ ውጭ ወጥቶ ምርር ብሎ አለቀሰ።
ወታደሮች በኢየሱስ ላይ አፌዙበት
22፥63-65 ተጓ ምብ – ማቴ 26፥6768ማር 14፥65ዮሐ 18፥2223
63ኢየሱስን አስረው ይጠብቁት የነበሩት ሰዎችም ያፌዙበትና ይመቱት ጀመር፤ 64ዐይኑንም ሸፍነው፣ “እስቲ ትንቢት ተናገር፤ የመታህ ማነው?” እያሉ ይጠይቁት ነበር። 65ሌላም ብዙ የስድብ ቃል እየተናገሩ ያቃልሉት ነበር።
ኢየሱስ በጲላጦስና በሄሮድስ ፊት
22፥67-71 ተጓ ምብ – ማቴ 26፥63-66ማር 14፥61-63ዮሐ 18፥19-21
23፥23 ተጓ ምብ – ማቴ 27፥11-14ማር 15፥2-5ዮሐ 18፥29-37
23፥18-25 ተጓ ምብ – ማቴ 27፥15-26ማር 15፥6-15ዮሐ 18፥39–19፥16
66በነጋም ጊዜ፣ የሕዝብ ሽማግሌዎች፣ የካህናት አለቆችና ጸሐፍት ተሰበሰቡ፤ ኢየሱስንም በሸንጓቸው ፊት አቀረቡት። 67እነርሱም፣ “አንተ ክርስቶስ#22፥67 ወይም መሲሕ ነህን? እስቲ ንገረን” አሉት።
ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፤ “ብነግራችሁ አታምኑኝም፤ 68ብጠይቃችሁም አትመልሱም። 69ነገር ግን ከአሁን ጀምሮ የሰው ልጅ በእግዚአብሔር ኀይል ቀኝ ይቀመጣል።”
70በዚህ ጊዜ ሁሉም፣ “ታዲያ፣ አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህን?” አሉት።
እርሱም፣ “መሆኔን እኮ እናንተው ተናገራችሁት” አላቸው።
71እነርሱም፣ “ከእንግዲህ ሌላ ምስክር ምን ያስፈልገናል? ራሳችን ከገዛ አንደበቱ ሰምተናልና” አሉ።

Tällä hetkellä valittuna:

ሉቃስ 22: NASV

Korostus

Jaa

Kopioi

None

Haluatko, että korostuksesi tallennetaan kaikille laitteillesi? Rekisteröidy tai kirjaudu sisään