ሉቃስ 11
11
ኢየሱስ ያስተማረው ጸሎት
11፥2-4 ተጓ ምብ – ማቴ 6፥9-13
11፥9-13 ተጓ ምብ – ማቴ 7፥7-11
1አንድ ቀን ኢየሱስ በአንድ ስፍራ ይጸልይ ነበር፤ ጸሎቱንም እንደ ጨረሰ፣ ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ፣ “ጌታ ሆይ፤ ዮሐንስ ደቀ መዛሙርቱን ጸሎት እንዳስተማራቸው አንተም መጸለይን አስተምረን” አለው።
2እርሱም እንዲህ አላቸው፤ “ስትጸልዩ እንዲህ በሉ፤
“ ‘አባታችን # 11፥2 አንዳንድ ቅጆች በሰማይ የምትኖር አባታችን ይላሉ። ሆይ፤
ስምህ ይቀደስ፤
መንግሥትህ ትምጣ፤ # 11፥2 አንዳንድ ቅጆች ፈቃድህ በሰማይ እንደ ሆነች እንዲሁ በምድር ትሁን ይላሉ።
3 የዕለት እንጀራችንን በየዕለቱ ስጠን፤
4 በደላችንን ይቅር በለን፤
እኛም የበደሉንን # 11፥4 አንዳንድ ቅጆች በእኛ ላይ ኀጢአት የሠሩትን ይላሉ። ሁሉ ይቅር ብለናልና።
ወደ ፈተናም አታግባን፤ ከክፉው አድነን እንጂ።’ ” # 11፥4 አንዳንድ ቅጆች ከክፉው አድነን እንጂ የሚለው የላቸውም።
5ደግሞም እንዲህ አላቸው፤ “ከእናንተ አንዱ ወዳጅ ቢኖረውና በእኩለ ሌሊት ወደ እርሱ ሄዶ፣ ‘ወዳጄ ሆይ፤ ሦስት እንጀራ አበድረኝ፤ 6አንድ ባልንጀራዬ ከመንገድ መጥቶብኝ የማቀርብለት ምንም ነገር የለኝምና’ ብሎ ለመነው እንበል።
7 “በቤት ውስጥ ያለውም፣ ‘አታስቸግረኝ፤ በሩ ተቈልፏል፤ ልጆቼም አብረውኝ ተኝተዋል፤ ከእንግዲህ ተነሥቼ ልሰጥህ አልችልም’ ይለዋልን? 8እላችኋለሁ፤ ወዳጁ በመሆኑ ተነሥቶ ባይሰጠው እንኳ፣ ስለ ንዝነዛው#11፥8 ወይም ስለ ብዙ ልመናው ብቻ የሚፈልገውን ሁሉ ይሰጠዋል።
9 “ስለዚህ እላችኋለሁ፤ ለምኑ ይሰጣችኋል፤ ፈልጉ ታገኛላችሁ፤ በር አንኳኩ ይከፈትላችኋል፤ 10ምክንያቱም የሚለምን ሁሉ ይቀበላል፤ የሚፈልግም ያገኛል፤ በር ለሚያንኳኳም ይከፈትለታል።
11 “ከእናንተ መካከል አባት ሆኖ ሳለ ልጁ # 11፥11 አንዳንድ ቅጆች ዳቦ ቢለምነው ድንጋይ የሚሰጠው አለን? የሚል አላቸው። ዓሣ ቢለምነው እባብ የሚሰጠው ይኖራልን? 12ወይስ ዕንቍላል ቢለምነው ጊንጥ ይሰጠዋልን? 13እናንተ ክፉዎች ሆናችሁ ሳላችሁ፣ ለልጆቻችሁ መልካም ስጦታን መስጠት ካወቃችሁበት፣ የሰማዩ አባታችሁ ታዲያ ለሚለምኑት መንፈስ ቅዱስን እንዴት አብልጦ አይሰጥ!”
ጌታ ኢየሱስና ብዔልዜቡል
11፥14-15፡17-22፡24-26 ተጓ ምብ – ማቴ 12፥22፡24-29፡43-45
11፥17-22 ተጓ ምብ – ማር 3፥23-27
14አንድ ቀን ኢየሱስ ድዳ ጋኔን ያወጣ ነበር፤ ጋኔኑም ከወጣለት በኋላ ድዳው ሰው ተናገረ፤ ሕዝቡም ተገረመ። 15አንዳንዶቹ ግን፣ “በአጋንንት አለቃ፣ በብዔልዜቡል#11፥15 ግሪኩ ብዔዜቡል ወይም ብዔል ዜብል ይላል፤ እንዲሁም 18፡19 ይመ፣ አጋንንትን ያወጣል” አሉ፤ 16አንዳንዶቹ ደግሞ ሊፈታተኑት ከሰማይ ምልክት እንዲያሳያቸው ከእርሱ ይፈልጉ ነበር።
17ኢየሱስ ግን ሐሳባቸውን ዐውቆ እንዲህ አላቸው፤ “እርስ በርሱ የሚከፋፈል መንግሥት ሁሉ ይጠፋል፤ የሚለያይ ቤትም ይወድቃል። 18ሰይጣንም እርስ በርሱ ከተከፋፈለ፣ መንግሥቱ እንዴት ይጸናል? አጋንንትን በብዔልዜቡል እንደማወጣ ትናገራላችሁና። 19እንግዲህ እኔ አጋንንትን የማወጣው በብዔልዜቡል ከሆነ፣ ልጆቻችሁ በማን ያወጧቸው ይሆን? ስለዚህ እነርሱ ፈራጆች ይሆኑባችኋል። 20እኔ ግን አጋንንትን የማወጣው በእግዚአብሔር ጣት ከሆነ፣ የእግዚአብሔር መንግሥት ወደ እናንተ እንደ መጣች ዕወቁ።
21 “ብርቱ ሰው በሚገባ ታጥቆ ቤቱን ከጠበቀ፣ ንብረቱ በሰላም ይቀመጣል። 22ነገር ግን ይበልጥ ብርቱ የሆነ ሰው መጥቶ ካጠቃውና ካሸነፈው ታምኖበት የነበረውን ትጥቁን ያስፈታዋል፤ ምርኮውንም ወስዶ ለሌሎች ያካፍላል።
23 “ከእኔ ጋር ያልሆነ ይቃወመኛል፤ ከእኔ ጋር የማይሰበስብም ይበትናል።
24 “ርኩስ # 11፥24 ወይም ክፉ መንፈስ ከሰው ሲወጣ ዕረፍት ፍለጋ ውሃ በሌለበት ስፍራ ይንከራተታል፤ ሳያገኝም ሲቀር፣ ‘ወደ ወጣሁበት ቤቴ እመለሳለሁ’ ይላል፤ 25ሲመለስም ቤቱ ተጠራርጐና ተስተካክሎ ያገኘዋል። 26ከዚያም በኋላ ሄዶ ሌሎች ከእርሱ የከፉ ሰባት አጋንንት ይዞ ይመጣል፤ ገብተውበትም በዚያ ይኖራሉ፤ ለዚያ ሰው ከመጀመሪያው ይልቅ የኋለኛው ሁኔታ የከፋ ይሆንበታል።”
27ኢየሱስ ይህን እየተናገረ እያለ፣ ከሕዝቡ መካከል አንዲት ሴት ድምፅዋን ከፍ አድርጋ፣ “የተሸከመችህ ማሕፀንና የጠባሃቸው ጡቶች ብፁዓን ናቸው” አለችው።
28እርሱ ግን፣ “ብፁዓንስ የእግዚአብሔርን ቃል ሰምተው የሚታዘዙት ናቸው” አለ።
የዮናስ ምልክትነት
11፥29-32 ተጓ ምብ – ማቴ 12፥39-42
29ብዙ ሕዝብ እየተሰበሰበ በሄደ ጊዜ ኢየሱስ እንዲህ ይል ጀመር፤ “ይህ ትውልድ ክፉ ነው፤ ታምራዊ ምልክት ይፈልጋል፤ ነገር ግን ከዮናስ ምልክት በስተቀር ሌላ አይሰጠውም። 30ምክንያቱም ዮናስ ለነነዌ ሰዎች ምልክት እንደ ሆናቸው የሰው ልጅም ለዚህ ትውልድ ምልክት ይሆናል። 31የደቡቧ ንግሥት በፍርድ ጊዜ ከዚህ ትውልድ ጋር ተነሥታ ትፈርድባቸዋለች፤ እርሷ የሰሎሞንን ጥበብ ለመስማት ከምድር ዳርቻ መጥታለችና፤ እነሆ፤ ከሰሎሞን የሚበልጥ እዚህ አለ። 32የነነዌ ሰዎችም በፍርድ ጊዜ ከዚህ ትውልድ ጋር ተነሥተው ይፈርዱበታል፤ እነርሱ የዮናስን ስብከት ሰምተው ንስሓ ገብተዋልና፤ እነሆ፣ ከዮናስ የሚበልጥ እዚህ አለ።
የሰውነት መብራት
11፥34፡35 ተጓ ምብ – ማቴ 6፥22፡23
33 “መብራት አብርቶ በስውር ቦታ ወይም ከእንቅብ በታች የሚያስቀምጥ ማንም የለም፤ ይልቁን የሚገቡ ሰዎች ብርሃኑን እንዲያዩ በመቅረዝ ላይ ያስቀምጠዋል። 34የሰውነትህ ብርሃን ዐይንህ ናት፤ ዐይንህ ጤናማ ስትሆን መላ ሰውነትህ ብሩህ ይሆናል፤ ዐይንህ ታማሚ ከሆነች ግን መላ ሰውነትህ የጨለመ ይሆናል። 35ስለዚህ በውስጥህ ያለው ብርሃን ጨለማ እንዳይሆን ተጠንቀቅ። 36እንግዲህ ሰውነትህ ሁሉ ብሩህ ከሆነና የጨለመ የሰውነት ክፍል ከሌለበት፣ የሰውነትህ ሁለንተና መብራት በወገግታው ያበራልህ ያህል ይደምቃል።”
ስድስት ዐይነት ወዮታ
37ኢየሱስ ንግግሩን እንደ ጨረሰ፣ አንድ ፈሪሳዊ ከእርሱ ጋር ምግብ እንዲበላ ጋበዘው፤ እርሱም አብሮት ገብቶ በማእድ ተቀመጠ። 38ፈሪሳዊውም ኢየሱስ ከምግብ በፊት እጁን እንዳልታጠበ ባየ ጊዜ ተደነቀ።
39ጌታም እንዲህ አለው፤ “አሁን እናንተ ፈሪሳውያን የጽዋውንና የወጭቱን ውጫዊ ክፍል ታጸዳላችሁ፤ ውስጣችሁ ግን በሥሥትና በክፋት የተሞላ ነው። 40እናንት ሞኞች፤ የውጭውን የፈጠረ የውስጡንም አልፈጠረምን? 41ነገር ግን በውስጥ ያለውን ምጽዋት#11፥41 ወይም ያላችሁን አድርጋችሁ ስጡ፤ በዚህ ጊዜ ሁሉም ንጹሕ ይሆንላችኋል።
42 “እናንት ፈሪሳውያን ግን ወዮላችሁ፤ ከአዝሙድና ከጤና አዳም እንዲሁም ከአትክልት ሁሉ ዐሥራት ታወጣላችሁ፤ ሆኖም ፍትሕንና እግዚአብሔርን መውደድ ቸል ትላላችሁ፤ ነገር ግን ያንን ሳትተዉ ይህኛውን ማድረግ በተገባችሁ ነበር።
43 “እናንት ፈሪሳውያን ወዮላችሁ፤ በምኵራብ የክብር መቀመጫ፣ በገበያ መካከልም እጅ መነሣትን ትወድዳላችሁና።
44 “ሰዎች ሳያውቁ በላዩ የሚሄዱበትን የተሰወረ መቃብር ስለምትመስሉ፣ ወዮላችሁ።”
45ከሕግ ዐዋቂዎች አንዱ መልሶ “መምህር ሆይ፤ እንዲህ ስትናገር እኮ እኛንም መስደብህ ነው” ሲል መለሰለት።
46ኢየሱስም እንዲህ አለ፤ “እናንት ሕግ ዐዋቂዎችም ደግሞ ወዮላችሁ፤ ሰዎች ሊሸከሙ የማይችሉትን ከባድ ሸክም ታሸክማላችሁ፤ እናንተ ራሳችሁ ግን በጣታችሁ እንኳ አትነኩትም።
47 “አባቶቻችሁ የገደሏቸውን የነቢያትን መቃብር ስለምታበጃጁ፣ ወዮላችሁ፤ 48እንግዲህ የአባቶቻችሁን ሥራ የምታጸኑ ምስክሮች ናችሁ፤ እነርሱ ነቢያትን ገደሉ፤ እናንተም መቃብራቸውን ታበጃጃላችሁ። 49ስለዚህም የእግዚአብሔር ጥበብ እንዲህ አለች፤ ‘ነቢያትንና ሐዋርያትን እልክላቸዋለሁ፤ እነርሱ አንዳንዶቹን ይገድላሉ፤ ሌሎችንም ያሳድዳሉ።’ 50ስለዚህ ይህ ትውልድ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ስለ ፈሰሰው፣ ስለ ነቢያት ሁሉ ደም ተጠያቂ ነው፤ 51ከአቤል ደም ጀምሮ፣ በመሠዊያውና በቤተ መቅደሱ መካከል እስከ ፈሰሰው እስከ ዘካርያስ ደም ድረስ ይፈለግበታል፤ አዎን፣ እላችኋለሁ፤ ይህ ትውልድ ለዚህ ተጠያቂ ነው።
52 “እናንት ሕግ ዐዋቂዎች ወዮላችሁ፤ የዕውቀትን መክፈቻ ነጥቃችሁ ወስዳችኋልና፤ እናንተ ራሳችሁ አልገባችሁበትም፤ የሚገቡትንም ከልክላችኋል።”
53ኢየሱስ ከዚያ ከወጣ በኋላ፣ ጸሐፍትና ፈሪሳውያን ክፉኛ ይቃወሙትና በጥያቄም ያዋክቡት ጀመር፤ 54ከአፉ በሚወጣውም ቃል ሊያጠምዱት ያደቡ ነበር።
Currently Selected:
ሉቃስ 11: NASV
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጅ መብት © 2001 በ Biblica, Inc.
ፈቃድ የተገኘባቸው ናቸው። መብቱ በመላው ዓለም በሕግ የተጠበቀ።
Holy Bible, New Amharic Standard Version™ (Addisu Medebegna Tirgum™)
Copyright © 2001 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.