YouVersion Logo
Search Icon

የማርቆስ ወንጌል 2

2
ኢየሱስ ሽባውን ሰው መፈወሱ
(ማቴ. 9፥1-8ሉቃ. 5፥17-26)
1ከጥቂት ቀን በኋላ ኢየሱስ ወደ ቅፍርናሆም ተመልሶ መጣ፤ እዚያ በቤት ውስጥ መሆኑ ተሰማ። 2ቤቱ የማይበቃ ሆኖ ደጁ እንኳ እስኪጠብ ድረስ ብዙ ሰዎች ተሰበሰቡ፤ ቃሉንም ያስተምራቸው ነበር። 3በዚያን ጊዜ አራት ሰዎች አንድ ሽባ ሰው ተሸክመው ወደ እርሱ መጡ። 4ከሕዝቡም ብዛት የተነሣ ሽባውን ወደ ኢየሱስ ማቅረብ ቢያቅታቸው የቤቱን ጣራ ኢየሱስ ባለበት በኩል ከፍተው ሽባውን ከነአልጋው አወረዱት። 5ኢየሱስም እምነታቸውን አይቶ ሽባውን “ልጄ ኃጢአትህ ይቅር ተብሎልሃል” አለው።
6በዚያ ተቀምጠው የነበሩ አንዳንድ የሕግ መምህራን በልባቸው እንዲህ አሉ፤ 7“ይህ ሰው ለምን እንዲህ ያለ ስድብ በእግዚአብሔር ላይ ይናገራል? ከአንዱ ከእግዚአብሔር በቀር ኃጢአትን ይቅር ማለት የሚችል ማን ነው?”
8ወዲያውኑ ኢየሱስ ይህን የልባቸውን ሐሳብ በመንፈሱ ዐውቆ እንዲህ አላቸው፦ “ስለምን በልባችሁ ይህን ታስባላችሁ? 9ሽባውን፥ ‘ኃጢአትህ ይቅር ተብሎልሃል፤’ ከማለትና፥ ‘ተነሥተህ አልጋህን ተሸከምና ሂድ!’ ከማለት የትኛው ይቀላል? 10ነገር ግን የሰው ልጅ በምድር ላይ ኃጢአትን ይቅር ለማለት ሥልጣን ያለው መሆኑን እንድታውቁ” ብሎ ሽባውን፥ 11“ተነሥ፤ አልጋህን ተሸከምና ወደ ቤትህ ሂድ እልሃለሁ” አለው።
12ሽባውም ወዲያውኑ ተነሣና አልጋውን ተሸክሞ በሰዎቹ ሁሉ ፊት ወጣ። ስለዚህም ሰዎቹ ሁሉ ተደንቀው እንዲህ ያለ ነገር ከቶ አይተን አናውቅም እያሉ እግዚአብሔርን አመሰገኑ።
ኢየሱስ ማቴዎስ የተባለውን ሌዊን መጥራቱ
(ማቴ. 9፥9-13ሉቃ. 5፥27-32)
13ኢየሱስም እንደገና ወደ ገሊላ ባሕር አጠገብ ሄደ፤ ሕዝቡም ሁሉ ተሰብስበው ወደ እርሱ መጡና አስተማራቸው። 14በዚያም ሲያልፍ ሳለ በቀረጥ መቀበያ ስፍራ ተቀምጦ የነበረውን የእልፍዮስን ልጅ ሌዊን አይቶ፥ “ተከተለኝ” አለው፤ እርሱም ተነሥቶ ተከተለው።
15ከዚህ በኋላ ኢየሱስ በሌዊ ቤት በማእድ ተቀምጦ ነበር፤ ብዙ ሰዎችም ተከትለውት ስለ ነበር ከእነርሱ ብዙ ቀራጮችና ኃጢአተኞች ከኢየሱስና ከደቀ መዛሙርቱ ጋር በገበታ ቀርበው ነበር። 16ከፈሪሳውያን ወገን የሆኑ የሕግ መምህራን ኢየሱስ ከቀራጮችና ከኃጢአተኞች ጋር ሲበላ አይተው “ከቀራጮችና ከኃጢአተኞች ጋር የሚበላውና የሚጠጣው ስለምንድን ነው?” በማለት ደቀ መዛሙርቱን ጠየቁአቸው።
17ኢየሱስም ይህን ሰምቶ፦ “በሽተኞች እንጂ ጤነኞች ሐኪም አያስፈልጋቸውም፤ እኔም የመጣሁት ጻድቃንን ሳይሆን ኃጢአተኞችን ወደ ንስሓ ለመጥራት ነው፤” አላቸው።
ስለ ጾም የቀረበ ጥያቄ
(ማቴ. 9፥14-17ሉቃ. 5፥33-39)
18የዮሐንስ ደቀ መዛሙርትና ፈሪሳውያን ይጾሙ ነበር። አንዳንድ ሰዎች ወደ ኢየሱስ መጥተው፦ “የዮሐንስና የፈሪሳውያን ደቀ መዛሙርት ይጾማሉ፤ የአንተ ደቀ መዛሙርት ግን የማይጾሙት ስለምንድን ነው?” አሉት።
19ኢየሱስም “ሙሽራው ከእነርሱ ጋር እያለ ሚዜዎች መጾም ይገባቸዋልን? አይደለም! ሙሽራው ከእነርሱ ጋር ሳለ መጾም አይገባቸውም። 20ነገር ግን ሙሽራው ከእነርሱ የሚወሰድበት ቀን ይመጣል፤ በዚያን ጊዜ ይጾማሉ።
21“ባረጀ ልብስ ላይ አዲስ ዕራፊ የሚጥፍ የለም፤ ይህ ቢደረግ ግን፥ አዲሱ ዕራፊ አሮጌውን ልብስ በመሸምቀቅ ይቀደዋል፤ ቀዳዳውም ከበፊቱ የባሰ ይሆናል። 22እንዲሁም በአረጀ የወይን ጠጅ አቁማዳ አዲስ የወይን ጠጅ የሚያኖር የለም፤ ቢደረግ ግን የወይን ጠጁ አቁማዳውን ያፈነዳዋል፤ የወይን ጠጁም ይፈስሳል፤ አቁማዳውም ከንቱ ይሆናል። ስለዚህ ለአዲስ የወይን ጠጅ አዲስ አቁማዳ ያስፈልገዋል፤” አላቸው።
ስለ ሰንበት የቀረበ ጥያቄ
(ማቴ. 12፥1-8ሉቃ. 6፥1-5)
23በሰንበት ቀን ኢየሱስ በስንዴ እርሻ መካከል ያልፍ ነበር። ደቀ መዛሙርቱ ሲሄዱ የስንዴ እሸት መቅጠፍ ጀመሩ። #ዘዳ. 23፥25። 24ፈሪሳውያንም “እነሆ፥ ደቀ መዛሙርትህ በሰንበት ያልተፈቀደውን ስለምን ያደርጋሉ?” ሲሉ ጠየቁት።
25ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “ዳዊት ከተከታዮቹ ጋር በተራበና በተቸገረ ጊዜ ምን እንዳደረገ አላነበባችሁምን? #1ሳሙ. 21፥1-6። 26አብያታር የካህናት አለቃ በነበረበት ዘመን እርሱ ወደ እግዚአብሔር ቤት ገብቶ፥ ከካህናት በቀር ለሌሎች መብላት ያልተፈቀደውን፥ የተቀደሰውን የመባ ኅብስት በላ፤ ከእርሱም ጋር ለነበሩት ሰዎች ሰጣቸው።” #ዘሌ. 24፥9።
27ደግሞም ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፦ “ሰንበት ለሰው ተሠራ እንጂ ሰው ለሰንበት አልተፈጠረም። 28እንዲሁም የሰው ልጅ ለሰንበትም ጌታዋ ነው።”

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in