YouVersion Logo
Search Icon

1ኛ መጽሐፈ መቃብያን 3

3
የአይሁድ መሪ ይሁዳ መቃቢስ
የይሁዳ መቃቢስ ሙሾ
1መቃቢስ የተባለው ልጁ ይሁዳ በእርሱ ቦታ ተተካ (ተነሣ)። 2ወንድሞቹ የአባቱ ተከታዮች ሁሉ ረዱት፤ ስለ እስራኤል በደስታ ተዋጉ። 3የሕዝቡን ክቡርና ዝና አስፋፋ፤ ታላቅ ጀግና ሆኖ የጦር ልብስ ለበሰ፤ የጦር መሣሪያዎቹን ታጠቀ፤ ጦርነት ገጠመ። 4በአደን ላይ እንዳለ አንበሳ ሆነ፤ በምግቡና በግዳዩም ላይ ማግሳት ጀመረ፤ 5ክፉዎቹን እያሳደደ አባረራቸው፤ በሕዝቡ ላይ በደል የፈጸሙትን ሁሉ በእሳት አቃጠላቸው። 6ክፉዎቹ የእርሱ ፍራት አደረባቸው፤ ክፉ አድራጊዎች ሁሉ በፍራት ተንቀጠቀጡ፤ በእርሱ እጅ ነፃነት ተገኘ። 7የብዙዎችን ነገሥታት ሕይወት መራር አደረገባቸው፤ የእርሱ ሥራዎች ያዕቆብን (እስራኤልን) አስደሰቱ፤ መታሰቢያውም ለዘለዓለም ይመሰገናል። 8የይሁዳን ከተሞች አረሳቸው፤ አረማውያንንም ፈጃቸው፤ መዓትን ከእስራኤል አራቀ። 9እስከ ምድር ዳርቻ ዝናው ተሰማ፤ ጠፍተው የነበሩትን ሁሉ ሰበሰበ።
የመጀመሪያዎቹ የይሁዳ ድሎች
10አጰሎንዮስ (የንጉሡ ሹም) እስራኤልን ለመውጋት አረማውያንና ብዙ የሰማሪያ ሰዎችን ሰበሰበ። 11ይሁዳ ጉዳዩ ተነገረውና ጦርነት ሊገጥመው ወጣ፤ ተዋጋውና ገደለው፤ ብዙዎች ሞተው ወደቁ፤ የቀሩት ሸሹ። 12ምርኮዎቻቸው ተሰበሰቡ፤ ይሁዳ የአጰሎንዮስን ሰይፍ ወሰደ፤ በሕይወቱ ሙሉ በየጦርነቱ ላይ ተገለገለበት። 13የሦርያ የጦር አዛዥ ሴሮን ይሁዳ የጦር ሰዎችንና ታማኞች ሰዎችን እንዳከማቸ ሰማ፤ 14እንዲህም አለ፤ “እኔ ዝና አተርፋለሁ፤ በዚህ መንግሥትም ክብር አገኛለሁ፤ የንጉሡን ትእዛዝ ንቀው አንታዘዝም ያሉትን ይሁዳንና ሰዎቹን እወጋቸዋለሁ”። 15ስለዚህ በተራው እርሱም ዘመተ፤ ከእርሱም ጋር ብዙ አረማውያን ወታደሮች በእስራኤል ላይ በቀላቸውን ሊወጡ አብረውት ዘመቱ። 16ወደ ሴቶሮን አቀበት ቀረበ፤ ይሁዳም ከጥቂት ሰዎች ጋር ሆኖ ጦርነት ሊገጥመው ወጣ። 17ሰዎቹ ጦርነት ሊገጥማቸው የሚመጣውን የጦር ሠራዊት ባዩ ጊዜ ይሁዳን፥ “እኛ በቍጥር ጥቂቶች ነን፤ ታዲያ ከኛ በጣም ከሚበዙት ሰዎች ጋር መዋጋት እንዴት እንችላለን? ዛሬ ምንም ሳንበላ ነው የዋልነው ደክሞናል” አሉት። 18ይሁዳ እንዲህ ሲል መለሰላቸው፥ “የብዙ ሰዎች በጥቂት ሰዎች እጅ መውደቅ እኮ በአምላክ ዐይን አስቸጋሪ አይደለም፤ 19በጦርነት ድል መንሣት የሚገኘው ከሠራዊት ብዛት ሳይሆን ከእግዚአብሔር በሚመጣው ኃይል ነው። 20እነርሱ እኛንና ሚስቶቻችንን፥ ልጆቻችንን ለመደመሰስና ለመዝረፍ ወደ እኛ የሚመጡት በትዕቢትና በክፋት ተወጥረው ነው፤ 21እኛ ግን የምንዋጋው ስለ ሕይወታችንና ስለ ሕጋችን ብለን ነው፤ 22እርሱ አምላካችን በፊታችን ይሰባብራቸዋል፤ እናንተ እንግዲህ አትፍሩዋቸው”። 23ወዲያውኑ ንግግሩን እንደጨረሰ በድንገት አደጋ ጣለባቸው፤ ሴሮንና የጦር ሠራዊቱ በፊቱ ተሸነፉ፤ 24በቤቶሮን ቁልቁለት እስከ ሜዳው ድረስ ተከታትለው ወጉዋቸው፤ ስምንት መቶ ሰዎች ያህል ሞቱ፤ የቀሩት ወደ ፍልስጥኤማውያን አገር ሸሹ። 25ይሁዳና ወንድሞቹ በዙሪያቸው ያሉትን አረማውያን ሕዝቦችን ማስፈራራትና ማንቀጥቀጥ ጀመሩ። 26የይሁዳ ዝና እስከ ንጉሡ ደረሰ፤ ሕዝብ ሁሉ ይሁዳ ስላደረገው ጦርነት ይናገር ነበር።
በፋርስና በይሁዳ ወረራ የአንጥዮኩስ ዝግጅት፥ የሊስያስ ውክልና
27እነዚህን ነገሮች በሰማ ጊዜ ንጉሠ አንጥዮኩስ በጣሙን ተቆጣ፤ የመንግሥቱን ወታደሮች በሙሉ ሰብስባ እጅግ ከባድ የጦር ሠራዊት አዘጋጀ። 28የሀብት ግምጃ ቤቱንም ከፍቶ ለሠራዊቱ የዓመት ደሞዛቸውን አደላቸው፤ በተጨማሪም ለድንገተኛ ንቅናቄ ተዘጋጅተው እንዲጠባበቁ ተነገራቸው። 29በዚያን ጊዜ በሣጥኖቹ ውስጥ ገንዘብ እንዳልነበረና የክፍለ ሀገሩም የግብር ገቢ በቂ እንዳልነበረ አየ፤ ይህ የገንዘብ መጉደል የመጣው ከጥንት ጀምሮ ሁልጊዜ የነበሩት ሕጐች በመፍረሳቸው በአገሩ ውስጥ መከራና ብጥብጥ በመነሣቱ ምክንያት ነው። 30ከእርሱ በፊት ከነበሩት ነገሠታት ይበልጥ ቀድሞ በለጋስነት የሚያደርገውን ወጪና ልግስና ለማድረግ አለመቻሉን በመገንዘብ ፈራ፥ 31ጭንቀት ያዘው፤ ስለዚህ ከክፍለሀገሮች ግብር ለማስፈከልና ብዙ ገንዘብ ለመሰብሰብ ፋርስን ለመውረር ወሰነ። 32ከንጉሥ ጋር ዝምድና ያለውንና ክቡር ሰው የሆነውን ሊስያስን ከኤፈራጥስ እስከ ምስር ድንበሮች ድረስ ያሉትን ንጉሣዊ ጉዳዮች እንዲያከናውን ሾመና እዚያው ተወው። 33የልጁን የአንጥዮኩስን አስተደደግና ትምህርት ንጉሡ እስኪመለስ ድረስ እንዲከታተል ኃላፊነት ተሠጠው። 34ከሠራዊቱ እኩሌታውን ክፍልና ዝሆኖችን አስረከበው፤ ሰለውሳኔዎቹም አስፈላጊ ምክሮችን ለገሠው፤ በተለይም ስለ ይሁዳ አገርና ሰለ ኢየሩሳሌም ነዋሪዎች አስታወቀው። 35የእስራኤልን ኃይልና በኢየሩሳሌም ጥቂት የቀሩትንም ለመደምሰስና በዚያ ቦታ ላይ ያላቸውን ትውስታቸውን ለማጥፋት ወደ እነርሱ የጦር ሠራዊቱን መላክ እንደሚገባው ነገረው፤ 36በመላው አገራቸው ላይ የባዕድ አገር ሰዎችን ማስቀመጥና አገራቸውንም በዕጣ ማከፋፈል እንደሚገባ አስታወቀው። 37ንጉሡ ቀሪውን የወታደሮቹን ክፍል ይዞ በመቶ አርባ ሰባት ዓመተ ዓለም የመንግሥቱ መናገሻ ከተማ ከሆነችው ክፍል ይዞ በመቶ አርባ ሰባት ዓመተ ዓለም የመንግሥቱ መናገሻ ከተማ ከሆነችው አንጾኪያ ተነሣ፤ ኤፍራጥስን ተሻግሮ በላይኛዎቹ ክፍለ ሀገሮች አድርጐ አለፈ።
ኒቃኖርና ጐርጊያስ የሶሪያን ጦር ወደ ይሁዳ አዘመቱ
38ሊስያስ ከንጉሡ ወዳጆች መካከል ብርቱዎች የሆኑትን የዶራሜን ልጅ ጰጠሎሜዎስን፥ ኒቃኖርን፥ ጐርጊያስን መረጠ፤ 39ወደ ይሁዳም አገር እንዲሄድና በንጉሡ ትእዛዝ መሠረት አገሩን እንዲያጠፉ አርባ ሺህ እግረኞችንና ሰባት ሽህ ፈረሰኞችን ከእነርሱ ጋር ወደ ይሁዳ አገር ላከ። 40እነርሱ ከጦር ሠራዊታቸው ሁሉ ጋር ሄደው ወደ አማሁስ አጠገብ ደረሱና ሠፈራቸውን በሜዳው ላይ አደረጉ፤ 41የእዚያ አገር ነጋዴዎች ዝናቸውን ሰምተው ብዙ ወርቅና ብር፥ እግር ብረቶችም ይዘው መጡ፤ የእስራኤልን ሰዎች እንደ ባርያ ገዝተዋቸው ለመውሰድ ወደ ሰፈሩ ሄዱ። የሦርያ (የኢዶምያስ) ወታደሮችና የፍልስጥኤማውያን አገር ወታደሮችም ከእነርሱ ጋር ተባበሩ። 42ይሁዳና ወንድሞቹ መከራቸው እየከበደ እንደሄደና በምድራቸው ላይ የጦር ሠራዊቶች እንደሰፈሩ አዩ። ሕዝቡን ጠራርጐ ማጥፋት ነው ያለውን የንጉሡንም ውሳኔ አወቁ። 43“ሕዝባችንን ከጥፋቱ እናውጣው፤ ስለ ሕዝባችንና ስለ ቅዱስ ቦታችን እንዋጋ” ተባባሉ። 44ለጦርነት ለመዘጋጀት በመጸለይ የእግዚአብሔርን ርኀራኄና ምሕረት ለመለመን ሕዝቡን ሰበሰቡ። 45ኢየሩሳሌም ባዶዋን ቀርታ ነበር፤ ከልጆችዋ ማንም የሚገባና የሚወጣ አልነበረም፤ ቤተ መቅደሱ ተበዝብዞ ነበር፤ አረመኔ ገብቶበታል፥ በያዕቆብ (በእስራኤል) እልልታዎች ተወግደዋል፤ ዋሽንትና ክራር አይሰሙበትም።
በምጽጳ የአይሁዳውያን መሰባሰብ
46ተሰብስበው በኢየሩሳሌም ፊት ለፊት ወደሚገኘው ወደ ምጽጳ ወጡ፤ ምክንያቱም ቀድሞ እስራኤላውያን የጸሎት ቦታ ነበራቸውና። 47በዚያን ቀን ጾሙ፥ ያደፈ ልብስ ለበሱ፥ ራሳቸው ላይ አመድ ነሰነሱ፥ ልብሳቸውን ቀደዱ፥ 48መቼም አረማውያን ወደ ጣዕቶቻቸው ምስሎች ይጸልያሉ፤ እስራኤላውያን ግን ለማንበብ የሙሴን ሕግ መጽሐፍ ከፈቱ፤ 49የካህናት አልባሳትን የመጀመሪያ ምርቶችን ዓሥራቶችን አመጡ፤ የስለታቸውን ቀን የፈጸሙትን ናዝራውያንንም አመጡ። 50ድምጻቸውን ከፍ አድርገው ወደ ሰማይ እንዲህ አሉ፥ “እነዚህን ሰዎች ምን እናድርጋቸው? ወዴትስ እንውሰዳቸው? 51ቅዱስ ቦታህን በዝብዘውታል፥ አርክሰውታል፥ ካህናትህ በኀዘንና በውርደት ላይ ናቸው። 52እነሆ አረማውያን ሕዝቦች እኛን ለማጥፋት ተስማምተውብናል፤ እነርሱ በእኛ ላይ የሚያቅዱትን ሁሉ አንተ ታውቃለህ፤ 53አንተ ካልረዳኸን እንዴት አድርገን ልንቋቋማቸው እንችላለን?” 54ቀጥሎም መለከት በመንፋት ታላቅ ድምፅ አሰሙ። 55ከዚህ በኋላ ይሁዳ ሕዝቡን የሚመሩ የሺህ አለቆችን፥ የመቶ አለቆችን፥ የሃምሳ አለቆችን፥ የዐሥር አለቆችን ሾመ። 56ቤታቸውን የሚሠሩትን ወይም ለማግባት የታጩትን በቅርብ ወይን የተከሉትን ወይም ፍርሃት ያደረባቸውን በሕጉ መሠረት ወደ ቤታቸው እንዲሄዱ ነገራቸው። 57በዚያን ጊዜ የጦር ሠራዊቱ መሄድ ጀመረና በአማሁስ በስተ ደቡብ ሰፈረ። 58ይሁዳ እንዲህ አላቸው፥ “ተዘጋጁ ጀግኖች ሁኑ፥ እኛንና መቅደሳችሁን ለማጥፋት የተሰበሰቡትን እነዚህ አረማውያን ሕዝቦች ነገ ለመውጋት ዝግጁዎች ሆናችሁ ቆዩ፤ 59ምክንያቱም የሕዝባችንንና የቤተ መቅደሳችንን ጥፋት ከማየት እየተዋጋን መሞት ይሻለናል። 60የእግዚአብሔር (የሰማይ) ፈቃድ ይፈጸማል”።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in