YouVersion Logo
Search Icon

1ኛ መጽሐፈ መቃብያን 7

7
የቀዳማዊ ዲሜጥሮስ መንገሥ፥ የባቂደስና የአልቂሞስ ወደ
ይሁዳ መላክ
1በመቶ ሐምሳ አንድ ዓመት ገደማ የሰለውቂስ ልጅ ዲሜጥሮስ ከሮም አምልጦ ከጥቂት ሰዎች ጋር ባሕር አጠገብ ወደምትገኝ ወደ አንዲት ከተማ ሄደ፤ እዚያ ነገሠ። 2ወደ አባቶቹ ቤተ መንግሥት በገባ ጊዜ ሠራዊቱ አንጥዮኩስንና ሊስያስን ወደ እርሱ ለማምጣት ያዙዋቸው፤ 3ይዘናቸዋል ብለው ቢነግሩትም፥ “ፊታቸውን አታሳዩኝ” አላቸው። 4ሠራዊቱም ገደላቸው። ዲሜጥሮስም በንጉሣዊ ዙፋኑ ላይ ተቀመጠ። 5በዚያን ጊዜ ከእስራኤል ሕዝብ ውስጥ ሃይማኖትና ሕግ ያልነበራቸው ሰዎች ሁሉ የሊቀ ካህንነት ሹመት ይመኝ በነበረው በአልቂሞስ ተመርተው ወደ እርሱ መጡ። 6በንጉሡ ፊት ሕዝቡን እንዲህ ሲሉ አወገዙ፥ “ይሁዳና ወንድሞቹ ወዳጆችህን ሁሉ አጠፉ፤ እኛንም ከሀገራችን ውጭ እንድንበታተን አደረጉን፤ 7ስለዚህ አሁን በኛ መካከልና በንጉሡ ግዛት ውስጥ ይሁዳ የጠፋቸውን ጥፋቶች ሂዶ እንዲያይ አንድ የታመነ ሰው ላክ፤ እነርሱና ረዳቶቻቸውም ሁሉ ይቀጡ”። 8ንጉሡም ታላቅና ታማኝ የነበረውን የአፍራጦስ ማዶ ገዢና ከንጉሡ ወዳጆች አንዱ የነበረውን ባቂደስን መረጠ። 9ከኀጢአተኛው ከአልቂሞስ ጋር ላከው፤ ለአልቂማስ የክህነት ሥልጣን ሰጠውና የእስራኤልን ልጆች እንዲቀበል ሾመው። 10ከብዙ ሠራዊት ጋር አብረው ሄዱና ወደ ይሁዳ ምድር ደረሱ፤ ለይሁዳና ለወንድሞቹ የውሸት የሰላም ቃል የያዘ መልእክት ላኩ። 11አይሁዳውያኑ እነርሱ የባዕድ ሠራዊት ይዘው መምጣታቸውን ባዩ ጊዜ ንግግራቸውን አላመኑም። 12የሙሴ ሕግ መምህራን ትክክለኛ መፍትሔ ለመፈለግ ተሰብስበው ወደ አልቄሚስና ወደ ባቂደስ ሄዱ። 13ከእስራኤላውያን መካከል የመጀመሪያዎቹ ሰላም ፈላጊዎች አሲዳውያን ነበሩ። 14እነርሱም፥ “ከወታደሮቹ ጋር አብሮ የመጣው ከአሮን ዘር የሆነው ካህን ነው፤ በእኛ ላይ ፍርድን አጓድሎ ክፉ ነገር አያደርግብንም” ይሉ ነበር። 15እርሱም የሰላም ንግግር አደረገላቸውና፥ “በናንተም ሆነ በወዳጆቻችሁ ላይ ምንም ክፉ ነገር አናደርግባችሁም” ሲል በመሐላ አረጋገጠላቸው። 16እነርሱም አመኑት፤ ነገር ግን በመጽሐፉ ላይ እንደተጠቀሰው ስድሳዎቹን አስይዞ ባንድ ቀን አስገደላቸው፤ 17ይህንም ያደረገው፥ “በኢየሩሳሌም ዙሪያ የቅዱሳንህን ሥጋ በትነዋል፥ ደማቸውንም አፍስሰዋል፤ የሚቀብራቸው ማንም አልነበረም” ተብሎ የተጻፈው ይፈጸም ዘንድ ነው። 18“ያደረጉትን ስምምነትና መሐላ ስላፈረሱ እነዚያ ሰዎች እውነተኝነትና ትክክለኝነት የለባቸውም” ተባሉ። ፍርሃትና ጭንቀትም በነሱ ላይ ነገሠ። 19ባቂደስ ከኢየሩሳሌም ሄዶ ሰፈሩን በቤተዜት አደረገ፤ እርሷን ትተው ከሄዱትም ሰዎች መካከል ብዙዎችን አሠረ፤ እንዲሁም ከሕዝቡ አንዳንዶቹን አስያዘ፤ እንዲገደሉም አደረገ በኋላ በታላቁ ጉርጓድ ውስጥ ጣላቸው። 20ክፍለ ሀገሩን አልቂሞስ መልሶ ሰጠው፤ የሚያግዘው ሠራዊትም ተወለት፤ ከዚህ በኋላ ባቂደስ ወደ ንጉሡ ተመልሶ ሄደ። 21አልቂሞስ ሊቀ ካህናት መሆኑን ለማሳመን ታገለ፤ 22በሕዝቡ መካከል ሁከት ይነዙ የነበሩ ሰዎች ሁሉ በዙሪያው ተሰበሰቡ፤ የይሁዳን ምድር ያዙ፤ በእስራኤል ላይ ትልቅ ጉዳት አመጡ። 23ይሁዳ በእስራኤል ልጆች ላይ ከአረመኔዎች የባሰ የሚያደርጉትን የአልቂሞስንና ወገኖቹን ክፋት ባየ ጊዜ 24በይሁዳ አገሮች ሁሉ በዙሪያቸው ተዘዋወረ፤ በከሐዲዎች ላይ ተበቀለ፤ በአገሩ ውስጥ እንዳይዘዋወሩ ከለከለ።
ኒቃኖረ በይሁዳ ምድር፥ የካፋር ሳልማ ጦርነት
25ይሁዳና ጓደኞቹ ይበል ብርቱዎች መሆናቸውን ባየ ጊዜና ሊቋቋማቸው አለመቻሉን በተገነዘበ ጊዜ አልቂሞስ ወደ ንጉሡ ተመልሶ ብዙ ክፋት ሠርተዋል ሲል ከሰሳቸው። 26የእስራኤልን ሕዝብ በጥላቻና በጠላትነት የሚመለከተውን ከክቡራት ክፍል ሆኖ ከጦር መሪዎቹ አንዱ የነበረውን ኒቃኖርን ሕዝቡን እንዲደመስስ በማዘዝ ንጉሡ ላከው። 27ኒቃኖር ወደ ኢየሩሳሌም ብዙ ሠራዊት ይዞ ሄደ፤ ለይሁዳና ለወንድሞቹ በውሸት የሰላም ቃል ተናገረ፤ 28“በእኔና በእናንተ መካከል ውጊያ አይሁን፤ የሰላም ንግግር ለማድረግ በጥቂት ሰዎች ታጅቤ እመጣለሁ” አለ። 29ወደ ይሁዳ ሄደ፤ በወዳጅነት ሰላምታ ተሰጣጡ፤ ነገር ግን ጠላቶች ይሁዳን ይዘው ለመውሰድ ተዘጋጅተው ነበር። 30ኒቃኖር ወደ እርሱ የመጣው በአታላይነት መንፈስ መሆኑን አውቆ ይሁዳ ፈራውና የሰላም ንግግሩን ለማድረግ አልፈቀደም። 31ኒቃኖር ተንኮሉ እንደታወቀበት ተገንዝቦ ከፋርሰላም ከይሁዳ ጋር ለመዋጋት ወጣ፤ 32በኒቃኖር በኩል አምስት መቶ ያህል ሰዎች ሞቱ፤ የቀሩት ወደ ዳዊት ከተማ ሸሽተው ሄዱ።
ቤተ መቅደሱ ላይ የተሰነዘረ ዛቻ
33ከእነዚህ ነገሮች በኋላ ኒቃኖር ወደ ጽዮን ተራራ ወጣ፤ ካህናት በሰላም እጅ ለመንሳትና ስለ ንጉሡ የሚቀርበውን የሚቃጠል መሥዋዕትን ለእርሱ ለማሳየት ከሕዝብ ሽማግሌዎች ጋር ሆነው ከቤተ መቅደስ ወጡ። 34እርሱ ግን በማላገጥ ሳቀባቸው፥ አዋረዳቸው፥ የትዕቢት ቃል ተናገራቸው። 35እንዲህ ሲል በቁጣ ማለ፥ “አሁን በዚህ ጊዜ ይሁዳ ከነሠራዊቱ በእጄ ካልገባ እኔ አንድ ጊዜ ሰላም አድርጌ ስመለስ በዚች ግንብ ላይ እሳት እለቅባታለሁ።” ይህን ብሎ በቁጣ ወጥቶ ሄደ። 36ካህናቱ ተመልሰው ገቡ፤ በመሠዊያውና በቤተ መቅደሱ ፊት ቆመው እንባቸውን እያፈሰሱ እንዲህ አሉ፥ 37አምላክ ሆይ የጸሎትና የልመና ቤት እንድትሆን፥ ስምህ በውስጧ እንዲጠራ ይህችን ግንብ የመረጥህ አንተ ነህ፤ 38በዚህ ሰው ላይና በሠራዊቱም ላይ አንተ ተበቀል፤ በሰይፍ ተመትተው ይውደቁ፤ ስድባቸውን አስታውስ፤ ጊዜም አትስጣቸው።
የኒቃኖር ቀን በአዳሳ
39ኒቃኖር ከኢየሩሳሌም ወጣና ሰፈሩን በቤቶሮን አደረገ፤ እዚያ የሶሪያ ጦር ሠራዊት ሊተባበረው መጣለት፤ 40ይሁዳ ከሦስት ሺህ ሰዎች ጋር ሆኖ ሰፈሩን በአሰሳ በማድረግ በዚያን ጊዜ እንዲህ ሲል ጸለየ፥ 41“የንጉሡ መልእክተኞች በተሳደቡ ጊዜ መልአክህ መጥቶ ከእነርሱ መካከል መቶ ሰማንያ አምስት ሺህ ሰዎችን መታ፤ 42ዛሬም እንዲሁ እኛ ፊት ይህን የጦር ሠራዊት ቀጥቅጥ፤ እርሱ ቤተ መቅደስህን መስደቡን ሌሎችም ይወቁ፤ እንደ ክፋቱ ፍረድበት።” 43ሠራዊቶቹ በዓሥራ ሦስት አዳር (28 መጋቢት) ውጊያውን ጀመሩ፤ የኑቃኖር ሠራዊት ተመታ፤ እርሱም ራሱ በውጊያው ላይ በመጀመሪያ ተገደለ። 44እርሱ መውደቁን ባዩ ጊዜ የኒቃኖር ወታደሮች መሣሪያቸውን ጥለው ሸሹ። 45አይሁዳውያኑ ከአዳሳ እስከ ጋዜር ጠረፍ ድረስ የአንድ ቀን መንገድ ተከታተሏቸው፤ የሚከታተሏቸው መሆኑንም ለማመልከት መለከት ነፉ። 46ከይሁዳ ምድር መንደሮች ዙሪያ ሁሉ እነርሱን ለመክበብና ለመውጋት ሰዎች ይወጡ ነበር፤ ሁሉም በሰይፍ ተመትተው ወደቁ፤ አንድ እንኳ አላመለጠም። 47ከዚህ በኋላ የተዘረፉትንና የተማረኩትን ዕቃዎች ሰበሰቡ፤ የኒቃኖርን ራሱንና (ጭንቅላቱን) በትዕቢት የዘረጋውን ቀኝ እጁን ቆረጡና ወስደው በኢየሩሳሌም ሰው እንዲያያቸው አደረጉ። 48ሕዝቡ ደስ አለው፥ ያ ቀን ታላቅ የደስታ ቀን ተብሎ ተከበረ። 49ይህ ቀን በየዓመቱ በዓሥራ ሦስት አዳር (28 መጋቢት) እንዲከበር ተደነገገ። 50የይሁዳ ምድር ለጥቂት ጊዜ ዕረፍት አግኝቶ እፎይ አለ።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in