YouVersion Logo
Search Icon

2ኛ መጽሐፈ መቃብያን 7

7
የሰባት ወንድማማቾች ሰማዕትነት
1እንዲሁም ሰባት ወንድማማቾች ከእናታቸው ጋር ተያዙና ታሰሩ። ንጉሡ በጅራፍና በበሬ ጅማት እያስገረፈ በሕግ የተከለከለውን የዓሣማ ሥጋ እንዲቀምሱ አስገደዳቸው። 2ከእነሱ አንዱ በወንድሞቹ ስም፥ “ከእኛ ምን ትጠይቃለህ፥ ምንስ ማወቅ ትፈለጋለህ? የአባቶቻችንን ሕግ ከማፍረስ መሞትን እንመርጣለን” አለ። 3ንጉሡ በጣም ተቆጥቶ ብረት ምጣድና ብረት ድስት በእሳት እንዲያግሉ አዘዘ። 4ብረት ምጣዱና ብረት ድስቱ በጣም በጋሉ ጊዜ ንጉሡ ያን በወንድሞቹ ስም የተናረገውን ሰው ምላሱ እንዲቆረጥ፥ የራስ ቅሉ ቆዳ እንዲገፈፍ፥ በወንድሞቹና በእናቱ ፊት እጆቹና እግሮቹ እንዲቆረጡ አዘዘ። 5በሙሉ ከቆራረጡት በኋላ ገና በሕይወቱ እያለ በብረት መጣድ ላይ አድርገው አንዲጠብሱት አዘዘ፤ ከጋለው ብረት ምጣድ ላይ ጭሱ ሲወጣ ሳለ ወንድሞቹና እናቱ ያለ ፍርሃት ለመሞት ይመካከሩ ነበር፤ እንዲህም ይሉ ነበር፤ 6“እግዚአብሔር አምላክ ያያል፤ ሙሴ እንደተናረገው በእውነት ይራራልናል፤ ሙሴ እግዚአብሔር ለአገልጋዮቹ ይራራላቸዋል ሲል መስክሮአልና”። 7የመጀመሪያው እንዲህ ሆኖ ከሞተ በኋላ ሁለተኛውን ወደሚያሠቃዩበት ቦታ ወሰዱት፤ 8የራስ ቅሉን ቆዳ ከነጠጉሩ ገፍፈው ከጣሉ በኋላ “የአካልህ ክፍሎች እያንዳንዱ ከሚበሠቃዩ የዓሣማ ሥጋ ትበላለህን?” ሲሉ ጠየቁት። 9እርሱ ግን ድምፁን ከፍ አድርጐ ተናገረ፥ “ጨካኝ አውሬዎች ከዚህ ከአሁኑ ሕይወት ትገላግሉን ይሆናል፤ የዓለም ጌታ ግን ስለ ሕጎቹ በመሞታችን ለዘለዓለም እንኖር ዘንድ ያስነሣናል”። 10ከእርሱ በኋላ ሦስተኛውን አሠቃዩት፥ ምላስህን አውጣ ሲሉት በቶሎ አወጣ እጆቹንም ያለ ምንም ፍርሃት ዘረጋላቸው። 11“እነርሱን የሰጠኝ አምላክ ነው፤ ስለ ሕጉ ስል እንቃቸዋለሁ፤ ከእርሱ እንደገና መልሼ ላገኛቸው ተስፋ አለኝ” አላቸው። 12ንጉሡና ከንጉሡ ጋር የነበሩት ሰዎች ሥቃዩን ሁሉ ከምንም በማይቆጥረው በእዚህ ወጣት ብርታት ተደነቁ፤ 13ይህ ከሞተ በኋላ አራተኛውንም በተመሳሳይ ሁኔታ አሠቃዩት፤ 14እርሱ ሊሞት ሲል እንዲህ አለ፥ “እግዚአብሔር በሰጠን ተስፋ መሠረት በእርሱ ከሞት የምነነሣ መሆናችንን በመጠባበቅ በሰው እጅ መሞት የተሻለ ነው፤ አንተ ግን ከሞት በሕይወት አትነሣም”። 15ቀጥሎ አምስተኛውን አመጡና አሠቃዩት፤ 16እርሱ ግን ንጉሡን ትኩር ብሎ እያየ እንዲህ አለ፥ “አንተ ምንም ሟች፥ በስባሽ ብትሆን ሥልጣን አለህ፤ የፈለግኸውንም ማድረግ ትችላለህ፤ ግን ዘራችን በእግዚአብሔር የሚጣል አይምሰልህ። 17አንተ ግን ጠብቅ፥ ታላቅ ሥልጣኑን ታያለህ፤ አንተን ከነዘርህ ያሠቃይሀል”። 18ከእርሱ በኋላ ስድስተኛውን አመጡ፤ እርሱም ሊሞት ሲል እንዲህ አለ፥ “በከንቱ አትሳሳት፤ በአምላካችን ላይ ኃጢአት ስለሠራን እኛ ስለእራሳችን ነው የምንሠቃየው፤ ይህ መጥፎ ዕድል የወደቀብን ስለዚህ ነው፤ 19ከእግዚአብሔር ጋር የምትዋጋ አንተ ግን ቅጣትንህን ሳትቀበል የምትቀር አይምስልህ”። 20እጅግ የምታስደንቅና ትውስታዋ የማይጠፋው እናትየዋ ናት፤ እርሷ ሰባቱም ልጆችዋ በአንድ ቀን ሲሞቱ እያየች ጸጥ ብላ ታገሰች፤ ምክንያቱም ተስፋዋን በእግዚአብሔር ላይ ጥላ ስለ ነበር ነው። 21ልጆችዋን በአባቶችዋ ቋንቋ ትመክራቸው ነበር፤ በታላቅ እምነትም የሴትነት ክርክሯን በተባዕት ድፍረት በማጽናት እንዲህ አለቻቸው፥ 22“ማሕፀኔ እንዴት እንደተፈጠራችሁ አላውቅም፤ እስትንፋስና ሕይወት የሰጠኋችሁ እኔ አይደለሁም፤ የእያንዳንዳችሁን አካል የሠራሁት እኔ አይደለሁም። 23ሰውን ገና ሲወለድ የፈጠረና ከሁሉ ነገር በፊት የነበረ የዓለም ፈጣሪ በምሕረቱ መንፈስንና ሕይወትን ይሰጣችኋል፤ ምክንያቱም ስለ ሕጎቹ ስትሉ ለሕይወታችሁ አልሳሳችሁምና”። 24አንጥዮኩስ የተናቀ መሆኑን አሰበና እነዚህ ቃሎች የውርደት ሳይሆን አይቀሩም በማለት ተጠራጠረ። የሁሉም ታናሽ ቀርቶ ነበር፤ እርሱን በምክር ተናረገው፤ እንዲሁም የአባቶቹን ባህል የተወ እንደሆነ ባለጠጋና ደስተኛ እንደሚያደርገው በመሐላ አረጋገጠለት፤ ወዳጁ እንደሚያደርገውና ከፍ ያለ ሹመት እንደሚሰጠው ነገረው፤ 25ወጣቱ ልጅ ነገሩን ስላልተቀበለው ንጉሡ እናቱን ጠራና ልጅሽ ሕይወቱን እንዲያድን ምክሪው አላት፤ 26ንጉሡ ብዙ ከመከራት በኋላ እሺ ልጁን ላሳምነው እሞክራለሁ አለች፤ 27ስለዚህ ወደ ልጇ ጐንበስ አለችና በንጉሡ እያላገጠች በአባቶዋ ቋንቋ እንዲህ ስትል ተናገረች፤ “ልጄ ሆይ ዘጠኝ ወር በማሕፀኔ ለተሸከምሁህ ራራልኝ፤ ሦስት ዓመት አጠባሁህ፤ አሁን እስካለህበት ዕድሜ ድረስ እየመገብሁ አሳደግሁህ፤ ምንም ሳይጐድልህ ለዚህ አደረስኩህ። 28የእኔ ልጅ አደራ እያልሁ እለምንሃለሁ፤ ሰማይና ምድርን ተመልከት፤ በእነርሱ ውስጥ ያለውን ነገር ሁሉ ተመልከት፤ እግዚአብሔር ህልው ካልሆነ ነገር የፈጠራቸው መሆኑን ዕወቅ፤ የሰው ዘርም የተፈጠረው እንዲሁ ነው። 29ልጄ ሆይ ይህን ነፍሰ ገዳይ አትፍራ፤ በምሕረት ቀን ከወንድሞችህ ጋር እንዳገኝህ እንደወንድሞችህ በክብር ሙት”። 30እርሷ ንግግሯን እንደጨረሰች ወዲያውኑ ወጣቱ እንዲህ አለ፥ “ምን ትጠብቃላችሁ? የንጉሡን ትእዛዝ አልቀበልም፤ በሙሴ ለአባቶቻችን የተሰጠውን አከብራለሁ፤ 31አንተ በዕብራውያን ላይ ይህን መከራ ያመጣህ ከእግዚአብሔር እጅ አታመልጠም፤ 32ምክንያቱም እኛ የምንሠቃየው በኃጢአታችን ምክንያት ነው። 33አዎ እኛን ለመቅጣትና ለመገሠጽ ሕያው የሆነው አምላካችን በእኛ ላይ ተቆጣ፤ ከአገልጋዮቹ ጋር እንደገና ይታወቃል። 34አንተ ግን ከሰው ሁሉ ይብስ የከፋህ ኃጢአተኛ በከንቱ ራስህን ከፍ ከፍ አታድርግ፤ በእግዚአብሔር አገልጋዮች ላይ እጅህን በማንሣት በከንቱ አትታበይ፤ 35ምክንያቱም አንተ ሁሉን ከሚችልና ሁሉን ከሚያይ አምላክ ፍርድ ገና አላመለጥህም። 36አሁን ለሚያልፈው ሕይወት ሲሉ የሚያልፈውን ሥቃይ የተቀበሉ ወንድሞቻችን ለእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ሲሉ ወደቁ (ሞቱ)፤ አንተ ግን በእግዚአብሔር ፍርድ ስለ ትዕቢትህ የተነገባውን ቅጣት ታገኛለህ። 37እኔም እንደ ወንድሞቼ ስለ አባቶቼ ሕግ ሥጋዬንና ሕይወቴን አሳልፌ እሰጣለሁ፤ እግዚአብሔር ለሕዝባችን ቶሎ እንዲራራና አንተንም በፈተናና በመቅሠፍት እርሱ ብቻ አምላክ መሆኑን ለማወቅ እንዲያስችልህ እለምነዋለሁ፤ 38ሁሉን የሚችል አምላክ በቅን ፍርዱ በዘራችን ላይ ያወረደው መዓት በእኔና በወንድሞቼ እንዲቆም እለምነዋለሁ”። 39ይህ ወጣት ስላላገጠበት ከሌሎቹ ይበልጥ የንጉሡ መዓት ወረደበት። 40ወጣቱ ሳያድፍ ተስፋውን በእግዚአብሔር ላይ ጥሎ ሞተ። 41በመጨረሻም ከልጆችዋ በኋላ እናትዬዋ ሞተች። 42ስለ አምልኮ መብልና ስለ አስፈሪው ሥቃይ የምንለውን በዚሁ እናበቃለን።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in