ሉቃስ 19
19
ቀረጥ ሰብሳቢው ዘኬዎስ
1ኢየሱስ ወደ ኢያሪኮ ገብቶ በዚያ ዐልፎ ይሄድ ነበር። 2ስሙ ዘኬዎስ የተባለ አንድ ሰው በዚያ ነበረ፤ ዋና ቀረጥ ሰብሳቢና ሀብታም ነበረ። 3እርሱም ኢየሱስ የተባለው የትኛው እንደ ሆነ ሊያይ ይፈልግ ነበር፤ ቁመቱ ዐጭር ነበረና ከሕዝቡ ብዛት የተነሣ ሊያየው አልቻለም። 4ኢየሱስ በዚያ መንገድ ያልፍ ስለ ነበርም፣ ሊያየው ወደ ፊት ሮጦ አንድ ሾላ ዛፍ ላይ ወጣ።
5ኢየሱስም እዚያ ቦታ ሲደርስ፣ ቀና ብሎ፣ “ዘኬዎስ ሆይ፤ ዛሬ አንተ ቤት መዋል ይገባኛልና ፈጥነህ ውረድ” አለው። 6እርሱም ፈጥኖ ወርዶ በደስታ ተቀበለው።
7በዚያ የነበሩ ሰዎች ሁሉም ይህን አይተው፣ “ከኀጢአተኛ ቤት ገብቶ ሊስተናገድ ነው።” በማለት ማጕረምረም ጀመሩ።
8ዘኬዎስ ግን ቆመና ጌታን፣ “ጌታ ሆይ፤ እነሆ ካለኝ ሀብት ሁሉ ግማሹን ለድኾች እሰጣለሁ፤ ማንንም በሐሰት ቀምቼ ከሆነ፣ አራት ዕጥፍ አድርጌ እመልሳለሁ” አለው።
9ኢየሱስም እንዲህ አለው፤ “ይህ ሰው ደግሞ የአብርሃም ልጅ ስለሆነ፣ ዛሬ መዳን ወደዚህ ቤት መጥቷል፤ 10ምክንያቱም የሰው ልጅ የመጣው የጠፋውን ሊፈልግና ሊያድን ነው።”
የዐሥሩ ምናን ምሳሌ
19፥12-27 ተጓ ምብ – ማቴ 25፥14-30
11ሕዝቡ ይህን እየሰሙ ሳሉ፣ በምሳሌ መናገሩን ቀጠለ፤ ምክንያቱም ወደ ኢየሩሳሌም በመቃረቡና ሰዎቹም የእግዚአብሔር መንግሥት የሚገለጥ ስለ መሰላቸው ነው። 12ስለዚህም እንዲህ አለ፤ “አንድ መስፍን የንጉሥነትን ማዕረግ ተቀብሎ ለመመለስ ወደ ሩቅ አገር ሄደ። 13ከአገልጋዮቹም መካከል ዐሥሩን ጠርቶ ዐሥር ምናን ሰጣቸውና ‘ተመልሼ እስክመጣ ድረስ በዚህ ገንዘብ ነግዱበት’ አላቸው።
14 “የአገሩ ሰዎች ግን ስለ ጠሉት፤ ‘ይህ ሰው በላያችን እንዲነግሥ አንፈልግም’ ብለው ከኋላው መልእክተኞችን ላኩበት።
15 “ይሁን እንጂ ይህ መስፍን ንጉሥ ሆኖ ወደ አገሩ ተመለሰ፤ እነዚያ አገልጋዮቹም እርሱ በሰጣቸው ገንዘብ ነግደው ምን ያህል እንዳተረፉ ለማወቅ አስጠራቸው።
16 “የመጀመሪያው አገልጋይ ቀርቦ፣ ‘ጌታ ሆይ፤ የሰጠኸኝ ምናን ዐሥር ምናን ትርፍ አስገኝቷል’ አለው።
17 “ጌታውም፣ ‘አንተ ታማኝ አገልጋይ፣ መልካም አድርገሃል፤ በትንሽ ነገር ታማኝ ሆነህ ስለ ተገኘህ፣ በዐሥር ከተሞች ላይ ሥልጣን ተሰጥቶሃል’ አለው።
18 “ሁለተኛውም ቀርቦ፣ ‘ጌታ ሆይ፤ የሰጠኸኝ ምናን አምስት ምናን ትርፍ አስገኝቷል’ አለው።
19 “ጌታውም፣ ‘አንተ ደግሞ በአምስት ከተሞች ላይ ሥልጣን ተሰጥቶሃል’ አለው።
20 “ሌላውም አገልጋይ ቀርቦ እንዲህ አለው፤ ‘ጌታ ሆይ፤ በጨርቅ ጠቅልዬ ያቈየሁት ምናንህ ይኸው፤ 21አንተ ያላስቀመጥኸውን የምትወስድ፣ ያልዘራኸውን የምታጭድ ጨካኝ ሰው ስለ ሆንህ ፈራሁህ።’
22 “ጌታውም እንዲህ አለው፤ ‘አንተ ክፉ አገልጋይ! በራስህ ቃል እፈርድብሃለሁ፤ ያላስቀመጥሁትን የምወስድ፣ ያልዘራሁትን የማጭድ፣ ጨካኝ ሰው መሆኔን ካወቅህ፣ 23መጥቼ ገንዘቤን ከነትርፉ እንድወስድ፣ ለምን ለሚሠሩበት ሰዎች አልሰጠህም?’
24 “ጌታውም እዚያ የቆሙትን፣ ‘ምናኑን ውሰዱበትና ዐሥር ምናን ላለው ስጡት’ አላቸው።
25 “እነርሱም፣ ‘ጌታ ሆይ፤ እርሱ እኮ ዐሥር ምናን አለው’ አሉት።
26 “እርሱም እንዲህ አለ፤ ‘እላችኋለሁ፤ ላለው ሁሉ ይጨመርለታል፤ የሌለው ግን ያው ያለው እንኳ ይወሰድበታል። 27ነገር ግን እኔ በላያቸው እንዳልነግሥ የፈለጉትን እነዚያን ጠላቶቼን ወደዚህ አምጡና በፊቴ ዕረዷቸው።’ ”
ኢየሱስ በታላቅ ክብር ወደ ኢየሩሳሌም መግባቱ
19፥29-38 ተጓ ምብ – ማቴ 21፥1-9፤ ማር 11፥1-10
19፥35-38 ተጓ ምብ – ዮሐ 12፥12-15
28ኢየሱስ ይህን ከተናገረ በኋላ፣ ወደ ኢየሩሳሌም ሊወጣ ቀድሟቸው ይሄድ ነበር። 29ደብረ ዘይት በተባለው ተራራ ወደሚገኙት፣ ወደ ቤተ ፋጌና ወደ ቢታንያ ከተሞች በቀረበ ጊዜ፣ ከደቀ መዛሙርቱ ሁለቱን እንዲህ ሲል ላካቸው፤ 30“በፊታችሁ ወዳለችው መንደር ሂዱ፤ ወደዚያም ስትገቡ ማንም ገና ያልተቀመጠበት ውርንጫ ታስሮ ታገኛላችሁ፤ ፈትታችሁ ወደዚህ አምጡት። 31ማንም፣ ‘ለምን ትፈቱታላችሁ?’ ብሎ ቢጠይቃችሁ፣ ‘ለጌታ ያስፈልገዋል’ በሉት።”
32የተላኩትም ሄደው ልክ እንደ ነገራቸው ሆኖ አገኙት። 33ባለቤቶቹም ውርንጫውን ሲፈቱ አይተው፣ “ውርንጫውን ለምን ትፈታላችሁ?” አሏቸው።
34እነርሱም፣ “ለጌታ ያስፈልገዋል” አሉ።
35ከዚያም ውርንጫውን ወደ ኢየሱስ አመጡት፤ ልብሳቸውንም በላዩ ጣል አድርገው ኢየሱስን በውርንጫው ላይ አስቀመጡት። 36ሰዎችም እርሱ በሚሄድበት መንገድ ላይ ልብሳቸውን ያነጥፉ ነበር።
37በደብረ ዘይት ተራራ ቍልቍል ወደሚወስደው መንገድ በተቃረቡ ጊዜ፣ ቍጥራቸው እጅግ ብዙ የሆነ ደቀ መዛሙርት ስላዩት ታምራት ሁሉ ደስ እያላቸው ድምፃቸውን ከፍ በማድረግ እንዲህ እያሉ እግዚአብሔርን ያመሰግኑ ጀመር፤
38“በጌታ ስም የሚመጣው ንጉሥ የተባረከ ነው!”
“በሰማይ ሰላም፣ በአርያምም ክብር ይሁን!”
39በሕዝቡ መካከል የነበሩ አንዳንድ ፈሪሳውያንም ኢየሱስን፣ “መምህር ሆይ፤ ደቀ መዛሙርትህን ገሥጻቸው እንጂ” አሉት።
40እርሱም፣ “እላችኋለሁ፤ እነርሱ ዝም ቢሉ፣ ድንጋዮች ይጮኻሉ” አላቸው።
41ኢየሱስም ወደ ኢየሩሳሌም ሲቃረብ ከተማዋን አይቶ አለቀሰላት፤ 42እንዲህም አለ፤ “ሰላምሽ የሚሆነውን ምነው አንቺ ዛሬ በተረዳሽ ኖሮ! አሁን ግን ከዐይንሽ ተሰውሯል፤ 43ጠላቶችሽ ዙሪያሽን ቅጥር ሠርተው፣ ከየአቅጣጫውም ከብበው አንቺን የሚያስጨንቁበት ጊዜ ይመጣልና፤ 44አንቺንና በቅጥርሽ ውስጥ የሚኖሩትንም ልጆችሽን ከዐፈር ይደባልቃሉ፤ ድንጋይም በድንጋይ ላይ አይተዉም፤ የመጐብኛሽን ጊዜ አላወቅሽምና።”
ኢየሱስ በቤተ መቅደስ
19፥45፡46 ተጓ ምብ – ማቴ 21፥12-16፤ ማር 11፥15-18፤ ዮሐ 2፥13-16
45ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ወደ ቤተ መቅደስ ገብቶ፣ ሻጮችን ከዚያ አስወጣ፤ 46ደግሞም “ ‘ቤቴ የጸሎት ቤት ይሆናል’ ተብሎ ተጽፏል፤ እናንተ ግን ‘የወንበዴዎች ዋሻ’ አደረጋችሁት” አላቸው።
47በየቀኑም በቤተ መቅደስ ያስተምር ነበር፤ የካህናት አለቆች፣ ጸሐፍትና የሕዝብ መሪዎችም ሊገድሉት ይፈልጉ ነበር፤ 48ነገር ግን ሕዝቡ ሁሉ ከእርሱ ጋር ተቈራኝተው ትምህርቱን ይከታተሉ ስለ ነበር፣ የሚያደርጉት ግራ ገባቸው።
Tällä hetkellä valittuna:
ሉቃስ 19: NASV
Korostus
Jaa
Kopioi
Haluatko, että korostuksesi tallennetaan kaikille laitteillesi? Rekisteröidy tai kirjaudu sisään
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጅ መብት © 2001 በ Biblica, Inc.
ፈቃድ የተገኘባቸው ናቸው። መብቱ በመላው ዓለም በሕግ የተጠበቀ።
Holy Bible, New Amharic Standard Version™ (Addisu Medebegna Tirgum™)
Copyright © 2001 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.