YouVersion Logo
Search Icon

የማቴዎስ ወንጌል 7

7
በሌሎች ላይ መፍረድ የማይገባ መሆኑ
(ሉቃ. 6፥37-42)
1ቀጥሎም ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “በእናንተ ላይ እንዳይፈረድባችሁ፥ በማንም ላይ አትፍረዱ፤ 2በሌሎች ላይ በምትፈርዱበት ፍርድ፥ በእናንተም ላይ ይፈረድባችኋል፤ እንዲሁም በምትሰፍሩበት መስፈሪያ ይሰፈርባችኋል። #ማር. 4፥24። 3በአንተ ዐይን ያለውን ግንድ ሳታይ፥ ስለምን በወንድምህ ዐይን ውስጥ ያለውን ጒድፍ ትመለከታለህ? 4ደግሞስ በአንተ ዐይን ግንድ እያለ፥ ወንድምህን ‘እስቲ በዐይንህ ያለውን ጒድፍ ላውጣልህ’ እንዴት ትለዋለህ? 5አንተ ግብዝ! አስቀድመህ በአንተ ዐይን ያለውን ግንድ አውጣ፤ ከዚያም በኋላ፥ በወንድምህ ዐይን ውስጥ ያለውን ጒድፍ ለማውጣት አጥርተህ ታያለህ። 6የተቀደሰውን ነገር ለውሾች አትስጡ፤ ዕንቋችሁንም በዐሣማዎች ፊት አትጣሉ፤ ዐሣማዎቹ ዕንቋችሁን በእግራቸው ይረግጡታል፤ ውሾቹም ተመልሰው ይነክሱአችኋል።
የጸሎት ውጤት
(ሉቃ. 11፥9-13)
7“ለምኑ ይሰጣችኋል፤ ፈልጉ ታገኛላችሁ፤ በር አንኳኩ ይከፈትላችኋል፤ 8የሚለምን ሁሉ ይቀበላል፤ የሚፈልግም ያገኛል፤ በር ለሚያንኳኳም ይከፈትለታል። 9ከእናንተ መካከል ልጁ ዳቦ ቢለምነው፥ ድንጋይ የሚሰጠው ማነው? 10ዓሣ ቢለምነውስ፥ እባብ ይሰጠዋልን? 11እንግዲህ እናንተ ክፉዎች ሆናችሁ ሳለ፥ ለልጆቻችሁ መልካም ነገር መስጠትን ካወቃችሁ፤ ታዲያ፥ በሰማይ ያለው አባታችሁማ ለሚለምኑት እንዴት አብልጦ መልካም ነገርን አይሰጣቸውም! 12እንግዲህ ሰዎች ሊያደርጉላችሁ የምትፈልጉትን ሁሉ፥ እናንተም ለእነርሱ እንዲሁ አድርጉላቸው፤ የሕግና የነቢያት ትምህርትም የሚሉት ይህንኑ ነው። #ሉቃ. 6፥31።
ስለ ጠባብዋ በር
(ሉቃ. 13፥24)
13“በጠባብዋ በር ግቡ፤ ወደ ጥፋት የሚያስገባው በር ሰፊ፥ መንገዱም ትልቅ ነው። ወደዚያ የሚገቡትም ሰዎች ብዙዎች ናቸው። 14ወደ ሕይወት የሚያስገባው በር ግን ጠባብ ነው፤ መንገዱም አስቸጋሪ ነው፤ እርሱን የሚያገኙት ሰዎች ጥቂቶች ናቸው። #ኤር. 21፥8፤ ዘዳ. 30፥19።
ዛፍ በፍሬው ይታወቃል
(ሉቃ. 6፥43-44)
15“የበግ ለምድ ለብሰው ከሚመጡባችሁ፥ በውስጣቸው ግን እንደ ነጣቂ ተኲላዎች ከሆኑት ከሐሰተኞች ነቢያት ተጠንቀቁ፤ #ሕዝ. 22፥27። 16እነርሱንም የምታውቁአቸው በሥራቸው ፍሬ ነው። ከእሾኽ ቊጥቋጦ የወይን ፍሬ፥ ከኮሸሽላስ የበለስ ፍሬ ይለቀማልን? 17እንዲሁም መልካም ዛፍ ሁሉ መልካም ፍሬ ያፈራል፤ መጥፎ ዛፍ ግን መጥፎ ፍሬ ያፈራል። 18መልካም ዛፍ መጥፎ ፍሬ ማፍራት አይችልም፤ መጥፎ ዛፍም መልካም ፍሬ ማፍራት አይችልም። 19መልካም ፍሬ የማያፈራ ዛፍ ሁሉ፥ ተቈርጦ ወደ እሳት ይጣላል። #ማቴ. 3፥10፤ ሉቃ. 3፥9። #ማቴ. 12፥33። 20ስለዚህ፥ ሐሰተኞች ነቢያትን በሥራቸው ፍሬ ታውቁአቸዋላችሁ። 21‘ጌታ ሆይ! ጌታ ሆይ!’ የሚለኝ ሁሉ ወደ መንግሥተ ሰማይ አይገባም፤ ወደ መንግሥተ ሰማይ የሚገባው በሰማይ ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚፈጽም ነው። 22በፍርድ ቀን ብዙዎች፥ ‘ጌታ ሆይ! ጌታ ሆይ! በስምህ ትንቢት አልተናገርንምን? በስምህስ አጋንንትን አላወጣንምን? በስምህስ ብዙ ተአምራትን አላደረግንምን?’ ይሉኛል። 23እኔም በዚያ ቀን፥ ‘በጭራሽ አላውቃችሁም! እናንተ ክፉ አድራጊዎች ከእኔ ወዲያ ራቁ!’ እላቸዋለሁ። #መዝ. 6፥8።
በአለት ወይም በአሸዋ ላይ የተሠሩ ቤቶች ምሳሌ
(ሉቃ. 6፥47-49)
24“ይህን ቃሌን ሰምቶ በሥራ ላይ የሚያውለው ሁሉ፥ ቤቱን በድንጋይ መሠረት ላይ የሠራ ብልኅ ሰውን ይመስላል። 25ዝናብ ዘነበ፥ ጐርፍ ጐረፈ፥ ነፋስም ነፈሰና ያን ቤት ገፋው፤ ይሁን እንጂ፥ ቤቱ በድንጋይ መሠረት ላይ ስለ ተሠራ አልወደቀም። 26ይህን ቃሌን ሰምቶ በሥራ ላይ የማያውለው ግን፥ ቤቱን በአሸዋ ላይ የሠራ ሞኝ ሰውን ይመስላል። 27ዝናብ ዘነበ፥ ጐርፍም ጐረፈ፥ ነፋስም ነፈሰና ያንን ቤት ገፋው፤ ቤቱም ወዲያውኑ ወደቀ፤ አወዳደቁም ታላቅ ሆነ።” 28ኢየሱስ እነዚህን ነገሮች ተናግሮ ባበቃ ጊዜ ሕዝቡ በትምህርቱ ተደነቁ። 29የተደነቁትም እርሱ እንደ ሕግ መምህሮቻቸው ሳይሆን፥ እንደ ባለሥልጣን ያስተምራቸው ስለ ነበረ ነው። #ማር. 1፥22፤ ሉቃ. 4፥32፤ ማር. 1፥22፤ ሉቃ. 4፥32።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in