YouVersion Logo
Search Icon

የማቴዎስ ወንጌል መግቢያ

መግቢያ
የማቴዎስ ወንጌል፥ ኢየሱስ የመምጣቱ ተስፋ አስቀድሞ የተነገረለት አዳኝ መሆኑንና እግዚአብሔር በብሉይ ኪዳን ለሕዝቡ የሰጠውን የተስፋ ቃል የፈጸመውም በእርሱ አማካይነት መሆኑን የሚያበሥረውን የምሥራች ቃል የያዘ ነው። ይህም የምሥራች ቃል ኢየሱስ በመካከላቸው ተወልዶ ላደገው ለአይሁድ ብቻ ሳይሆን፥ ለመላው ዓለም ጭምር ነው።
የማቴዎስ ወንጌል በጥንቃቄ የተዘጋጀ መጽሐፍ ነው፤ ከኢየሱስ መወለድ ይጀምርና ስለ ጥምቀቱና ስለ ፈተናው ካብራራ በኋላ፥ በገሊላ የፈጸመውን የስብከት፥ የማስተማርና የመፈወስ አገልግሎት ያቀርባል። ከዚያም በመቀጠል ኢየሱስ ከገሊላ ወደ ኢየሩሳሌም ስላደረገው ጒዞና በዚህ ዓለም በቈየበት ዘመን በመጨረሻ ሳምንት ስለ ሆኑት ነገሮች ይዘረዝራል፤ እነዚህም ነገሮች ስቅለቱን፥ ሞቱንና ትንሣኤውን ያጠቃልላሉ።
ይህ ወንጌል ኢየሱስን፥ የእግዚአብሔርን ሕግ ለመተርጐም ሥልጣን ያለውና ስለ እግዚአብሔር መንግሥት የሚያስተምር ታላቅ መምህር እንደ ሆነ አድርጎ ያቀርበዋል። ከትምህርቱ አብዛኛው ክፍል በተለያየ መልክ በተጠናቀሩ አምስት ክፍሎች ይመደባል፦
1. የእግዚአብሔርን መንግሥት ዜጎች ጠባይ፥ ሥራ፥ መብት፥ ግዴታና የመጨረሻ ዕድል ፈንታ የሚያስረዳው የተራራው ስብከት (ም. 5-7)
2. ዐሥራ ሁለቱ ደቀ መዛሙርት ለወንጌል ስብከት በተላኩበት ጊዜ የተሰጡአቸው መመሪያዎች (ም. 10)
3. ስለ እግዚአብሔር መንግሥት የቀረቡ ልዩ ልዩ ምሳሌዎች (ም. 13)
4. የደቀ መዝሙርነትን ፍች የሚያስረዳ ትምህርት (ም. 18)
5. ስለ አሁኑ ዘመን ፍጻሜና ስለ እግዚአብሔር መንግሥት መምጣት የተሰጠ ትምህርት (ከም. 24-25)
አጠቃላይ የመጽሐፉ ይዘት
የኢየሱስ ክርስቶስ የዘር ሐረግና ልደቱ 1፥1—2፥23
የመጥምቁ ዮሐንስ አገልግሎት 3፥1-12
የኢየሱስ መጠመቅና መፈተን 3፥13—4፥11
ኢየሱስ ሥራውን በገሊላ መጀመሩ 4፥12—18፥35
ከገሊላ ወደ ኢየሩሳሌም 19፥1—20፥34
የመጨረሻው ሳምንት በኢየሩሳሌምና በአካባቢዋ 21፥1—27፥66
የጌታችን ትንሣኤና መገለጡ 28፥1-20

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in