YouVersion Logo
Search Icon

የማ​ቴ​ዎስ ወን​ጌል 7

7
በሌሎች ላይ መፍረድ እንደማይገባ
(ሉቃ. 6፥37-4211፥9-13)
1-2“እንዳይፈረድባችሁ አትፍረዱ፤ በምትፈርዱበት ፍርድ ይፈረድባችኋልና፤ በምትሰፍሩበትም መስፈሪያ ይሰፈርባችኋል። 3በወንድምህም ዐይን ያለውን ጉድፍ ስለምን ታያለህ፤ በዐይንህ ግን ያለውን ምሰሶ ስለ ምን አትመለከትም? 4ወይም ወንድምህን ‘ከዐይንህ ጕድፍ ላውጣ ፍቀድልኝ’ እንዴትስ ትለዋለህ? እነሆም፥ በዐይንህ ምሰሶ አለ። 5አንተ ግብዝ፤ አስቀድመህ ከዐይንህ ምሰሶውን አውጣ፤ ከዚያም በኋላ ከወንድምህ ዐይን ጕድፉን ታወጣ ዘንድ አጥርተህ ታያለህ። 6በእግራቸው እንዳይረግጡት ተመልሰውም እንዳይነክሱአችሁ፥ የተቀደሰውን ለውሾች አትስጡ፤ ዕንቁዎቻችሁንም በእሪያዎች ፊት አትጣሉ።
7“ለምኑ፤ ይሰጣችሁማል፤ ፈልጉ፤ ታገኙማላችሁ፤ መዝጊያን አንኳኩ፤ ይከፈትላችሁማል። 8የሚለምነው ሁሉ ይቀበላልና፤ የሚፈልገውም ያገኛል፤ መዝጊያንም ለሚያንኳኳ ይከፈትለታል። 9ወይስ ልጁ እንጀራ ቢለምነው ድንጋይን የሚሰጠው ከእናንተ ማን ሰው ነው? 10ዓሣስ ቢለምነው እባብን ይሰጠዋልን? 11እንኪያስ እናንተ ክፉዎች ስትሆኑ ለልጆቻችሁ መልካም ስጦታ መስጠትን ካወቃችሁ በሰማያት ያለው አባታችሁ ለሚለምኑት እንዴት አብልጦ መልካም ነገርን ይሰጣቸው! 12እንግዲህ ሰዎች ሊያደርጉላችሁ የምትወዱትን ሁሉ እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉላቸው፤ ሕግም ነቢያትም ይህ ነውና።
ስለ ጥባብዋ በር
(ሉቃ. 13፥24)
13“በጠበበው ደጅ ግቡ፤ ወደ ጥፋት የሚወስደው ደጅ ሰፊ መንገዱም ትልቅ ነውና፤ ወደ እርሱም የሚገቡ ብዙዎች ናቸው፤ 14ወደ ሕይወት የሚወስደው ደጅ የጠበበ፥ መንገዱም የቀጠነ ነውና፤ የሚያገኙትም ጥቂቶች ናቸው።
ስለ ሐሰተኞች ነቢያት
(ሉቃ. 6፥43-44)
15“የበግ ለምድ ለብሰው ከሚመጡባችሁ በውስጣቸው ግን ነጣቂዎች ተኵላዎች ከሆኑ ከሐሰተኞች ነቢያት ተጠንቀቁ። 16ከፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ። ከእሾህ ወይን ከኩርንችትስ በለስ ይለቀማልን? 17እንዲሁ መልካም ዛፍ ሁሉ መልካም ፍሬ ያደርጋል፤ ክፉም ዛፍ ክፉ ፍሬ ያደርጋል። 18መልካም ዛፍ ክፉ ፍሬ ማፍራት፥ ወይም ክፉ ዛፍ መልካም ፍሬ ማፍራት አይቻለውም። 19መልካም ፍሬ የማያፈራ ዛፍ ሁሉ ይቆረጣል፤ ወደ እሳትም ይጣላል። 20ስለዚህም ከፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ። 21በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ እንጂ ‘ጌታ ሆይ! ጌታ ሆይ!’ የሚለኝ ሁሉ መንግሥተ ሰማያት የሚገባ አይደለም። 22በዚያ ቀን ብዙዎች ‘ጌታ ሆይ! ጌታ ሆይ! በስምህ ትንቢት አልተናገርንምን? በስምህስ አጋንንትን አላወጣንምን? በስምህስ ብዙ ተአምራትን አላደረግንምን?’ ይሉኛል። 23የዚያን ጊዜም ‘ከቶ አላወቅኋችሁም፤ እናንተ አመፀኞች፥ ከእኔ ራቁ’ ብዬ እመሰክርባቸዋለሁ።
በዐለትና በአሸዋ ላይ ስለተሠሩ ቤቶች
(ሉቃ. 6፥47-49)
24“ስለዚህ ይህን ቃሌን ሰምቶ የሚያደርገው ሁሉ ቤቱን በዐለት ላይ የሠራ ልባም ሰውን ይመስላል። 25ዝናብም ወረደ ጎርፍም መጣ ነፋስም ነፈሰ ያንም ቤት ገፋው፤ በዐለት ላይም ስለ ተመሠረተ አልወደቀም። 26ይህንም ቃሌን ሰምቶ የማያደርገው ሰው ሁሉ ቤቱን በአሸዋ ላይ የሠራ ሰነፍ ሰውን ይመስላል። 27ዝናብም ወረደ ጎርፍም መጣ ነፋስም ነፈሰ ያንም ቤት መታው፤ ወደቀም፤ አወዳደቁም ታላቅ ሆነ።”
28ኢየሱስም ይህን ነገር በጨረሰ ጊዜ ሕዝቡ በትምህርቱ ተገረሙ፤ እንደ ጻፎቻቸው ሳይሆን፥ 29እንደ ባለ ሥልጣን ያስተምራቸው ነበርና።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in