YouVersion Logo
Search Icon

የማቴዎስ ወንጌል 1

1
የኢየሱስ ክርስቶስ የትውልድ ሐረግ
(ሉቃ. 3፥23-38)
1የዳዊትና የአብርሃም ዘር የሆነው የኢየሱስ ክርስቶስ የትውልድ ሐረግ ይህ ነው፦ #መዝ. 132፥11፤ ኢሳ. 11፥1።
2አብርሃም ይስሐቅን ወለደ፤ ይስሐቅ ያዕቆብን ወለደ፤ ያዕቆብ ይሁዳንና ወንድሞቹን ወለደ፤ 3ይሁዳ ፋሬስንና ዛራን ትዕማር ከምትባል ሴት ወለደ፤ ፋሬስ ሔስሮንን ወለደ፤ ሔስሮንም አራምን ወለደ፤ 4አራም ዓሚናዳብን ወለደ፤ ዓሚናዳብ ነአሶንን ወለደ፤ ነአሶን ሰልሞንን ወለደ፤ 5ሰልሞን ቦዔዝን ረዓብ ከምትባል ሴት ወለደ፤ ቦዔዝ ኢዮቤድን ሩት ከምትባል ሴት ወለደ፤ ኢዮቤድ እሴይን ወለደ፤ 6እሴይ ንጉሥ ዳዊትን ወለደ። #ሩት 4፥18-22፤ 1ዜ.መ. 2፥13-15።
ንጉሥ ዳዊት የኦርዮ ሚስት ከነበረችው ሰሎሞንን ወለደ፤ 7ሰሎሞን ሮብዓምን ወለደ፤ ሮብዓም አቢያን ወለደ፤ አቢያ አሳፍን ወለደ፤ 8አሳፍ ኢዮሣፍጥን ወለደ፤ ኢዮሣፍጥ ኢዮራምን ወለደ፤ ኢዮራም ዖዝያን ወለደ፤ 9ዖዝያንም ኢዮአታምን ወለደ፤ ኢዮአታም አካዝን ወለደ፤ አካዝ ሕዝቅያስን ወለደ፤ 10ሕዝቅያስ ምናሴን ወለደ፤ ምናሴ አሞጽን ወለደ፤ አሞጽ ኢዮስያስን ወለደ፤ 11ኢዮስያስ የእስራኤል ሕዝብ ወደ ባቢሎን ተማርከው በሄዱበት ዘመን ኢኮንያንንና ወንድሞቹን ወለደ። #2ነገ. 24፥14-15፤ 2ዜ.መ. 36፥10፤ ኤር. 27፥20።
12ከባቢሎን ምርኮ በኋላ ኢኮንያን ሰላትያልን ወለደ፤ ሰላትያል ዘሩባቤልን ወለደ፤ 13ዘሩባቤል አብዩድን ወለደ፤ አብዩድ ኤልያቄምን ወለደ፤ ኤልያቄም አዞርን ወለደ፤ 14አዞር ሳዶቅን ወለደ፤ ሳዶቅ አኪምን ወለደ፤ አኪም ኤልዩድን ወለደ፤ 15ኤልዩድ አልዓዛርን ወለደ፤ አልዓዛር ማታንን ወለደ፤ ማታን ያዕቆብን ወለደ፤ 16ያዕቆብ መሲሕ የተባለውን ኢየሱስን የወለደች የማርያም እጮኛ የሆነውን ዮሴፍን ወለደ። #1፥16 መሲሕ፦ ክርስቶስ ማለት መሲሕ ወይም የተቀባ ማለት ነው።
17እንግዲህ ከአብርሃም እስከ ዳዊት ዐሥራ አራት ትውልድ፥ ከዳዊት እስከ ባቢሎን ምርኮ ዐሥራ አራት ትውልድ፥ ከባቢሎን ምርኮ እስከ መሲሕ ዐሥራ አራት ትውልድ ነው።
የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት
(ሉቃ. 2፥1-7)
18ኢየሱስ ክርስቶስ የተወለደበት ሁኔታ እንዲህ ነበር፦ እናቱ ማርያም ለዮሴፍ ታጭታ ሳለች፥ ሳይገናኙ በመንፈስ ቅዱስ ፀንሳ ተገኘች። #ሉቃ. 1፥27። 19እጮኛዋ ዮሴፍ ደግ ሰው ስለ ነበረ፥ ማርያምን በሰው ፊት ሊያጋልጣት አልፈለገም፤ ስለዚህ በስውር ሊተዋት አሰበ። 20ነገር ግን ይህን ነገር ሲያስብ ሳለ፥ የጌታ መልአክ በሕልም ተገልጦለት እንዲህ አለው፤ “የዳዊት ዘር ዮሴፍ ሆይ! እጮኛህ ማርያም የፀነሰችው በመንፈስ ቅዱስ ስለ ሆነ፥ እርስዋን ወደ ቤትህ ለመውሰድ አትፍራ። 21እርስዋ ወንድ ልጅ ትወልዳለች፤ እርሱ ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ስለሚያድን ስሙን ኢየሱስ ትለዋለህ።” #ሉቃ. 1፥31።
22ይህም ሁሉ የሆነው ጌታ እንዲህ ሲል በነቢይ አማካይነት የተናገረው እንዲፈጸም ነው፤ 23“እነሆ፥ ድንግል ትፀንሳለች፤ ወንድ ልጅም ትወልዳለች፤ ስሙም ‘ዐማኑኤል’ ተብሎ ይጠራል።” ዐማኑኤል ማለትም “እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ነው” ማለት ነው። #ኢሳ. 7፥14።
24ዮሴፍ ከእንቅልፉ በነቃ ጊዜ፥ የጌታ መልአክ ባዘዘው መሠረት እጮኛውን ማርያምን ወደ ቤቱ ወሰዳት። 25ይሁን እንጂ፥ ልጅዋን እስከ ወለደች ድረስ አላወቃትም ስሙንም ኢየሱስ ብሎ ጠራው። #ሉቃ. 2፥21። #1፥25 አላወቃትም ማለት፦ እንደ ባልና እንደ ሚስት ግንኙነት አላደረጉም ማለት ነው።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in