ዮሐንስ 8

8
በምንዝር የተያዘች ሴት
1ኢየሱስ ግን ወደ ደብረ ዘይት ሄደ። 2በማለዳም በቤተ መቅደስ አደባባይ እንደ ገና ታየ፤ ሕዝቡም በዙሪያው ተሰበሰበ፤ ሊያስተምራቸውም ተቀመጠ። 3የኦሪት ሕግ መምህራንና ፈሪሳውያን በምንዝር የተያዘች ሴት አመጡ፤ በሕዝቡም ፊት አቁመዋት፣ 4ኢየሱስን እንዲህ አሉት፤ “መምህር ሆይ፣ ይህች ሴት ስታመነዝር ተያዘች፤ 5ሙሴም፣ እንደዚች ያሉ ሴቶች በድንጋይ እንዲወገሩ በሕጉ አዝዞናል፤ አንተስ ምን ትላለህ?” 6ይህን ጥያቄ ያቀረቡለት፣ እርሱን የሚከስሱበት ምክንያት ለማግኘት ሲፈትኑት ነው።
ኢየሱስ ግን ጐንበስ ብሎ በጣቱ በምድር ላይ ይጽፍ ጀመር። 7በጥያቄ ሲወተውቱት ቀና ብሎ፣ “ከእናንተ ኀጢአት የሌለበት እርሱ አስቀድሞ ድንጋይ ይወርውርባት” አላቸው። 8እንደ ገናም ጐንበስ ብሎ በምድር ላይ ጻፈ።
9ይህን እንደ ሰሙ፣ ከሽማግሌዎች ጀምሮ አንድ በአንድ ወጡ፤ ሴትዮዋም እዚያው ፊቱ እንደ ቆመች ኢየሱስ ብቻውን ቀረ። 10ኢየሱስም ቀና ብሎ፣ “አንቺ ሴት፣ ሰዎቹ የት ሄዱ? የፈረደብሽ የለምን?” አላት።
11እርሷም፣ “ጌታ ሆይ፤ አንድም የለም” አለች።
ኢየሱስም፣ “እኔም አልፈርድብሽም፤ በይ ሂጂ፤ ከእንግዲህ ግን ኀጢአት አትሥሪ” አላት።#8፥11 ብዙ የጥንት ቅጆች ይህ ክፍል (7፥53–8፥11) የላቸውም፤ ወይም በሌላ ስፍራ ወይም በሌሎች ወንጌሎች ያስገቡታል።
የኢየሱስ ምስክርነት እውነት መሆኑ
12ኢየሱስ እንደ ገና ለሰዎቹ፣ “እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ፤ የሚከተለኝም የሕይወት ብርሃን ይሆንለታል እንጂ ከቶ በጨለማ አይመላለስም” አላቸው።
13ፈሪሳውያንም፣ “አንተ ስለ ራስህ ስለምትመሰክር ምስክርነትህ ተቀባይነት የለውም” አሉት።
14ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፤ “እኔ ስለ ራሴ ብመሰክር ከየት እንደ መጣሁና ወዴት እንደምሄድ ስለማውቅ ምስክርነቴ እውነት ነው፤ እናንተ ግን ከየት እንደ መጣሁ ወይም ወዴት እንደምሄድ የምታውቁት ነገር የለም። 15እናንተ እንደ ሰው አስተሳሰብ ትፈርዳላችሁ፤ እኔ በማንም አልፈርድም፤ 16ብፈርድም፣ ከላከኝ ከአብ ጋር እንጂ ብቻዬን ስላልሆንሁ ፍርዴ ትክክል ነው። 17የሁለት ሰዎች ምስክርነት ተቀባይነት እንዳለው በሕጋችሁ ተጽፏል። 18ስለ ራሴ የምመሰክር አንዱ እኔ ነኝ፤ ሌላውም ምስክሬ የላከኝ አብ ነው።”
19ከዚያም፣ “አባትህ የት ነው?” አሉት።
ኢየሱስም፣ “አባቴንም እኔንም አታውቁም፤ እኔን ብታውቁኝ ኖሮ፣ አባቴንም ባወቃችሁ ነበር” ሲል መለሰላቸው። 20ኢየሱስ ይህን የተናገረው በቤተ መቅደሱ ግቢ፣ በግምጃ ቤት አጠገብ ሲያስተምር ነበር፤ ይሁን እንጂ ጊዜው ገና ስላልደረሰ ማንም አልያዘውም።
21ኢየሱስም እንደ ገና፣ “እኔ እሄዳለሁ፤ እናንተም ትፈልጉኛላችሁ፤ በኀጢአታችሁም ትሞታላችሁ፤ እኔ ወደምሄድበት ግን ልትመጡ አትችሉም” አላቸው።
22አይሁድም፣ “ ‘እኔ ወደምሄድበት ልትመጡ አትችሉም’ ያለው ራሱን ሊገድል ይሆን?” አሉ።
23እርሱ ግን እንዲህ አላቸው፤ “እናንተ ከታች ናችሁ፤ እኔ ከላይ ነኝ፤ እናንተ ከዚህ ዓለም ናችሁ፤ እኔ ከዚህ ዓለም አይደለሁም። 24በኀጢአታችሁ እንደምትሞቱ ነግሬአችኋለሁ፤ እኔ እርሱ ነኝ#8፥24 ወይም ያ ያልሁት እርሱ እኔ ነኝ፤ እንዲሁም 28 ይመ ስላችሁ እኔ እርሱ እንደ ሆንሁ ካላመናችሁ፣ በኀጢአታችሁ ትሞታላችሁና።”
25እነርሱም፣ “ለመሆኑ፣ አንተ ማን ነህ?” አሉት።
ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “እስካሁን የነገርኋችሁ እኔ እርሱ ነኝ፤ 26በእናንተ ላይ ብዙ የምናገረውና ብዙ የምፈርደው ነገር አለኝ፤ ዳሩ ግን የላከኝ ታማኝ ነው፤ ከእርሱም የሰማሁትን ለዓለም እናገራለሁ።”
27እነርሱም ስለ አብ እየነገራቸው እንደ ነበር አላስተዋሉም። 28ስለዚህ ኢየሱስ እንዲህ አለ፤ “የሰው ልጅን ከፍ ከፍ ባደረጋችሁት ጊዜ፣ ያ ያልሁት እርሱ እኔ እንደ ሆንሁና አብ ያስተማረኝን እንደምናገር፣ በራሴም ፈቃድ ምንም እንደማላደርግ ታውቃላችሁ፤ 29የላከኝ እርሱ ከእኔ ጋር ነው፤ ምንጊዜም የሚያስደስተውን ስለማደርግ ብቻዬን አልተወኝም።” 30ይህንም እንደ ተናገረ ብዙዎች በእርሱ አመኑ።
የአብርሃም ልጆች
31ኢየሱስም በእርሱ ያመኑትን አይሁድ እንዲህ አላቸው፤ “በትምህርቴ ብትጸኑ እናንተ በእውነት ደቀ መዛሙርቴ ናችሁ፤ 32እውነትንም ታውቃላችሁ፤ እውነትም ነጻ ያወጣችኋል።”
33እነርሱም መልሰው፣ “እኛ የአብርሃም ልጆች ነን#8፥33 በግሪኩ ዘር ይላል፤ 37 ይመ፤ ለማንም ባሪያዎች ሆነን አናውቅም፤ ታዲያ፣ ‘ነጻ ትወጣላችሁ’ እንዴት ትለናለህ?” አሉት።
34ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “እውነት እላችኋለሁ፤ ኀጢአት የሚያደርግ የኀጢአት ባሪያ ነው፤ 35ባሪያ ለዘለቄታ በቤተ ሰቡ ውስጥ አይኖርም፤ ልጅ ግን ምንጊዜም በቤት ይኖራል። 36እንግዲህ ወልድ ነጻ ካወጣችሁ፣ በእውነት ነጻ ትሆናላችሁ። 37የአብርሃም ልጆች መሆናችሁን ዐውቃለሁ፤ ነገር ግን ቃሌን ስለማትቀበሉ ልትገድሉኝ ቈርጣችሁ ተነሥታችኋል። 38እኔ በአባቴ ዘንድ ያየሁትን እናገራለሁ፤ እናንተም ከአባታችሁ የሰማችሁትን ታደርጋላችሁ።”#8፥38 ወይም ስለዚህ ከአባታችሁ የሰማችሁትን አድርጉ
39እነርሱም፣ “አባታችንስ አብርሃም ነው” ብለው መለሱለት።
ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፤ “የአብርሃም ልጆችስ ብትሆኑ#8፥39 አንዳንድ የጥንት ቅጆች የአብርሃም ልጆች ከሆናችሁ ይላሉ።፣ አብርሃም የሠራውን ትሠሩ ነበር። 40ከእግዚአብሔር ሰምቼ እውነቱን የነገርኋችሁን እኔን ለመግደል ቈርጣችሁ ተነሥታችኋል፤ አብርሃም ግን እንዲህ አላደረገም። 41እናንተ የምታደርጉት አባታችሁ የሚያደርገውን ነው።”
እነርሱም፣ “እኛስ በዝሙት የተወለድን አይደለንም፤ አባታችንም አንዱ እግዚአብሔር ብቻ ነው” ሲሉ መለሱለት።
የዲያብሎስ ልጆች
42ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፤ “እግዚአብሔር አባታችሁ ቢሆን ኖሮ፣ እኔ ከእግዚአብሔር ወጥቼ መጥቻለሁና፣ በወደዳችሁኝ ነበር፤ እርሱ ላከኝ እንጂ በገዛ ራሴ አልመጣሁም። 43የምናገረውን ለምን አታስተውሉም? ምክንያቱም ቃሌን መስማት ስለማትችሉ ነው። 44እናንተ የአባታችሁ የዲያብሎስ ናችሁ፤ የአባታችሁንም ፍላጎት ለመፈጸም ትሻላችሁ። እርሱ ከመጀመሪያ ነፍሰ ገዳይ ነበር፤ በእርሱ ዘንድ እውነት ስለሌለ በእውነት አልጸናም፤ እርሱ ሐሰተኛ፣ የሐሰትም አባት በመሆኑ ሐሰትን ሲናገር፣ የሚናገረው ከራሱ አፍልቆ ነው፤ 45እኔ ግን እውነት ስለምናገር አታምኑኝም። 46ከእናንተ ስለ ኀጢአት በማስረጃ ሊከስሰኝ የሚችል አለን? እውነት የምናገር ከሆነ፣ ለምን አታምኑኝም? 47ከእግዚአብሔር የሆነ እግዚአብሔር የሚለውን ይሰማል፤ እናንተ ግን ከእግዚአብሔር ስላልሆናችሁ አትሰሙም።”
ኢየሱስ ስለ ራሱ የተናገረው
48አይሁድም መልሰው፣ “አንተ ሳምራዊ ነህ፤ ደግሞም ጋኔን ዐድሮብሃል ማለታችን ትክክል አይደለምን?” አሉት።
49ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “እኔስ አባቴን አከብረዋለሁ እንጂ ጋኔን አላደረብኝም፤ እናንተ ግን ታዋርዱኛላችሁ። 50እኔ የራሴን ክብር አልፈልግም፤ የሚፈልግ ግን አለ፤ ፈራጁም እርሱ ነው። 51እውነት እላችኋለሁ፤ ማንም ቃሌን ቢጠብቅ፣ ሞትን ፈጽሞ አያይም።”
52አይሁድም እንዲህ አሉት፤ “ጋኔን እንዳለብህ አሁን ዐወቅን፤ አብርሃም ሞተ፤ ነቢያትም እንዲሁ፤ አንተ ግን ማንም ቃልህን ቢጠብቅ ሞትን ፈጽሞ እንደማይቀምስ ትናገራለህ። 53አንተ ከአባታችን ከአብርሃም ትበልጣለህን? እርሱ ሞተ፤ ነቢያቱም እንዲሁ፤ ለመሆኑ አንተ ማን ነኝ ልትል ነው?”
54ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “እኔ ራሴን ባከብር፣ ክብሬ ከንቱ ነው፤ የሚያከብረኝ ግን እናንተ አምላካችን የምትሉት አባቴ ነው። 55እናንተ ባታውቁትም እኔ ዐውቀዋለሁ፤ አላውቀውም ብል፣ እኔም እንደ እናንተው ሐሰተኛ እሆናለሁ። እኔ ግን ዐውቀዋለሁ፤ ቃሉንም እጠብቃለሁ። 56አባታችሁ አብርሃም ቀኔን ለማየት ተስፋ በማድረግ ተደሰተ፤ አየም፤ ሐሤትም አደረገ።”
57አይሁድም፣ “ገና አምሳ ዓመት ያልሞላህ፣ አንተ አብርሃምን አይተሃል!” አሉት።
58ኢየሱስም፣ “እውነት እላችኋለሁ፤ አብርሃም ከመወለዱ በፊት እኔ፣ እኔ ነኝ” አላቸው። 59በዚህን ጊዜ ሊወግሩት ድንጋይ አነሡ፤ ኢየሱስ ግን ተሰወረባቸው፤ ከቤተ መቅደስም ወጥቶ ሄደ።

Tällä hetkellä valittuna:

ዮሐንስ 8: NASV

Korostus

Jaa

Kopioi

None

Haluatko, että korostuksesi tallennetaan kaikille laitteillesi? Rekisteröidy tai kirjaudu sisään