YouVersion Logo
Search Icon

1ኛ መጽሐፈ መቃብያን 9

9
የይሁዳ መቃቢስ መሞትና የቤርሶይት ጦርነት
1ደሜጥሮስ የኒቃኖርን ከነሠራዊቱ በጦርነት ላይ መውደቅ በሰማ ጊዜ እንደገና ባቂደስንና አልቅሞስን ከሠራዊቱ የቀኝ ክንፍ ሠራዊት ጋር ወደ ይሁዳ አገር ላከ። 2እነርሱ ወደ ገሊላ በሚወስደው መንገድ አልፈው በአርበሊስ ምድር የምትገኘዋን መላሎትን ከበቡና ያዟት፤ እዚያ ብዙ ሰዎችን ገደሉ። 3በመጀመሪያው ወር በመቶ ሐምሳ ሁለት ዓመተ ዓለም በኢየሩሳሌም ፊት ለፊት ሠፈሩ፤ 4ከዚያ ተነሥተው ከሃያ ሺህ እግረኛና ከሁለት ሺህ ፈረሰኛ ሠራዊት ጋር ወደ ቤርሳይት ሄዱ። 5ይሁዳ ግን ምርጥ የሆኑ ሦስት ሺህ ተዋጊዎች ይዞ ሰፈሩን በኤልአሳ አደረገ። 6የጠላት ወታደሮች ተደናግጠው ብዙዎቹ ከዱ፤ ከስምንት መቶ ሰዎች በቀር ሌላ የተገኘ የለም። 7ውጊያው ልክ ሊጀመር በታቀደበት ሰዓት ይሁዳ የእርሱ ሠራዊት የጐደለበት መሆኑን አየ፤ ወታደሮቹን ለማሰባሰብ ጊዜ በማጣቱ ልቡ በኀዘን ተሰበረ። 8ተስፋ ቆርጦ የቀሩትን ወታደሮች፥ “እንነሣ፤ ምናለበት ልንወጋቸው እንችል እንደሆነ እንውጣና እንግጠማቸው” አለ። 9እነርሱ አይሆነም አሉት፤ “አሁን ለጊዜው እኛ ሕይወታችንን ከማዳን በቀር ምንም ማድረግ አንችልም፤ ከወንድሞቻችን ጋር ሆነን ተመልሰን እንዋጋለን፤ አሁን እኛ በጣም ጥቂቶች ነን” አሉት። 10ይሁዳም፥ “እኔ ሽሽትን መርጧል አልባልም፤ ሰዓታችን ደርሶ ከሆነ ስለ ወንድሞቻችን በጀግንነት እንሙት፤ ክብራችንን አናስነውር” ሲል መለሰላቸው።
11የጠላት ጦር ሠራዊት ከሰፈሩ ወጥቶ ውጊያ ሊገጥማቸው መጣ፤ ፈረሰኛ ጦር በሁለት ክፍል ተከፍሎ ነበር፤ ከጦር ሠራዊቱ ፊት ቀድመው ወንጫፊዎችና ቀስተኞች እንዲሁም የፈጥኖ ደራሽ ጀግኖች ሁሉ ይሄዱ ነበር። 12ባቂዳስ በቀኝ ክንፍ በኩል ነበር፤ መለከት እየተነፋ ሠራዊቱ በሁለት ጐን ወደ ፊት ይሄድ ነበር። የይሁዳ ሰዎችም እንዲሁ መለከት ነፉ። 13ከሠራዊቱ ድምፅ የተነሣ ምድር ተንቀጠቀጠች ውጊያውም ከጠዋት ጀምሮ እስከ ማታ ቀጠለ። 14በቂደስና ኃይለኛው ጦር በቀኝ በኩል መሆኑን ይሁዳ አየ፤ በድፍረት የተሞሉትን ሁሉ በይሁዳ ዙሪያ አሰባሰቡ፤ 15በቀኝ ክንፍ በኩል ያሉትን ገለባበጡና እስከ አዞጦን (አዘሬ) ኮረብታ ድረስ አባረሩዋቸው፤ 16የቀኝ ክንፍ ሰዎች መሸነፋቸውን ባዩ ጊዜ የግራ ክንፍ ሰዎች ወደ ይሁዳና ወደ እርሱ ሰዎች ተመልሰው ተከተሉት። 17የከረረ ውጊያ ተደረገ፤ ከዚህም ከዚያም ብዙ ሰዎች አለቁ። 18ይሁዳም ወደቀ፤ ሌሎቹ ሸሹ።
የይሁዳ መቃቢስ የቀብር ሥነ ሥርዓት
19ዮናታንና ስምዖን ወንድማቸውን ይሁዳን አንሥተው በሞዲን በአባቶቹ መቃብር ቀበሩት። 20መላው የእስራኤል ሕዝብ አለቀሱለት፤ ትልቅ ኀዘንም አደረጉለት፤ 21“እስራኤልን ያድን የነበረው ጀግና እንዴት ወደቀ?” እያሉ ብዙ ቀኖች አለቀሱ። 22ሌሎቹ የይሁዳ ሥራዎች፥ የዋለባቸው ጦር ሜዳዎች፤ የሰበሰባቸው ምርኮዎች፤ በየወቅቱ ያገኛቸው ከፍተኛ ማዕረጎች አልተመዘገቡም። ነገር ግን እጅግ በርካታ እንደ ነበሩ የተሰወረ አልነበረም።
የአይሁድ መሪና የካህናት አለቃ ዮናታን
የግሪኩ ቡድን ድል፤
ዮናታን ተቃውሞውን መራ
23ከይሁዳ ሞት በኋላ አመፀኞቹ ከሐዲዎቹ እንደገና በእሥራኤል ምድር ሁሉ ብቅ ብቅ አሉ፤ 24በዚያን ጊዜ ትልቅ ረሃብ ስለ ነበር አገሩ ከእርሱ ጋር ተስማማ፤ 25ባቂደስ ሆን ብሎ ከዓመፀኞቹ መካከል አገሩን የሚያስተዳድሩ ሰዎች መረጠ፤ 26የይሁዳን ወዳጆች እያደኑ ይዘው ወደ ባቂደስ ይወስዷቸው ነበር፤ ያላግጡባቸው ነበር፥ 27የነቢያት መጨረሻ ጊዜ ከነበረበት ቀን አንሥቶ እንዲህ ያለ ጭቆና በእስራኤል ላይ ተደርጐ አይታወቅም ነበር። 28በዚያን ጊዜ የይሁዳ ወዳጆች ተሰበሰቡና ዮናታንን እንዲህ አሉት፤ 29“ወንድምህ ይሁዳ ከሞተ ጀምሮ እንደ እርሱ ያለ በጠላቶቻችን ላይ በባቂደስና የሕዝባችን ጠላቶች በሆኑት ሰዎች ላይ የሚነሣ ሰው አልተገኘም። 30ስለዚህ ውጊያችንን እንድናደርግ አንተን ዛሬ በእርሱ ቦታ አለቃችንና መሪያችን አድርገን መርጠንሃል” 31ዮናታን ወዲያውኑ መሪነትን ተቀብሎ በወንድሙ በይሁዳ ቦታ ተተካ።
ዮናታን በተቆዓ በረሃ ውስጥ በሜዴባ ዙሪያ ያካሄደው ደም አፍሳሽ ፍልሚያ
32ባቂደስ ይህን በሰማ ጊዜ ዮናታንን ሊገድለው ፈለገ። 33ለዮናታንና ለወንድሙ ለስምዖን እንዲሁም ዮናታንን ለተከተሉት ሰዎች ሁሉ ይህን ዜና ስለደረሳቸው፤ ወደ ተቆዳ ሸሽተው ሄዱ፤ በአጽፋር በሚባለው የበረሃ ገነትም አጠገብ ሠፈሩ። 34ባቂደስ በሰንበት ቀን ይህን ነገር ሰማና ከሠራዊቱ ሁሉ ጋር ሆኖ ወደ ዮርዳኖስ ማዶ ተሻገረ። 35ዮናታን ጓዙ ብዙ ስለ ነበረ ወዳጆቹ ናቦታውያን ጓዙን በእነርሱ ዘንድ ለማስቀመጥ እንዲፈቅዱለት ለመጠየቅ የወታደሮች አዛዥ የነበረውን ወንድሙን ወደ እነርሱ ላከው። 36ግን ከሜዳባ ወገን የሆኑ አምራይ ልጆች መንገድ ላይ ጠብቀው ዮሐንስና ያለውንም ነገር ሁሉ ዘርፈው ምርኮአቸውን ይዘው ሄዱ። 37ይህ ነገር ከተደረገ በኋላ የአምራይ ልጆች ትልቅ የጋብቻ በዓል የሚያደርጉ መሆናቸውን ለዮናታንና ለወንድሙ ለስምዖን ተነገራቸው፤ ሙሽራይቱን ከናዳባት (ከናባታ) በታላቅ ክብር ያመጡ ነበር። እርሷ የአንድ በከነዓን አገር የተከበረ ሰው ልጅ ነበረች። 38እነርሱም የወንድማቸውን የዮሐንስን መገደል አስታወሱ፥ ከተራራ ላይ ወጥተው ከተራራው ጥግ በስተ ኋላ ተደበቁ። 39ቀና ብለው በጫጫታ መካከል ብዙ ሰዎች ሲመጡ አዩ፤ ሙሽራው፤ ሚዜዎቹና ወንድሞቹ ብዙ ጓዝ ይዘው ከአጀቡ ፊት ፊት እየሄዱ፥ ከበሮ እየመቱ፥ እየዘፈኑ በጦርነት ጊዜ እንደሚሆነው የደመቀ ትርኢት እያሳዩ ሲመጡ ተመለለከቱ። 40ከተደበቁበትም ዘለው በውጣት ጨፈጨፍዋቸው፤ ብዙዎቹ ቆስለው ወደቁ፤ የተረፉትም ወደ ተራራው ሸሹ፤ እነዮናታን የሰዎቹን ዕቃዎች ሁሉ ይዘው ሄዱ። 41በእዚህ ዓይነት ሰርጉ ወደ ኀዘን ተለወጠ፤ ሙዚቃውም ወደ ዋይታ ተለወጠ፤ 42የወንድማቸውንም ደም እንደዚህ ተበቀሉና ወደ ዮርዳኖስ ረግረግ ስፍራዎች ተመልሰው ሄዱ።
ዮርዳኖስን ማቋረጥ
43ባቂደስ ይህ ነገር ተነገረውና ከብዙ ሠራዊት ጋር እስከ ዮርዳኖስ ወንዝ አጠገብ ድረስ በሰንበት ቀን ሄደ። 44በዚያን ጊዜ ዮናታን የእርሱን ሰዎች እንዲህ አላቸው፥ “እንነሣ፤ ሕይወታችንን ለማዳን እንዋጋ፤ ምክንያቱም ዛሬ እንደ ትላንትና እንደ ትላንት በስቲያ አይደለም። 45እንደምትመለከቱት ከፊትም ከኋላም መዋጋት አለብን በአንድ በኩል በዮርዳኖስ ውሃ በሌላ በኩል ማጥና ጫካው ስለሚጠብቀን ምንም ማምለጫ ቀዳዳ አይኖረንም። 46አሁን እንግዲህ ከጠላቶቻችሁ እጅ ለማምለጥ ወደ ሰማይ ጩሁ”። 47ዮናታን ፍልሚያውን ጀመረ፤ ዮናታን ባቂደስን ለመምታት እጁን ሠነዘረ፤ ሶሪያዊው ግን ራሱን አላቆ ተፈተለከ፤ 48ዮናታንና ጓደኞቹ በዮርዳኖስ ውስጥ ዘልለው ገቡና እየዋኙ ወዲያ ማዶ ተሻገሩ፤ ጠላት ግን ተከትለዋቸው ለመሻገር አልቻሉም። 49በዚያ ቀን በቂደስ ሺህ ተከታዮቹን አጣ።
ባቂደስ ምሽጎችን ገነባ አልቂይሞስ ሞት
50ባቂደስ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሰ። በይሁዳ ምድር ከተሞች ሠራ፤ በኢያሪኮ፥ በኤማሁስ፥ በቤቶሮን፥ በቤቴል፥ በተሞናታ፥ በፋራቶን፥ በጫፎን ምሽግ ሠራ፤ ከፍተኛ ግንቦችንና መዝጊያዎችን፥ መሸጐሪያዎችንም አደረገ። 51እስራኤላውያን ለማስጨነቅ በእያንዳንዱ ምሽግ ወታደሮችን አቆመ። 52የቤተሱራን፥ የጊዜርን፥ የኢየሩሳሌምን ምሽግ አጠናከረ። በእዚያ ወታደሮችና የስንቅ መጋዘንን አደረገ። 53የአገሩን ታላላቅ ሰዎች ልጆቻውን በመያዣነት ያዘባቸውና በኢየሩሳሌም ምሽግ ውስጥ አሠራቸው። 54በመቶ ሐምሳ ሦስት ዓመተ ዓለም፤ በሁለተኛው ወር አልቂሞስ የቤተ መቅደሱን የውስጥ ግንብ እንዲያፈርስ አዘዘ፤ ዕቅዱም የነቢያትን ሥራ ለማፍረስ ነበር። የማፍረሱንም ሥራ አስጀመረ። 55በዚያን ጊዜ አልቂሞስ መቅሠፍት አገኘው፥ ሥራውም ተቋረጠ፤ አንደበቱ ተያዘ፤ ሽባ ሆነ፤ ከዚያ ወዲያ አንዲት ቃል እንኳን መናገርና ስለ ቤቱ አንድ ነገር እንኳ ማዘዝ አቃተው። 56አልቂሞስ ብዙም ሳይቆይ በከፍነተኛ ስቃይ ሞተ። 57ባቂደስ የአልቂሞስን ሞት ባየ ጊዜ ወደ ንጉሡ ተመለሰ፤ በይሁዳ አገርም ሁለት ዓመት ሰላም ሆነ።
የቤትባሲ መከበብ
58ከሐዲዎች እንዲህ ሲሉ ተማከሩ፥ “እነሆ ዮናታንና የእርሱ ተከታዮች በሰላምና ያለ ፍርሃት ይኖራሉ፤ ስለዚህ ሄደን ባቂደስን እናመጣዋለን፤ እርሱ ሁሉንም ባንድ ሌሊት ይዞ ያስራቸዋል።” 59ሄደውም ከእርሱ ጋር ተማከሩ። 60ባቂደስ ብዙ ወታደሮች ይዞ ከእነርሱ ጋር ሄደ፤ ዮናታንንና ጓደኞቹን እንዲይዙ በይሁዳ አገር ለሚገኙ የጦር ጓደኞቹ ሁሌ በሥውር ይጽፍላቸው ነበር። ግን ሐሳባቸው ከሸፈባቸውና ያሰቡት አልሆነላቸውም። 61እንዲያውም ይህን ክፉ ምክር የመከሩ ሐምሳ የሚሆኑ የሀገሩ ሰዎች ተይዘው ተገደሉ። 62ከዚህ በኋላ ዮናታንና ስምዖን ተከታዮቻቸውም ወደ በረሃ፥ ወደ ቤትባሲ ሄዱ። እዚያ የፈራረሱትን እንደገና ሠሩ ከተማዋንም አጠናከሩ። 63ባቂደስ ይህን ሰምቶ ወታደሮቹን ሁሉ ሰበሰበ፤ በይሁዳ ምድር ላሉት ተከታዮችም አስታወቃቸው። 64በቤትባሲ ፊት ለፊት ቦታ ያዘና ከብቦ ለብዙ ቀናት ቤትባሲን ወጋት፤ የውጊያ ተሽከርካሪዎችንም አሠራ። 65ዮናታን ወንድሙን ስምዖንን በከተማ ትቶ ከቂት ሰዎች ጋር ሆኖ ወደ ገጠር ወጣ። 66ኦዶሜራንና ወንድሞቹን እንዲሁም የፋሴሮንን ልጆች በሠፈራቸው እንዳሉ ወጋቸው፤ እነሱም ከእርሱ ኃይል ጋር ተደባለቁ። 67ስምዖንና ሰዎቹ ወጡና ተሽከርካሪዎቹን አቃጠሉ። 68ባቂደስን ወጉት እርሱ ተሸንፎ ሐሳቡ ስላልተሳከላት በታላቅ ጭንቀት ላይ ወደቀ። 69ንዴቱንም ወደ ይሁዳ እንዲገባና በይሁዳ ወረዳ ላይ እንዲፈጽም ያነሣሡትን ከሐዲዎችን ሁሉ ሰብስቦ በመግደል እልሁን ተወጣ። ወዲየውኑ ወታደሮቹን ያዘ ወደ ሀገሩ ተመለሰ። 70ይህን በሰማ ጊዜ ዮናታን ሰላም ለማድረግና እስረኞችን ለመለዋወጥ ወደ እርሱ መልእክተኞችን ላከ፤ 71እርሱም ነገሩን ተቀብሎ ዮናታን በጠየቀው መሠረት አደረገ፤ ከእንግዲህ ወዲህ በመላ ሕይወቱ በእርሱ ላይ ክፉ ማድረግ እንደሚይፈልግም ማለለት። 72በይሁዳ አገር የማረካቸውንም ሰዎች መለሰለት፤ ከዚህ በኋላ ወደ ሀገሩ ተመለሶ ሄደ፤ ዳግመኛ ወደ ድንበሮቻቸው አልተመለሰም፤ 73በእስራኤል ላይ ሰይፍ ማንዣበብ አቆመ፥ በማቅማስ ዮናታን ተቀመጠ፤ እዚያ ሕዝቡን መደኘት ጀመረ፤ ዓመፀኞችንም ከእስራኤል አጠፋ።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in