YouVersion Logo
Search Icon

የማርቆስ ወንጌል 1

1
የመጥምቁ ዮሐንስ ስብከት
(ማቴ. 3፥1-12ሉቃ. 3፥1-18ዮሐ. 1፥19-28)
1ይህ የእግዚአብሔር ልጅ የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል መጀመሪያ ነው፤ #1፥1 አንዳንድ ቅጂዎች “የእግዚአብሔር ልጅ” የሚለውን ቃል አይጨምሩም። 2በነቢዩ ኢሳይያስ
“እነሆ፥ መንገድህን የሚጠርግ
መልእክተኛዬን በፊትህ አስቀድሜ እልካለሁ፤ #ሚል. 3፥1።
3ይህም፦
‘የጌታን መንገድ አዘጋጁ፤
ጥርጊያውንም አስተካክሉ’ እያለ፥
በበረሓ ከፍ አድርጎ የሚናገር ሰው ድምፅ” #ኢሳ. 40፥3።
ተብሎ እንደ ተጻፈው ነው።
4ስለዚህ መጥምቁ ዮሐንስ “የኃጢአትን ይቅርታ እንድታገኙ፥ ንስሓ ገብታችሁ ተጠመቁ” በማለት በበረሓ እያወጀ መጣ። 5ከይሁዳ ምድርና ከኢየሩሳሌም ከተማ ብዙ ሰዎች ወደ እርሱ ይመጡ ነበር፤ ኃጢአታቸውንም እየተናዘዙ በዮርዳኖስ ወንዝ በእርሱ እጅ ይጠመቁ ነበር።
6የዮሐንስ ልብስ ከግመል ጠጒር የተሠራ ነበር፤ በወገቡም ጠፍር ይታጠቅ ነበር፤ ምግቡም አንበጣና የጣዝማ ማር. ነበር። #2ነገ. 1፥8። 7እንዲህም ይል ነበር፦ “የጫማውን ማሰሪያ ጐንበስ ብዬ ለመፍታት እንኳ የማልበቃ ከእኔ እጅግ የሚበልጥ ከእኔ በኋላ ይመጣል፤ 8እኔ በውሃ አጠምቃችኋለሁ፤ እርሱ ግን በመንፈስ ቅዱስ ያጠምቃችኋል።”
የኢየሱስ መጠመቅና መፈተን
(ማቴ. 3፥13-174፥1-11ሉቃ. 3፥21-224፥1-13)
9በዚያን ጊዜ ኢየሱስ በገሊላ ክፍለ ሀገር ከምትገኝ ከናዝሬት ከተማ መጥቶ በዮርዳኖስ ወንዝ በዮሐንስ እጅ ተጠመቀ። 10ዮሐንስም ወዲያውኑ ኢየሱስ ከውሃው እንደ ወጣ ሰማይ ሲከፈትና መንፈስ ቅዱስም በርግብ አምሳል ሆኖ በእርሱ ላይ ሲወርድ አየ። 11በዚያን ጊዜ፥ “በአንተ ደስ የሚለኝ፥ የምወድህ ልጄ ነህ” የሚል ድምፅ ከሰማይ መጣ። #ዘፍ. 22፥2፤ መዝ. 2፥7፤ ኢሳ. 42፥1፤ ማቴ. 3፥17፤ 12፥18፤ ማር. 9፥7፤ ሉቃ. 3፥22።
12ወዲያውኑ የእግዚአብሔር መንፈስ ኢየሱስን ወደ በረሓ ወሰደው። 13በዚያም በረሓ በሰይጣን እየተፈተነ አርባ ቀን ቈየ፤ ከአራዊትም ጋር ነበረ፤ መላእክትም አገለገሉት።
ኢየሱስ የማስተማር ሥራውን በገሊላ እንደ ጀመረ
(ማቴ. 4፥14-17ሉቃ. 4፥14-15)
14ዮሐንስም ተይዞ ወደ እስር ቤት ከገባ በኋላ ኢየሱስ የእግዚአብሔርን ወንጌል እየሰበከ ወደ ገሊላ መጣ። 15ሲያስተምርም፦ “ዘመኑ ተፈጽሞአል፤ የእግዚአብሔር መንግሥት ቀርባለችና ንስሓ ግቡ! በወንጌልም እመኑ!” ይል ነበር። #ማቴ. 3፥2።
ኢየሱስ አራት ዓሣ አጥማጆችን እንደ ጠራ
(ማቴ. 4፥18-22ሉቃ. 5፥1-11)
16ከዚህ በኋላ ኢየሱስ በገሊላ ባሕር አጠገብ ሲያልፍ ስምዖንና ወንድሙ እንድርያስ ዓሣ አጥማጆች ስለ ነበሩ መረባቸውን ወደ ባሕር ሲጥሉ አያቸው። 17ኢየሱስም፦ “ኑ ተከተሉኝ፤ ዓሣን እንደምታጠምዱ ሁሉ ሰዎችንም እንድትሰበስቡልኝ አደርጋችኋለሁ፤” አላቸው። 18እነርሱም ወዲያውኑ መረባቸውን ትተው ተከተሉት።
19ከዚያም ጥቂት አለፍ እንዳለ፥ ሌሎች ሁለት ወንድማማችን አየ፤ እነርሱም የዘብዴዎስ ልጆች ያዕቆብና ዮሐንስ ነበሩ፤ እነርሱ በጀልባ ላይ ሆነው መረባቸውን ይጠግኑ ነበር፤ 20ኢየሱስ ወዲያውኑ ጠራቸው፤ እነርሱም አባታቸውን ዘብዴዎስን ከሠራተኞቹ ጋር በጀልባው ላይ ትተውት ኢየሱስን ተከተሉት።
ርኩስ መንፈስ ያደረበት ሰው መዳኑ
(ሉቃ. 4፥31-37)
21አልፈውም ወደ ቅፍርናሆም ከተማ ደረሱ፤ ወዲያው በሚቀጥለውም ሰንበት ኢየሱስ ወደ ምኲራብ ገብቶ ማስተማር ጀመረ። #1፥21 ምኲራብ፦ የአይሁድ የጸሎት ቤት ነው። 22ኢየሱስ፥ የሕግ መምህራን እንደሚያስተምሩት ዐይነት ሳይሆን እንደ ባለሥልጣን ያስተምራቸው ስለ ነበረ የሰሙት ሁሉ በትምህርቱ ተደነቁ።
23አንድ ርኩስ መንፈስ ያደረበት በምኲራባቸው የነበረ አንድ ሰው እንዲህ ሲል ጮኸ፤ 24“የናዝሬቱ ኢየሱስ ሆይ፥ አንተ ከእኛ ጋር ምን ጉዳይ አለህ? ልታጠፋን መጣህን? አንተ ማን እንደ ሆንክ እኔ ዐውቃለሁ፤ አንተ የእግዚአብሔር ቅዱስ ነህ።”
25ኢየሱስም ርኩሱን መንፈስ “ጸጥ ብለህ ከእርሱ ውጣ!” ብሎ ገሠጸው።
26ርኩሱ መንፈስ ሰውየውን ጥሎ ካንፈራገጠው በኋላ በታላቅ ድምፅ እየጮኸ ከእርሱ ወጣ። 27“ይህ ምንድን ነው? ምን ዐይነት አዲስ ትምህርት ነው? ርኩሳን መናፍስትን እንኳ በሥልጣኑ ያዛል፤ እነርሱም ይታዘዙለታል፤” እያሉ ሁሉም በመገረም እርስ በርሳቸው ይጠያየቁ ጀመር።
28ወዲያውኑ፥ የኢየሱስ ዝና በገሊላ ዙሪያ ባሉት አገሮች ሁሉ ተሰማ።
ኢየሱስ ብዙ ሕመምተኞችን መፈወሱ
(ማቴ. 8፥14-17ሉቃ. 4፥38-41)
29በዚያኑ ጊዜ ኢየሱስ ከምኲራብ ወጥቶ ከያዕቆብና ከዮሐንስ ጋር ወደ ስምዖንና እንድርያስ ቤት ገባ። 30በቤት ውስጥ፥ የስምዖን ዐማት በንዳድ ሕመም አተኲሶአት ተኝታ ነበር፤ ስለ እርስዋም መታመም ወዲያው ለኢየሱስ ነገሩት። 31ኢየሱስም ወደ እርስዋ ቀረበና እጅዋን ይዞ አስነሣት፤ ትኲሳቱም ወዲያው ለቀቃት፤ ተነሥታም አስተናገደቻቸው።
32ፀሐይ ጠልቃ በመሸ ጊዜ ሰዎች በሽተኞችንና በአጋንንት የተያዙትን ሁሉ ወደ ኢየሱስ አመጡ። 33የከተማው ሰዎች ሁሉ በደጅ ተሰብስበው ነበር። 34ኢየሱስ በልዩ ልዩ በሽታ የሚሠቃዩትን ብዙ ሰዎች ፈወሰ፤ ብዙ አጋንንትንም አስወጣ፤ አጋንንቱም እርሱ ማን እንደ ሆነ ያውቁ ነበር፤ ይሁን እንጂ ኢየሱስ እንዲናገሩ አልፈቀደላቸውም።
ኢየሱስ በገሊላ ወንጌልን ማስተማሩ
(ሉቃ. 4፥42-44)
35ሊነጋ ሲል፥ ኢየሱስ በማለዳ ተነሥቶ ወጣና ለመጸለይ ወደ አንድ ገለልተኛ ቦታ ሄደ፤ 36ስምዖንና ከእርሱ ጋር የነበሩት እርሱን ፍለጋ ወጥተው ሄዱ። 37ባገኙትም ጊዜ፥ “ሰዎች ሁሉ ይፈልጉሃል” አሉት።
38ኢየሱስም፦ “እኔ የመጣሁት ለማስተማር ስለ ሆነ ወንጌልን እንዳስተምር በቅርብ ወዳሉት መንደሮች እንሂድ!” አላቸው።
39ስለዚህ በየምኲራቦቻቸው እያስተማረና አጋንንትን እያስወጣ በገሊላ ሁሉ ይዘዋወር ነበር። #ማቴ. 4፥23፤ 9፥35።
ኢየሱስ ለምጻሙን ሰው ማንጻቱ
(ማቴ. 8፥1-4ሉቃ. 5፥12-17)
40አንድ ለምጻም#1፥40 ለምጽ፦ እንደ መጽሐፍ ቅዱስ አገላለጥ፥ በሰውነት ላይ የሚታይ ልዩ ልዩ ዐይነት ተላላፊ የቆዳ በሽታን ሁሉ ያመለክታል። ወደ ኢየሱስ መጣና በእግሩ ሥር ተንበርክኮ፦ “ብትፈቅድስ ልታነጻኝ ትችላለህ፤” ሲል ለመነው።
41ኢየሱስም ራራለትና እጁን ዘርግቶ እየዳሰሰው፥ “ፈቅጃለሁ፤ ንጻ!” አለው። 42ሰውየውም ወዲያውኑ ከለምጹ ነጻ። 43ኢየሱስ ሰውዬውን በጥብቅ አስጠንቅቆ አሰናበተው፤ 44“ይህን ነገር ለማንም እንዳትናገር ተጠንቀቅ፤ ነገር ግን ሄደህ ራስህን ለካህን አሳይ፤ ለሕዝቡም ምስክር እንዲሆን ስለ መዳንህ ሙሴ ያዘዘውን መሥዋዕት አቅርብ፤” ብሎ አዘዘው። #ዘሌ. 4፥1-32።
45ይሁን እንጂ ሰውየው ከዚያ ወጥቶ ይህን ነገር ለሰው ሁሉ ማውራት ጀመረ። በዚህም ምክንያት ኢየሱስ ወደ ማናቸውም ከተማ በግልጥ መግባት አልቻለም። ነገር ግን ከከተማ ውጪ ሰው በሌለበት ቦታ ይኖር ነበር፤ ሆኖም ሰዎች ከየስፍራው ወደ እርሱ ይመጡ ነበር።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in