YouVersion Logo
Search Icon

1ኛ መጽሐፈ መቃብያን 8

8
የሮማውያን የምስጋና ቃል
1የሮማውያን ዝና ወደ ይሁዳ ጆሮ ደረሰ፤ እነርሱ ጐበዝ ጦረኞች ነበሩ፤ ከጐናቸው ለማሰለፉ ሰዎች ሁሉ ደጐች ነበሩ፤ ወደ እነርሱ ለሚመጡ ሰዎች ሁሉ ወዳጅነታቸውን የሚሰጡ (የሚለግሡ) ነበሩ፤ ጀግና ጦረኞች ነበሩ። 2ያደረጓቸውን ዘመቻዎች፥ በገላትያ አገር የፈጸሟቸውን ብዝበዛዎች፥ የገላትያን ሰዎች ማሸነፋቸውንና እንዲገብሩ ማድረጋቸውን ለይሁዳ አወሩለት፤ 3እዚያ የሚገኙትን የብርና የወርቅ ማዕድኖችን ለመውሰድ በእስጳንያ አገር ያደረጉትን እና 4በብልኀነታቸውና በጥንካሬአቸው ይህን አገር እንዴት አድርገው እንደያዙት አወሩለት፤ በእውነቱ ቦታው ከእነርሱ በጣም ሩቅ ነበር፤ እነርሱን ለመውጋት ከምድር ዳርቻ የመጡ ነገሥታትም ነበሩ፤ ብዙ ጉዳት አድርሰውባቸው አጥፋተዋቸዋል፤ ሌሎቹ ግን የዓመት ግብር ይከፍሏቸው ነበር፤ 5በመጨረሻም የኪቲማውያንን ንጉሥ ፊሊጶስን ጴርሰስንም በእነርሱ ላይ የተነሡባቸውን ሁሉ ወግተው አሸንፈዋቸዋል። 6መቶ ሃያ ዝሆኖች፥ ፈረሰኛው ጦረኞችና የሠረገላ ጦረኞች እንዲሁም ብዙ ሠራዊት አስከትቶ ሊወጋቸው የመጣባቸውን የእስያ ንጉሥ የነበረውን አንጥዮኩስን አሸንፈውታል፤ 7ንጉሡም በሕይወቱ ተይዞ እርሱም ወራሾቹም ከእርሱ በኋላ በተወሰነው ጊዜ ከባድ ግብር እንዲከፍሉ ተደርጐባቸዋል፤ ዋስም እንዲቀርብ ተደርጓል፤ 8የሕንድ፥ የምድያም፥ የልድያ አገሮች እንዲሁም አንዳንድ ምርጥ አገሮች ተወስደውበት ለንጉሥ ዩሚነስ ተሰጥተውበታል። 9የግሪክ ሰዎች ሄደው ሊፈጁዋቸው ፈልገው ነበር፤ 10ሮማውን ነገሩን ባወቁ ጊዜ አንድ የጦር መሪ ብቻ ልከው ጦርነት ገጠሟቸው፤ ከግሪካውያን ብዙዎች ሞቱ፤ ሚስቶቻቸውና ልጆቻቸው በውርስ ተወሰዱ፤ ሮማውያን ንብረታቸውን ዘርፈው ወሰዱባቸው፤ አገራቸውን አስገበሩ፤ ምሽጐቻቸውን አፈረሱ፤ እስከ ዛሬ ድረስ እንዲያገለግሏቸው አድርገዋቸዋል። 11እንዲሁም የተቃወሟቸውን መንግሥታትና ደሴቶች ደምስሰው አስገብረዋቸዋል። 12ነገር ግን ወዳጆቻቸውንና በእነርሱ የሚተማመኑትን በተመለከተ ግን የገቡትን ቃል አያጥፉም። ሩቆችንም ሆነ ቅርቦችን ነገሥታት ይዘው አረብረዋል፤ ስማቸውን የሚሰሙ ሁሉ ይፈሩዋቸዋል። 13መንገሥና እርዳታም ማግኘት ይገባቸዋል የሚሏቸውን ያነግሣሉ፥ ሌሎችን ግን ይሽራሉ፤ በጣም ከፍ ያለ ኃይል ያላቸው ናቸው። 14ታዲያ ይህ ሁሉ ሲሆን አንድ እንኳ ከእነርሱ ዘውድ የደፋና ለመመካት ከፈይ የለበሰ የለም። 15መልካም ሥርዓት እንዲጠበቅ የሕዝብን ጉዳዮች ሁልጊዜ የሚመረምሩ ሦስት መቶ ሃያ አባሎች ያሉበት ከፍተኛ ምክር ቤት አላቸው፤ 16የሚያስተዳድራቸውና በበላይነት መንግሥታቸውን በሙሉ የሚጠብቅ አንድ ሰው በየዓመቱ ይሾማሉ፤ ምንም ሳይመቀኙበትና ሳይቀኑበት ሁሉም ለእርሱ ብቻ ይታዘዛሉ።
አይሁዳውያን ከሮማውያን ጋር የገቡት (ቃል ኪዳን)
17ይሁዳ የዮሐንስን ልጅ፤ የአኮስን የልጅ ልጅ አውጶለሞንና የኤልዓዛርን ልጅ ኢያሶንን ስለ ፍቅርና ስለውል እንዲነጋገሩ ወደ ሮም ላካቸው፤ 18የግሪካውያን መንግሥት እስራኤልን ወደ ባርነት እንደሚጥል በማየት ቀንበራቸውን ለማንሣት ብሎ ነው የላካቸው። 19መልእክተኞቹ ወደ ሮም ሄዱ፥ መንገድ በጣም ረጅም ነበር፤ ወደ ታላቁ ምክር ግንብ ገቡና እንዲህ ሲሉ ተናገሩ፥ 20“ይሁዳ መቃቢስና ወንድሞቹ እንዲሁም የአይሁድ ሕዝብም ከእናንተ ጋር ቃል ኪዳንና ሰላም ለማድረግ ከቃል ኪዳን ጓደኞቻችሁና ከወዳጆቻችሁ ጋር የትብብርና የሰላም ስምምነት እንድንዋዋል እና የእናንተም ወዳጆች እንድንሆን ፈልገው ወደ እናንተ ልከውናል”። 21የምክር ቤቱ አባላት በነገሩ ደስ ተሰኙ። 22እነሆ በናስ ሠሌዳ ላይ በመቅረጽ ጽፈው የሰላምና የቃል ኪዳን መታሰቢያ እንዲሆን ወደ ኢየሩሳሌም የላኩት የጽሑፍ ግልባጭ እንዲህ ይላል፥ 23“ለሮማውያን ለአይሁዳውያንም ሕዝብ ለዘለዓለም በባሕርና በምድር ብልጽግና ይሁን፥ ሰይፍና ጠላት ከእርሱ ይራቅ፤ 24ነገር ግን በመጀመሪያ በሮም ወይም የበላይ ጠባቂነትዋ በሚገኝበት በማንኛውም ቦታ ከሚገኙት ከጦር ጓደኞችዋ በአንድ ላይ የሚያስጋ ነገር ቢገኝ 25የአይሁድ ሕዝብ ከሮም ጋር ሆኖ በሙሉ ልብ ይዋጋል፤ የሚዋጋውም የጊዜው ሁኔታ በሚያስገድደው መሠረት ነው። 26ከሮም ጋር ጦርነት ለሚገጥሙ ጠላቶች ሮም እንደወሰነችው ስንዴ ወይም የጦር መሣሪያ ወይም ገንዘብ ወይም መርከቦች አይሰጡም፤ ወይም አያበድሩም። በመልሱ ምንም ሳይቀበሉ ግዳጃቸውን ይፈጽማሉ። 27እንዲሁም አስቀድሞ የአይሁድን ሕዝብ የሚነካ ጦርነት ቢነሣ የጊዜው ሁኔታ በሚያስገድደው መሠረት ሮማውያን ከሕዝቡ ጋር ሆነው በሙሉ ልብ ይዋጋሉ። 28ሮም እንደወሰነችው ለእስራኤል ጠላቶች ስንዴ ወይም የጦር መሣሪያ ወይም ገንዘብ ወይም መርከቦች አይቀርቡም፤ ሮማውያን ግን በታማኝንት ግዳጃቸውን ይወጣሉ። 29ከአይሁድ ሕዝብም ጋር ያደረጉት ቃል ኪዳን ይህን ይመስል ነበር። 30በመጪው ጊዜ እነዚህ ወይም እነዚያ አንዳንድ ነገር መጨመር ወይም መቀነስ ቢፈልጉ እንደ ፈለጉት ያደርጋሉ፤ የተጨመረው ወይም የተቀነሰው ነገር በሙሉ ተቀባይነት ይኖረዋል።” 31ንጉሥ ዲሜጥሮስ በእነርሱ ላይ ስለመፈጸመው በደል እንዲህ ብለን ጽፈንለታል፥ “ወዳጆቻችንና የጦር ጓደኞቻችን በሆኑት አይሁዳውያን ላይ ሰለምን ቀንበርህን አከበድህባቸው? 32እንደገና እነርሱ የከሰሱህ እንደሆነ እኛ እነርሱን እናግዛለን፤ አንተን በባሕርም ሆነ በምድር እንወጋሃለን።”

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in