YouVersion Logo
Search Icon

የማቴዎስ ወንጌል 8

8
ኢየሱስ ለምጻሙን ሰው ማንጻቱ
(ማር. 1፥40-45ሉቃ. 5፥12-16) #8፥0 ለምጽ፦ እንደ መጽሐፍ ቅዱስ አገላለጥ በሰውነት ላይ የሚታይ ልዩ ልዩ ዐይነት የቆዳ በሽታን ሁሉ ያመለክታል።
1ኢየሱስ ከተራራው በወረደ ጊዜ፥ እጅግ ብዙ ሰዎች ተከተሉት። 2በዚህ ጊዜ አንድ ለምጻም ሰው መጥቶ ሰገደለትና “ጌታ ሆይ! ብትፈቅድስ ልታነጻኝ ትችላለህ” አለ። 3ኢየሱስም እጁን ዘርግቶ ዳሰሰውና “ፈቅጃለሁ፤ ንጻ!” አለው። ለምጻሙም ወዲያውኑ ከለምጹ ነጻ። 4ከዚህ በኋላ ኢየሱስ፥ ከለምጹ የዳነውን ሰው እንዲህ አለው፤ “ይህን ነገር ለማንም አትናገር፤ ነገር ግን ሄደህ መዳንህን ለካህን አሳይ፤ ምስክር ይሆንባቸው ዘንድ፥ ስለ መዳንህ ሙሴ ያዘዘውን መባ ለእግዚአብሔር አቅርብ” አለው።
ኢየሱስ የመቶ አለቃውን አገልጋይ እንደ ፈወሰ
(ሉቃ. 7፥1-10)
5ኢየሱስ ወደ ቅፍርናሆም ከተማ በገባ ጊዜ፥ አንድ ሮማዊ የመቶ አለቃ ወደ እርሱ ቀርቦ በመለመን፥ 6“ጌታ ሆይ፥ አገልጋዬ ሽባ ሆኖ፥ እጅግ በመሠቃየት በቤት ተኝቶአል” አለው። 7ኢየሱስም “እኔ መጥቼ እፈውሰዋለሁ” አለው። 8የመቶ አለቃው ግን እንዲህ ሲል መለሰ፦ “ጌታ ሆይ! አንተ ወደ ቤቴ እንድትገባ እኔ የተገባሁ ሰው አይደለሁም፤ ነገር ግን አንዲት ቃል ብቻ ተናገር፤ አገልጋዬም ይድናል። 9እኔ ራሴ ለባለ ሥልጣኖች ታዛዥ ስሆን፥ ከእኔ በታች የማዛቸው ወታደሮች አሉኝ፤ ከእነርሱ አንዱን ‘ሂድ!’ ስለው ይሄዳል፤ ሌላውንም ‘ና!’ ስለው ይመጣል፤ አገልጋዬም ‘ይህን አድርግ!’ ስለው ያደርጋል።”
10ኢየሱስ ይህን በሰማ ጊዜ ተደነቀ፤ ይከተሉት የነበሩትን ሰዎች እንዲህ አላቸው፤ “በእውነት እላችኋለሁ፤ ይህን የሚያኽል ትልቅ እምነት ያለው አንድም ሰው በእስራኤል ስንኳ አላገኘሁም። 11ብዙዎች ከምሥራቅና ከምዕራብ ይመጣሉ፤ ከአብርሃም፥ ከይስሐቅ፥ ከያዕቆብ ጋር በመንግሥተ ሰማይ በማዕድ ይቀመጣሉ እላችኋለሁ። #13፥29። 12የዚህ መንግሥት ወራሾች መሆን ይገባቸው የነበሩት ግን ውጪ ወደ አለው ጨለማ ይጣላሉ። በዚያም ለቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል።” 13ከዚህ በኋላ፥ ኢየሱስ የመቶ አለቃውን “ሂድ፤ እንደ እምነትህ ይሁንልህ” አለው። አገልጋዩም በዚያኑ ሰዓት ተፈወሰ።
ኢየሱስ ብዙ ሕመምተኞችን መፈወሱ
(ማር. 1፥29-34ሉቃ. 4፥38-41)
14ከዚያ ኢየሱስ ወደ ጴጥሮስ ቤት በገባ ጊዜ የጴጥሮስ ዐማት አተኲሶአት ታማ እንደ ተኛች አየ። 15እጅዋንም በዳሰሳት ጊዜ፥ ወዲያው ትኩሳቱ ለቀቃትና ዳነች፤ ተነሥታም ኢየሱስን ታገለግል ጀመር። 16በመሸም ጊዜ ሰዎች በአጋንንት የተያዙ ብዙ በሽተኞችን ወደ ኢየሱስ አመጡ፤ እርሱም በቃሉ ርኩሳን መናፍስትን አስወጣ፤ በሽተኞችንም ሁሉ ፈወሰ። 17ይህንንም በማድረጉ በነቢዩ ኢሳይያስ፥ “እርሱ ደዌአችንን ተቀበለ፤ ሕመማችንንም ተሸከመ” የተባለው ትንቢት ተፈጸመ።
የኢየሱስ ተከታዮች የሚገጥማቸው ችግር
(ሉቃ. 9፥57-62)
18ኢየሱስ፥ ብዙ ሰዎች በዙሪያው ተሰብስበው ባየ ጊዜ ወደ ባሕሩ ማዶ እንዲሻገሩ ደቀ መዛሙርቱን አዘዘ። 19ከዚህ በኋላ አንድ የሕግ መምህር፥ ወደ ኢየሱስ መጥቶ፥ “መምህር ሆይ፥ ወደምትሄድበት ሁሉ ልከተልህ” አለው። 20ኢየሱስም “ቀበሮዎች ጒድጓድ አላቸው፤ በአየር ላይ የሚበሩ ወፎችም የሚሰፍሩበት ጎጆ አላቸው፤ የሰው ልጅ ግን ራሱን እንኳ የሚያሳርፍበት ስፍራ የለውም” ሲል መለሰለት። 21ከደቀ መዛሙርቱም አንዱ “ጌታ ሆይ መጀመሪያ ሄጄ አባቴን እንድቀብር ፍቀድልኝ” አለው። #8፥21 እንድቀብር፦ አባቱ እስኪሞት ድረስ ጦሮ ለመቅበር ያለውን ፍላጎት የሚያመለክት ይመስላል። 22ኢየሱስም “አንተ እኔን ተከተለኝ፤ ሙታንን ግን ሙታናቸውን እንዲቀብሩ ተዋቸው” አለው።
ኢየሱስ ማዕበሉን ጸጥ እንዳደረገ
(ማር. 4፥35-41ሉቃ. 8፥22-25)
23ኢየሱስም ወደ ጀልባ ሲገባ፥ ደቀ መዛሙርቱ ተከተሉት። 24ታላቅ ዐውሎ ነፋስ በባሕሩ ላይ ስለ ተነሣ ማዕበሉ ጀልባይቱን ሊያሰጥማት ደረሰ፤ ኢየሱስ ግን ተኝቶ ነበር። 25ደቀ መዛሙርቱም ወደ ኢየሱስ ቀርበው፥ “ጌታ ሆይ! ልንጠፋ ነው፤ አድነን!” ብለው ቀሰቀሱት።
26እርሱም “እናንተ እምነት የጐደላችሁ! ስለምን ትፈራላችሁ?” አላቸው። ከዚያም በኋላ ኢየሱስ ተነሥቶ ነፋሱንና ባሕሩን ገሠጸ፤ ታላቅ ጸጥታም ሆነ። 27ሰዎቹም ተደንቀው፥ “ነፋስና ባሕር እንኳ የሚታዘዙለት ይህ እንዴት ያለ ሰው ነው?” አሉ።
ኢየሱስ በአጋንንት የተያዙ ሁለት ሰዎችን እንደ ፈወሰ
(ማር. 5፥1-20ሉቃ. 8፥26-39)
28ኢየሱስ የገሊላን ባሕር ተሻግሮ፥ ወደ ጌርጌሴኖን አገር በመጣ ጊዜ፥ አጋንንት የያዛቸው ሁለት ሰዎች ከመቃብር ቦታ ወጥተው ተገናኙት፤ በጣምም አደገኞች ስለ ነበሩ ማንም ሰው በዚያ መንገድ ማለፍ አይችልም ነበር። 29እነርሱም “አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ሆይ፥ አንተ ከእኛ ጋር ምን ጉዳይ አለህ? ጊዜው ሳይደርስ ልታሠቃየን መጣህን?” እያሉ ጮኹ። #መሳ. 11፥12፤ 2ሳሙ. 16፥10። 30ከእነርሱ ጥቂት ራቅ ባለ ስፍራ የብዙ ዐሣማዎች መንጋ ተሰማርቶ ነበር። 31አጋንንቱም “የምታስወጣን ከሆነ፥ እባክህ ወደዚያ ወደ ዐሣማዎቹ መንጋ ስደደን!” ሲሉ ለመኑት። 32ኢየሱስም “ሂዱ!” አላቸው። ስለዚህም ከሰዎቹ ወጥተው ወደ ዐሣማዎቹ ሄዱና ገቡባቸው። ዐሣማዎቹም በሙሉ ከገደሉ አፋፍ ላይ እየተንደረደሩ ወርደው በባሕር ውስጥ ሰጥመው ሞቱ። 33የዐሣማዎቹም እረኞች ሸሽተው፥ ወደ ከተማ ገቡና ሁሉን ነገር አወሩ፤ አጋንንት በያዙአቸው ሰዎች የሆነውንም ነገር ተናገሩ። 34ከዚህ በኋላ የከተማው ሰዎች ሁሉ ኢየሱስን ለማየት ወጡ፤ ባዩትም ጊዜ ከአገራቸው ወጥቶ እንዲሄድላቸው ለመኑት።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in