ዘፍጥረት 3
3
የሰው ውድቀት
1እባብ እግዚአብሔር አምላክ (ያህዌ ኤሎሂም) ከፈጠራቸው የዱር አራዊት ሁሉ ተንኰለኛ ነበረ፤ ሴቲቱንም፣ “በርግጥ እግዚአብሔር (ኤሎሂም)፣ ‘በአትክልቱ ስፍራ ካሉ ዛፎች ከማናቸውም እንዳትበሉ’ ብሏልን?” አላት።
2ሴቲቱም እባቡን እንዲህ አለችው፤ “በአትክልቱ ስፍራ ካሉት ዛፎች ፍሬ መብላት እንችላለን፤ 3ነገር ግን እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ‘በአትክልቱ ስፍራ መካከል ከሚገኘው ዛፍ ፍሬ እንዳትበሉ፤ እንዳትነኩትም፤ አለዚያ ትሞታላችሁ’ ብሏል።”
4እባቡም ሴቲቱን እንዲህ አላት፤ “መሞት እንኳ አትሞቱም፤ 5ከፍሬው በበላችሁ ጊዜ ዐይናችሁ እንደሚከፈትና መልካምና ክፉን በማወቅ፣ እንደ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) እንደምትሆኑ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ስለሚያውቅ ነው።”
6ሴቲቱ የዛፉ ፍሬ ለመብል መልካም፣ ለዐይን የሚያስደስትና ጥበብንም ለማግኘት የሚያጓጓ እንደ ሆነ ባየች ጊዜ፣ ከፍሬው ወስዳ በላች፤ ከእርሷም ጋር ለነበረው ለባሏ ሰጠችው፤ እርሱም በላ። 7የሁለቱም ዐይኖች ተከፈቱ፤ ዕራቍታቸውን መሆናቸውንም ተገነዘቡ። ስለዚህ የበለስ ቅጠል ሰፍተው አገለደሙ።
8ቀኑ መሸትሸት ሲል፣ እግዚአብሔር አምላክ (ያህዌ ኤሎሂም) በአትክልቱ ስፍራ ሲመላለስ አዳምና ሔዋን ድምፁን ሰምተው ከእግዚአብሔር አምላክ (ያህዌ ኤሎሂም) ፊት በዛፎቹ መካከል ተሸሸጉ። 9እግዚአብሔር አምላክ (ያህዌ ኤሎሂም) ግን አዳምን ተጣርቶ፣ “የት ነህ?” አለው።
10አዳምም፣ “ድምፅህን በአትክልቱ ስፍራ ሰማሁ፤ ዕራቍቴን ስለሆንሁ ፈራሁ፤ ተሸሸግሁም” ብሎ መለሰ።
11 እግዚአብሔርም፣ (ያህዌ)፣ “ዕራቍትህን መሆንህን ማን ነገረህ? ‘ከእርሱ እንዳትበላ’ ብዬ ካዘዝሁህ ዛፍ በላህን?” አለው።
12አዳምም፣ “ይህች ከእኔ ጋር እንድትኖር የሰጠኸኝ ሴት፣ እርሷ ከዛፉ ፍሬ ሰጠችኝና በላሁ” አለ።
13 እግዚአብሔር አምላክ (ያህዌ ኤሎሂም) ሴቲቱን፣ “ይህ ያደረግሽው ምንድን ነው?” አላት።
እርሷም፣ “እባብ አሳሳተኝና በላሁ” አለች።
14 እግዚአብሔር አምላክ (ያህዌ ኤሎሂም) እባብን እንዲህ አለው፤ “ይህን ስለ ሠራህ፣
“ከከብቶችና ከዱር እንስሳት ሁሉ
ተለይተህ የተረገምህ ሁን፤
በሕይወትህ ዘመን ሁሉ፣ በደረትህ
እየተሳብህ ትሄዳለህ፤
ዐፈርም ትበላለህ።
15በአንተና በሴቲቱ፣
በዘርህና በዘሯ መካከል፣
ጠላትነትን አደርጋለሁ፤
እርሱ ራስህን ይቀጠቅጣል፤#3፥15 ወይም ይመታል
አንተም ተረከዙን ትቀጠቅጣለህ።”
16ሴቲቱንም እንዲህ አላት፤
“በምጥ ጊዜ ጭንቅሽን አበዛለሁ፤
በሥቃይም ትወልጃለሽ፤
ፍላጎትሽም ወደ ባልሽ ይሆናል፤
እርሱም የበላይሽ ይሆናል።”
17አዳምንም እንዲህ አለው፤ “የሚስትህን ቃል ሰምተህ፣ ‘ከእርሱ አትብላ’ ብዬ ያዘዝሁህን ዛፍ በልተሃልና፣
“ከአንተ የተነሣ ምድር የተረገመች ትሁን፤
በሕይወትህ ዘመን ሁሉ
ምግብህን ጥረህ ግረህ ከእርሷ ታገኛለህ።
18ምድርም እሾኽና አሜከላ
ታበቅልብሃለች፤
ከቡቃያዋም ትበላለህ።
19ከምድር ስለ ተገኘህ፣
ወደ መጣህበት መሬት እስክትመለስ
ድረስ
እንጀራህን በፊትህ ላብ ትበላለህ፤
ዐፈር ነህና
ወደ ዐፈር ትመለሳለህ።”
20አዳምም#3፥20 ወይም ሰውየው የሕያዋን ሁሉ እናት ናትና ሚስቱን ሔዋን#3፥20 ሔዋን ማለት ሕያው ማለት ሳይሆን አይቀርም። ብሎ ጠራት። 21እግዚአብሔር አምላክ (ያህዌ ኤሎሂም) ከቈዳ ልብስ አዘጋጅቶ አዳምንና ሚስቱን አለበሳቸው።
22ከዚያም እግዚአብሔር አምላክ (ያህዌ ኤሎሂም)፣ “ሰው መልካምንና ክፉውን ለይቶ በማወቅ ረገድ አሁን ከእኛ እንደ አንዱ ሆኗል፤ አሁን ደግሞ እጁን ዘርግቶ ከሕይወት ዛፍ ቀጥፎ እንዳይበላ፣ ለዘላለምም እንዳይኖር ይከልከል” አለ። 23ስለዚህ የተገኘበትን ምድር እንዲያርስ፣ እግዚአብሔር አምላክ (ያህዌ ኤሎሂም) ሰውን ከዔድን የአትክልት ስፍራ አስወጣው፤ 24ሰውንም ካስወጣው በኋላ፣ ወደ ሕይወት ዛፍ የሚወስደውን መንገድ ለመጠበቅ ኪሩቤልንና በየአቅጣጫው የምትገለባበጥ ነበልባላዊ ሠይፍ ከዔድን በስተ ምሥራቅ አኖረ።#3፥24 ወይም ፊት ለፊት አስቀመጠ
Currently Selected:
ዘፍጥረት 3: NASV
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጅ መብት © 2001 በ Biblica, Inc.
ፈቃድ የተገኘባቸው ናቸው። መብቱ በመላው ዓለም በሕግ የተጠበቀ።
Holy Bible, New Amharic Standard Version™ (Addisu Medebegna Tirgum™)
Copyright © 2001 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.