ዘፍጥረት 17
17
የግዝረት ኪዳን
1አብራም ዕድሜው 99 ዓመት በሆነ ጊዜ፣ እግዚአብሔር (ያህዌ) ተገልጦለት እንዲህ አለው፤ “እኔ ኤልሻዳይ#17፥1 ሁሉን የሚገዛ ማለት ነው። ነኝ፤ በፊቴ ተመላለስ፤ ነቀፋም አይኑርብህ፤ 2በእኔና በአንተ መካከል የተመሠረተውን ኪዳን አጸናለሁ፤ ዘርህንም እጅግ አበዛለሁ።”
3አብራም በግንባሩ መሬት ላይ ተደፋ፤ እግዚአብሔርም (ኤሎሂም) እንዲህ አለው፤ 4“እነሆ፤ የምገባልህ ኪዳን ይህ ነው፤ የብዙ ሕዝቦች አባት ትሆናለህ። 5ከእንግዲህ ወዲያ ስምህ አብራም#17፥5 አብራም ማለት የከበረ አባት ማለት ነው። መባሉ ቀርቶ አብርሃም ይሆናል፤ የብዙ ሕዝቦች አባት አድርጌሃለሁና። 6ዘርህን እጅግ አበዛለሁ፤ ብዙ ሕዝብም አደርግሃለሁ፤ ነገሥታትም ከአንተ ይወጣሉ። 7በእኔና በአንተ፣ ከአንተም በኋላ ከዘርህ ጋር ከትውልድ እስከ ትውልድ የዘላለም ኪዳኔን እመሠርታለሁ፤ በዚህም የአንተና ከአንተም በኋላ የዘርህ አምላክ (ኤሎሂም) እሆናለሁ። 8ይህችን አሁን በእንግድነት የምትኖርባትን የከነዓንን ምድር በሙሉ ለአንተና ከአንተም በኋላ ለዘርህ ለዘላለም ርስት አድርጌ እሰጣለሁ፤ አምላካቸውም (ኤሎሂም) እሆናለሁ።”
9ከዚያም እግዚአብሔር (ኤሎሂም) አብርሃምን እንዲህ አለው፤ “በአንተም በኩል፣ አንተና ከአንተ በኋላ የሚመጣው ዘርህ ከትውልድ እስከ ትውልድ ኪዳኔን ትጠብቃላችሁ። 10አንተና ከአንተም በኋላ የሚመጣው ዘርህ የምትጠብቁት ኪዳን ይህ ነው፤ በመካከላችሁ ያለ ወንድ ሁሉ ይገረዝ። 11ስለዚህ ሁላችሁም ሸለፈታችሁን ትገረዛላችሁ፤ ይህም በእኔና በእናንተ መካከል ላለው ኪዳን ምልክት ይሆናል። 12የሚመጣውም ትውልድ ሁሉ፣ ማንኛውም ወንድ ልጅ፣ ስምንት ቀን ሲሞላው ይገረዝ፤ እንደዚሁም በቤትህ የተወለደውና ከውጭ በገንዘብ የተገዛ ባዕድ ሁሉ ይገረዝ። 13በቤትህ የተወለደም ሆነ በገንዘብህ የተገዛ ሁሉ መገረዝ አለበት፤ በሥጋችሁ የሚፈጸመው ይህ ኪዳኔ የዘላለም ኪዳን ይሆናል። 14የሥጋ ሸለፈቱን ያልተገረዘ ማንኛውም ወንድ ኪዳኔን በማፍረሱ ከወገኖቹ ይወገድ።”
15እግዚአብሔር (ኤሎሂም) አብርሃምን እንዲህ አለው፤ “ሦራን ከእንግዲህ ሦራ ብለህ አትጠራትም፤ ስሟ ከዛሬ ጀምሮ ሣራ ይሁን። 16እኔ እባርካታለሁ ከእርሷም ወንድ ልጅ እሰጥሃለሁ፤ የብዙም ሕዝቦች እናት ትሆን ዘንድ እባርካታለሁ፤ የሕዝቦችም ነገሥታት ከእርሷ ይወጣሉ።”
17አብርሃምም በግንባሩ መሬት ላይ ተደፋ፤ ሣቀና በልቡ፣ “እንዲያው ምንስ ቢሆን የመቶ ዓመት ሽማግሌ የልጅ አባት መሆን ይችላልን? ሣራስ በዘጠና ዓመቷ ልጅ መውለድ ትችላለችን?” አለ። 18አብርሃም እግዚአብሔርን (ኤሎሂም)፣ “እስማኤልን ብቻ ባርከህ ባኖርህልኝ” አለው።
19እግዚአብሔርም (ኤሎሂም) እንዲህ አለ፤ “ይሁን እሺ፤ ነገር ግን ሚስትህ ሣራ ወንድ ልጅ ትወልድልሃለች፤ ስሙንም ይስሐቅ#17፥19 ይስሐቅ ማለት ይሥቃል ማለት ነው። ብለህ ትጠራዋለህ፤ እኔም ከእርሱ በኋላ ለዘሩ ሁሉ የሚሆን የዘላለም ኪዳን ከእርሱ ጋር እገባለሁ። 20ስለ እስማኤልም ቢሆን ልመናህን ሰምቼሃለሁ፤ እርሱንም እባርከዋለሁ፤ ፍሬያማም አደርገዋለሁ፤ እጅግም አበዛዋለሁ፤ የዐሥራ ሁለት አለቆች አባት ይሆናል፤ ታላቅም ሕዝብ አደርገዋለሁ። 21ኪዳኔን ግን የዛሬ ዓመት በዚሁ ጊዜ ሣራ ከምትወልድልህ ልጅ፣ ከይስሐቅ ጋር አደርጋለሁ።” 22እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ከአብርሃም ጋር መነጋገሩን ከፈጸመ በኋላ ወደ ላይ ወጣ።
23በዚያችም ዕለት አብርሃም እግዚአብሔር (ያህዌ) ባዘዘው መሠረት ልጁን እስማኤልን፣ በቤቱ ውስጥ የተወለዱትንና ከውጭ በገንዘቡ የገዛቸውን ወንዶች በሙሉ ገረዛቸው። 24አብርሃም ሲገረዝ ዕድሜው 99 ዓመት ነበር። 25ልጁም እስማኤል ሲገረዝ 13 ዓመቱ ነበር። 26አብርሃምና ልጁ እስማኤል፣ ሁለቱም በዚያኑ ቀን ተገረዙ። 27በአብርሃም ቤት ያሉ ወንዶች ሁሉ፣ በቤቱ የተወለዱትም ሆኑ ከውጭ በገንዘብ የተገዙ ከእርሱ ጋር ተገረዙ።
Tällä hetkellä valittuna:
ዘፍጥረት 17: NASV
Korostus
Jaa
Kopioi
Haluatko, että korostuksesi tallennetaan kaikille laitteillesi? Rekisteröidy tai kirjaudu sisään
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጅ መብት © 2001 በ Biblica, Inc.
ፈቃድ የተገኘባቸው ናቸው። መብቱ በመላው ዓለም በሕግ የተጠበቀ።
Holy Bible, New Amharic Standard Version™ (Addisu Medebegna Tirgum™)
Copyright © 2001 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.