ሉቃስ 12
12
የማስጠንቀቂያና የማበረታቻ ቃላት
12፥2-9 ተጓ ምብ – ማቴ 10፥26-33
1በዚያን ጊዜ፣ በብዙ ሺሕ የሚቈጠር ሕዝብ እርስ በርስ እስኪረጋገጥ ድረስ ተሰብስቦ ሳለ፣ ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ ይል ጀመር፤ “ከፈሪሳውያን እርሾ ተጠንቀቁ፤ ይህም ግብዝነት ነው። 2የማይገለጥ የተሸፈነ፣ የማይታወቅ የተሰወረ ምንም የለም። 3ስለዚህ በጨለማ ያወራችሁት ሁሉ በብርሃን ይሰማል፤ በእልፍኝም ውስጥ በጆሮ ያንሾካሾካችሁት በሰገነት በይፋ ይነገራል።
4 “ወዳጆቼ ሆይ፤ እላችኋለሁ፣ ሥጋን የሚገድሉትን፣ ከዚያ ወዲያ ግን ምንም ማድረግ የማይችሉትን አትፍሩ። 5ነገር ግን መፍራት የሚገባችሁን አሳያችኋለሁ፤ ከገደለ በኋላ ወደ ገሃነም ለመጣል ሥልጣን ያለውን እርሱን ፍሩት፤ አዎን፣ እርሱን ፍሩት እላችኋለሁ። 6አምስት ድንቢጦች በዐሥር ሳንቲም#12፥6 ግሪኩ ሁለት ኢሳሪያ ይላል ይሸጡ የለምን? ይሁን እንጂ ከእነርሱ አንዷ እንኳ በእግዚአብሔር ዘንድ አትዘነጋም። 7የእናንተ የራሳችሁ ጠጕር ሁሉ እንኳ የተቈጠረ ነው፤ እንግዲህ አትፍሩ፤ ከብዙ ድንቢጦች የበለጠ ዋጋ አላችሁ።
8 “እላችኋለሁ፤ በሰው ፊት ለሚመሰክርልኝ ሁሉ፣ የሰው ልጅ ደግሞ በእግዚአብሔር መላእክት ፊት ይመሰክርለታል። 9በሰው ፊት የሚክደኝም በእግዚአብሔር መላእክት ፊት ይካዳል። 10በሰው ልጅ ላይ የማቃለል ቃል የሚሰነዝር ሁሉ ይሰረይለታል፤ መንፈስ ቅዱስን የሚሳደብ ግን አይሰረይለትም።
11 “ሰዎች ይዘው ወደ ምኵራብ፣ ወደ ገዥዎችና ወደ ባለሥልጣናት ባቀረቧችሁ ጊዜ፣ እንዴት ወይም ምን እንደምትመልሱ አትጨነቁ፤ 12በዚያ ሰዓት መንፈስ ቅዱስ መናገር የሚገባችሁን ያስተምራችኋልና።”
የሀብታሙ ሰው ሞኝነት
13ከሕዝቡም መካከል አንድ ሰው፣ “መምህር ሆይ፤ ወንድሜ ውርስ እንዲያካፍለኝ ንገረው” አለው።
14ኢየሱስም፣ “አንተ ሰው፤ በእናንተ ላይ ፈራጅ ወይም ዳኛ ያደረገኝ ማነው?” አለው። 15ደግሞም፣ “የሰው ሕይወቱ በሀብቱ ብዛት የተመሠረተ ስላልሆነ ተጠንቀቁ፤ ከስግብግብነትም ሁሉ ራሳችሁንም ጠብቁ” አላቸው።
16ቀጥሎም እንዲህ ሲል ምሳሌ ነገራቸው፤ “ዕርሻው እጅግ ፍሬያማ የሆነችለት አንድ ሀብታም ነበረ፤ 17ይህም ሰው፣ ምርቴን የማከማችበት ስፍራ ስለሌለኝ ምን ላድርግ? ብሎ በልቡ ዐሰበ።
18 “እንዲህም አለ፤ ‘እንደዚህ አደርጋለሁ፤ ያሉኝን ጐተራዎች አፈርስና ሌሎች ሰፋ ያሉ ጐተራዎች እሠራለሁ፤ በዚያም ምርቴንና ንብረቴንም ሁሉ አከማቻለሁ፤ 19ነፍሴንም፣ “ነፍሴ ሆይ፤ ለብዙ ዘመን የሚበቃሽ ሀብት አከማችቼልሻለሁ፤ እንግዲህ ዕረፊ፤ ብዪ፤ ጠጪ፤ ደስም ይበልሽ” እላታለሁ።’
20 “እግዚአብሔር ግን፣ ‘አንተ ሞኝ፤ ነፍስህን በዚህች ሌሊት ከአንተ ሊውስዱ ይፈልጓታል፤ እንግዲህ፣ ለራስህ ያከማቸኸው ለማን ይሆናል?’ አለው።
21 “ስለዚህ ለራሱ ሀብት የሚያከማች፣ ዳሩ ግን በእግዚአብሔር ዘንድ ሀብታም ያልሆነ ሰው መጨረሻው ይኸው ነው።”
አትጨነቁ
12፥23-31 ተጓ ምብ – ማቴ 6፥25-33
22ከዚያም ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ አለ፤ “ስለዚህ እላችኋለሁ፣ ስለ ሕይወታችሁ ምን እንደምትበሉ ወይም ስለ ሰውነታችሁ ምን እንደምትለብሱ አትጨነቁ፤ 23ሕይወት ከምግብ፣ ሰውነትም ከልብስ ይበልጣልና። 24ቍራዎችን ተመልከቱ፤ አይዘሩም፤ አያጭዱም፤ ማከማቻ ወይም ጐተራ የላቸውም፤ እግዚአብሔር ግን ይመግባቸዋል። እናንተማ ከወፎች እጅግ ትበልጡ የለምን? 25ለመሆኑ፣ ከእናንተ ተጨንቆ በዕድሜው ላይ አንድ ሰዓት መጨመር የሚችል ማነው?#12፥25 ወይም በቁመቱ ላይ አንድ ስንዝር 26እንግዲህ ቀላሉን ነገር እንኳ ማድረግ የማትችሉ ከሆነ፣ ስለ ሌላው ነገር ለምን ትጨነቃላችሁ?
27 “እስቲ አበቦች እንዴት እንደሚያድጉ ተመልከቱ፤ አይለፉም፤ አይፈትሉም፤ ነገር ግን እላችኋለሁ፤ ሰሎሞን እንኳ በዚያ ሁሉ ክብሩ ከእነርሱ እንደ አንዷ አልለበሰም። 28እንግዲህ እግዚአብሔር ዛሬ ታይቶ ነገ ወደ እሳት የሚጣለውን የሜዳ ሣር እንዲህ የሚያለብስ ከሆነ፣ እናንተ እምነት የጐደላችሁ፣ እናንተንማ እንዴት አብልጦ አያለብሳችሁም? 29ስለዚህ ምን እንደምትበሉና ምን እንደምትጠጡ በመሻት ልባችሁ አይጨነቅ፤ 30ይህንማ በዓለም ያለ ሕዝብ ሁሉ ይፈልጋል፤ አባታችሁ እኮ ይህ ሁሉ እንደሚያስፈልጋችሁ ያውቃል። 31ይልቁንስ የእግዚአብሔርን መንግሥት ፈልጉ፤ ይህም ሁሉ በተጨማሪ ይሰጣችኋል።
32 “እናንተ አነስተኛ መንጋ የሆናችሁ፤ መንግሥትን ሊሰጣችሁ የአባታችሁ መልካም ፈቃድ ነውና አትፍሩ፤ 33ያላችሁን ሽጡና ለድኾች ስጡ፤ ሌባ በማይሰርቅበት፣ ብል በማይበላበት፣ በማያረጅ ከረጢት የማያልቅ ንብረት በሰማይ አከማቹ፤ 34ልባችሁ፣ ንብረታችሁ ባለበት ቦታ ይሆናልና።
ነቅቶ መጠበቅ
12፥35፡36 ተጓ ምብ – ማቴ 25፥1-13፤ ማር 13፥33-37
12፥39-40፡42-46 ተጓ ምብ – ማቴ 24፥43-51
35 “በዐጭር ታጥቃችሁ ተዘጋጁ፤ መብራታችሁም የበራ ይሁን፤ 36ጌታቸው ከሰርግ ግብዣ እስኪመለስ የሚጠባበቁና መጥቶም በር ሲያንኳኳ ወዲያው ለመክፈት ዝግጁ የሆኑ ሰዎችን ምሰሉ። 37ጌታቸው በሚመጣበት ጊዜ ነቅተው የሚያገኛቸው አገልጋዮች ብፁዓን ናቸው። እውነት እላችኋለሁ፤ ጌታቸውም በዐጭር ይታጠቃል፤ በማእድ ያስቀምጣቸዋል፤ ቀርቦም ያስተናግዳቸዋል። 38ከሌሊቱ በሁለተኛውም ሆነ በሦስተኛው ክፍል መጥቶ እንደዚያው ነቅተው ቢያገኛቸው፣ እነዚያ አገልጋዮች ብፁዓን ናቸው። 39ይህን ግን ዕወቁ፤ ሌባ በምን ሰዓት እንደሚመጣ የቤቱ ባለቤት ቢያውቅ ኖሮ፣ ቤቱ ሲቈፈር ዝም ብሎ ባላየ ነበር። 40እናንተም ተዘጋጅታችሁ ጠብቁ፤ የሰው ልጅ ባላሰባችሁት ሰዓት ይመጣልና።”
41ጴጥሮስም፣ “ጌታ ሆይ፤ ይህን ምሳሌ የምትናገረው ለእኛ ብቻ ነው ወይስ ለሁሉም ጭምር ነው?” አለው።
42ጌታም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “እንግዲህ፣ ምግባቸውን በተገቢው ጊዜ እንዲሰጣቸው፣ ጌታው በቤተ ሰዎቹ ላይ የሚሾመው ታማኝና ብልኅ መጋቢ ማነው? 43ጌታው ሲመለስ እንዲህ ሲያደርግ የሚያገኘው አገልጋይ እርሱ ብፁዕ ነው። 44እውነት እላችኋለሁ፤ ባለው ንብረት ሁሉ ላይ ይሾመዋል። 45ዳሩ ግን ያ አገልጋይ፣ ጌታዬ ቶሎ አይመጣም፤ ይዘገያል፤ ብሎ ቢያስብና ወንድና ሴት አገልጋዮችን ቢደበድብ፣ ደግሞም እንዳሻው መብላት፣ መጠጣትና መስከር ቢጀምር፣ 46የዚያ አገልጋይ ጌታ ባላሰበው ቀንና ባልጠረጠረው ሰዓት ይመጣበታል፤ ስለዚህ ይቈራርጠዋል፤ ዕድል ፈንታውንም ከማያምኑ ጋር ያደርጋል።
47 “የጌታውን ፍላጎት እያወቀ የማይዘጋጅና ፈቃዱን የማያደርግ አገልጋይ እርሱ ክፉኛ ይገረፋል፤ 48ነገር ግን ይህን ሳያውቅ ቀርቶ መገረፍ የሚገባውን ያህል ያደረገ አገልጋይ በጥቂቱ ይገረፋል። ብዙ ከተሰጠው ሁሉ ብዙ ይፈለግበታል፤ ብዙ ዐደራ ከተቀበለም ብዙ ይጠበቅበታል።
ሰላም ሳይሆን መለያየት
12፥51-53 ተጓ ምብ – ማቴ 10፥34-36
49 “እኔ የመጣሁት በምድር ላይ እሳት ለመለኰስ ነው፤ አሁኑኑ ቢቀጣጠል ምንኛ ደስ ባለኝ! 50ነገር ግን የምጠመቀው ጥምቀት አለኝ፤ እስኪፈጸምም ድረስ እንዴት ተጨንቄአለሁ? 51በምድር ላይ ሰላምን ለማምጣት የመጣሁ ይመስላችኋል? አይደለም፤ እላችኋለሁ፤ እኔ የመጣሁት ለመለያየት ነው። 52ከአሁን ጀምሮ እርስ በርስ የተለያዩ በአንድ ቤተ ሰብ ውስጥ አምስት ሰዎች ይኖራሉ፤ ሁለቱ በሦስቱ ላይ፣ ሦስቱም በሁለቱ ላይ ተነሥተው ይለያያሉ። 53አባት በወንድ ልጁ ላይ፣ ወንድ ልጅም በአባቱ ላይ፣ እናት በሴት ልጇ ላይ፣ ሴት ልጅም በእናቷ ላይ፣ ዐማት በምራቷ ላይ፣ ምራትም በዐማቷ ላይ ተነሥተው ይለያያሉ።”
ዘመናትን መመርመር
54ደግሞም ለሕዝቡ እንዲህ አለ፤ “ደመና በምዕራብ በኩል ሲወጣ ስታዩ ወዲያው፣ ዝናብ ሊመጣ ነው ትላላችሁ፤ እንደዚያም ይሆናል፤ 55የደቡብ ነፋስም ከደቡብ በኩል ሲነፍስ፣ ቀኑ ሞቃት ይሆናል ትላላችሁ፤ እንደዚያም ይሆናል። 56እናንት ግብዞች፤ የምድሩንና የሰማዩን መልክ መመርመር ታውቁበታላችሁ፤ ታዲያ ይህን የአሁኑን ዘመን መመርመር እንዴት ተሳናችሁ?
57 “ታዲያ ራሳችሁ ትክክለኛ የሆነውን ነገር ለምን አትፈርዱም? 58ከባላጋራህ ጋር ወደ ዳኛ ፊት ለመቅረብ ስትሄድ፣ ገና በመንገድ ላይ ሳለህ ለመታረቅ ጥረት አድርግ፤ አለዚያ ጐትቶ ወደ ዳኛው ይወስድሃል፤ ዳኛውም ለመኰንኑ አሳልፎ ይሰጥሃል፤ መኰንኑም ወደ ወህኒ ይጥልሃል። 59እልሃለሁ፤ የመጨረሻዋን ሳንቲም#12፥59 ግሪኩ ሌፕቶን ይላል። እስክትከፍል ድረስ ከዚያ አትወጣም።”
Tällä hetkellä valittuna:
ሉቃስ 12: NASV
Korostus
Jaa
Kopioi
Haluatko, että korostuksesi tallennetaan kaikille laitteillesi? Rekisteröidy tai kirjaudu sisään
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጅ መብት © 2001 በ Biblica, Inc.
ፈቃድ የተገኘባቸው ናቸው። መብቱ በመላው ዓለም በሕግ የተጠበቀ።
Holy Bible, New Amharic Standard Version™ (Addisu Medebegna Tirgum™)
Copyright © 2001 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.