ኦሪት ዘፍጥረት 16
16
አጋርና ይስማኤል
1የአብራም ሚስት ሦራ ግን ልጅ አልወለደችለትም ነበር፤ ስምዋ አጋር የተባለ ግብፃዊት አገልጋይም ነበረቻት። 2ሦራም አብራምን፥ “እነሆ፥ እንዳልወልድ እግዚአብሔር ዘጋኝ፤ ከእርስዋ ትወልድ ዘንድ ወደ አገልጋዬ ሂድ” አለችው። አብራምም የሚስቱን የሦራን ቃል ሰማ። 3አብራምም በከነዓን ምድር ዐሥር ዓመት ከተቀመጠ በኋላ፥ የአብራም ሚስት ሦራ ግብፃዊት አገልጋይዋን አጋርን ወስዳ ለአብራም ሚስት ትሆነው ዘንድ ሰጠችው። 4አብራምም ወደ አጋር ገባ፤ ፀነሰችም፤ እንደ ፀነሰችም ባየች ጊዜ እመቤቷን ማክበርዋን ተወች። 5ሦራም አብራምን፥ “ከአንተ የተነሣ እገፋለሁ፤ እኔ አገልጋዬን በብብትህ ሰጠሁህ፤ እንደ ፀነሰችም ባየች ጊዜ እኔን ማክበርን ተወች፤ እግዚአብሔር በእኔና በአንተ መካከል ይፍረድ” አለችው። 6አብራምም ሚስቱን ሦራን፥ “እነሆ፥ አገልጋይሽ በእጅሽ ናት፤ እንደ ወደድሽ አድርጊባት” አላት። ሦራም አጋርን አሠቃየቻት፤ ከእርስዋም ኰበለለች።
7የእግዚአብሔር መልአክም በውኃ ምንጭ አጠገብ በሱር በረሃ በመንገድ አገኛት። 8የእግዚአብሔርም መልአክ፥ “የሦራ አገልጋይ አጋር ሆይ፥ ከወዴት መጣሽ? ወዴትስ ትሄጂያለሽ?” አላት። እርስዋም፥ “እኔ ከእመቤቴ ከሦራ ፊት እኰበልላለሁ” አለች። 9የእግዚአብሔር መልአክም፥ “ወደ እመቤትሽ ተመለሺ፤ ከእጅዋም በታች ራስሽን ዝቅ አድርጊ” አላት። 10እግዚአብሔርም#ግሪክ ሰባ. ሊ. እና ዕብ. “የእግዚአብሔር መልአክ” ይላል። “ከብዛቱ የተነሣ እስከማይቈጠር ድረስ ዘርሽን እጅግ አበዛለሁ፥” አላት። 11የእግዚአብሔር መልአክም አላት፥ “እነሆ፥ አንቺ ፀንሰሻል፤ ወንድ ልጅንም ትወልጃለሽ፤ ስሙንም ይስማኤል ብለሽ ትጠሪዋለሽ፤ እግዚአብሔር ሥቃይሽን ሰምቶአልና። 12እርሱም የበረሃ ሰው ይሆናል፤#ዕብ. “እርሱ የምድረ በዳ አህያን የሚመስል ሰው ይሆናል” ይላል። እጁ በሁሉ ላይ ይሆናል፤ የሁሉም እጅ ደግሞ በእርሱ ላይ ይሆናል፤ እርሱም በወንድሞቹ ሁሉ ፊት ይኖራል።” 13አጋርም ይናገራት የነበረውን የእግዚአብሔርን ስም#ዕብ. “ኤልሮኢ ብላ” ይላል። ጠራች፤ “አቤቱ የራራህልኝ አንተ ነህ፤ የተገለጠልኝን በፊቴ አይችዋለሁና።” 14ስለዚህም የዚያን ጕድጓድ ስም “በፊቴ የተገለጠልኝ የእርሱ ጕድጓድ” ብላ ጠራችው፤ እርሱም በቃዴስና በባሬድ መካከል ነው። አጋርም ተመለሰች።#“አጋርም ተመለሰች” የሚለው በግሪክ ሰባ. ሊ. እና በዕብ. የለም።
15ከዚህም በኋላ አጋር ለአብራም ወንድ ልጅን ወለደችለት፤ አብራምም አጋር የወለደችለትን የሕፃኑን ስም ይስማኤል ብሎ ጠራው። 16አጋር ይስማኤልን በወለደችለት ጊዜ አብራም የሰማንያ አምስት#ዕብ. እና ግሪክ ሰባ. ሊ. “ሰማንያ ስድስት” ይላል። ዓመት ሰው ነበረ።
Actualmente seleccionado:
ኦሪት ዘፍጥረት 16: አማ2000
Destacar
Compartir
Copiar
¿Quieres guardar tus resaltados en todos tus dispositivos? Regístrate o Inicia sesión