YouVersion Logo
Search Icon

የማቴዎስ ወንጌል 26

26
በኢየሱስ ላይ የተደረገ ሤራ
(ማር. 14፥1-2ሉቃ. 22፥1-2ዮሐ. 11፥45-53)
1ኢየሱስ ይህን ሁሉ ትምህርት አስተምሮ ባበቃ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱን እንዲህ አላቸው፤ 2“ከሁለት ቀን በኋላ የፋሲካ በዓል እንደሚሆን ታውቃላችሁ፤ የሰው ልጅ ለመሰቀል ተላልፎ ይሰጣል።” #ዘፀ. 12፥1-27።
3በዚያን ጊዜ የካህናት አለቆችና የሕዝብ ሽማግሌዎች በካህናት አለቃው ግቢ ተሰበሰቡ። 4እዚያም ኢየሱስን በተንኰል ለመያዝና ለመግደል አሤሩ። 5ነገር ግን “በሕዝቡ መካከል ሁከት እንዳይነሣ በበዓል ቀን አይሁን” አሉ።
አንዲት ሴት ኢየሱስን ሽቶ እንደ ቀባችው
(ማር. 14፥3-9ዮሐ. 12፥1-8)
6እነሆ፥ ኢየሱስ በቢታንያ ለምጻም በነበረው በስምዖን ቤት ነበረ። 7በዚያም ኢየሱስ በማእድ ተቀምጦ ሳለ አንዲት ሴት ዋጋው እጅግ ውድ የሆነ ሽቶ የሞላበት የአልባስጥሮስ ብልቃጥ ይዛ ወደ እርሱ ቀረበች፤ ሽቶውንም በራሱ ላይ አፈሰሰችው። #ሉቃ. 7፥37-38። #26፥7 አልባስጥሮስ፦ የክብር ዕቃ የሚሠራበት ነጭ የማዕድን ድንጋይ ነው። 8ደቀ መዛሙርቱ ይህን አይተው ተቈጡና እንዲህ አሉ፦ “ይህ ሽቶ ለምን በከንቱ ባከነ? 9ይህ ሽቶ በብዙ ዋጋ ተሸጦ ለድኾች ሊሰጥ ይችል ነበር!” 10ኢየሱስም ይህን ማለታቸውን ዐውቆ እንዲህ አላቸው፤ “ይህችን ሴት ለምን ታስቸግሩአታላችሁ? እርስዋ ለእኔ መልካም ነገር አድርጋለች፤ 11ድኾች ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ናቸው፤ እኔ ግን ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር እዚህ አልገኝም። #ዘዳ. 15፥11። 12እርስዋ ይህን ሽቶ በእኔ ላይ ማፍሰስዋ እኔን ለቀብር ለማዘጋጀት ነው። 13በእውነት እላችኋለሁ በዓለም ሁሉ ይህ ወንጌል በሚሰበክበት በማናቸውም ስፍራ ይህ እርስዋ ያደረገችው ለመታሰቢያዋ ይነገርላታል።”
ይሁዳ ኢየሱስን አሳልፎ ለመስጠት መስማማቱ
(ማር. 14፥10-11ሉቃ. 22፥3-6)
14በዚያን ጊዜ ከዐሥራ ሁለቱ ሐዋርያት አንዱ የሆነው አስቀሮታዊው ይሁዳ ወደ ካህናት አለቆች ሄደና 15“ኢየሱስን አሳልፌ ብሰጣችሁ ምን ትሰጡኛላችሁ?” አለ። እነርሱም ሠላሳ ጥሬ ብር ሰጡት #ዘካ. 11፥12። #26፥15 ጥሬ ብር፦ ሌላ ምንም ያልተጨመረበት የተጣራ ብር ማለት ነው። 16እርሱም ከዚያች ሰዓት ጀምሮ ኢየሱስን አሳልፎ የሚሰጥበትን ምቹ ጊዜ ይፈልግ ነበር።
ኢየሱስ የአይሁድን የፋሲካ ራት ከሐዋርያቱ ጋር እንደ በላ
(ማር. 14፥12-21፤ ሉቃ. 22፥7—14፥21-23፤ ዮሐ. 13፥21-30)
17በቂጣ በዓል መጀመሪያ ቀን ደቀ መዛሙርቱ ወደ ኢየሱስ ቀርበው “የፋሲካ በዓልን ራት የት እንድናዘጋጅልህ ትፈልጋለህ?” ሲሉ ጠየቁት። 18እርሱም “ወደ ከተማው ስትገቡ ወደምታገኙት ሰው ቤት ሂዱና ‘መምህር ጊዜዬ ቀርቦአልና ከደቀ መዛሙርቴ ጋር የፋሲካን በዓል ራት የምበላው በአንተ ቤት ነው ይላል’ በሉት” አለ። 19ደቀ መዛሙርቱም ኢየሱስ እንዳዘዛቸው አደረጉ፤ የፋሲካውንም ራት አዘጋጁ። 20በመሸም ጊዜ ኢየሱስ ከዓሥራ ሁለቱ ሐዋርያት ጋር በማእድ ተቀመጠ። 21ሲበሉም ኢየሱስ፦ “በእውነት እላችኋለሁ፤ ከእናንተ አንዱ እኔን አሳልፎ ይሰጣል” አለ። 22ደቀ መዛሙርቱም በዚህ ነገር በጣም አዝነው፥ እያንዳንዳቸው ጌታ ሆይ፥ “እኔ እሆን?” እያሉ ይጠይቁት ጀመር። 23ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “እኔን አሳልፎ የሚሰጥ ከእኔ ጋር በሳሕኑ ውስጥ የሚያጠቅሰው ነው። #መዝ. 41፥9። 24የሰው ልጅ ስለ እርሱ በተጻፈው መሠረት ይሞታል፤ ነገር ግን የሰው ልጅን አሳልፎ ለሚሰጥ ለዚያ ሰው ወዮለት! ያ ሰው ባልተወለደ ይሻለው ነበር።” 25አሳልፎ የሚሰጠው ይሁዳም፥ “መምህር ሆይ! እኔ እሆን?” አለ። ኢየሱስም፥ “አንተ እንዳልከው ነው” አለው።
የቅዱስ ቊርባን ሥርዓት
(ማር. 14፥22-26ሉቃ. 22፥15-231ቆሮ. 11፥23-25)
26ሲበሉም ኢየሱስ ኅብስት አንሥቶ ባረከ ቈርሶም ለደቀ መዛሙርቱ “እንካችሁ ብሉ ይህ ሥጋዬ ነው” ብሎ ሰጣቸው። 27ጽዋውንም አንሥቶ የምስጋና ጸሎት ካደረገ በኋላ እንዲህ ሲል ሰጣቸው፤ “ሁላችሁም ከዚህ ጽዋ ጠጡ፤ 28ይህ ስለ ብዙዎች ለኃጢአት ይቅርታ የሚፈስ የአዲስ ኪዳን ደሜ ነው፤ #ዘፀ. 24፥8፤ ኤር. 31፥31-34። 29በአባቴ መንግሥት አዲሱን የወይን ፍሬ ጭማቂ ከእናንተ ጋር እስከምጠጣበት ቀን ድረስ ከእንግዲህ ወዲህ ከዚህ የወይን ፍሬ ጭማቂ ዳግመኛ አልጠጣም እላችኋለሁ፤” 30ከዚህ በኋላ መዝሙር ዘምረው ወደ ደብረ ዘይት ተራራ ወጡ።
ጴጥሮስ እንደሚክደው ኢየሱስ አስቀድሞ እንደ ተናገረ
(ማር. 14፥27-31ሉቃ. 22፥31-34ዮሐ. 13፥36-38)
31በዚያን ጊዜ ኢየሱስ፥ ደቀ መዛሙርቱን እንዲህ አላቸው፤ “ ‘እረኛውን እመታለሁ፤ የመንጋውም በጎች ይበተናሉ’ ተብሎ ተጽፎአልና በዚህች ሌሊት፥ ሁላችሁም ትክዱኛላችሁ። #ዘካ. 13፥7። 32ነገር ግን ከሞት ከተነሣሁ በኋላ ወደ ገሊላ ቀድሜአችሁ እሄዳለሁ።” #ማቴ. 28፥16።
33በዚያን ጊዜ ጴጥሮስ፥ “ሌሎቹ ሁሉ እንኳ ቢክዱህ እኔ ከቶ አልክድህም!” ብሎ ተናገረ። 34ኢየሱስም “በእውነት እልሃለሁ፤ ዛሬ በዚህች ሌሊት ዶሮ ከመጮሁ በፊት አንተ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ” አለው። 35ጴጥሮስ ግን “ከአንተ ጋር መሞት እንኳ የሚያስፈልግ ቢሆን እሞታለሁ እንጂ ከቶ አልክድህም!” አለው። የቀሩትም ደቀ መዛሙርት ሁሉ እንዲሁ ይሉ ነበር።
ኢየሱስ በጌቴሴማኒ እንደ ጸለየ
(ማር. 14፥32-42ሉቃ. 22፥39-46)
36ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ጌቴሴማኒ ወደሚባል ስፍራ ሄደ፤ እዚያም እንደ ደረሱ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን፦ “እኔ እዚያ ሄጄ እስክጸልይ እናንተ እዚህ ቈዩ” አላቸው። 37ከእርሱ ጋር ጴጥሮስንና ሁለቱን የዘብዴዎስን ልጆች አስከትሎ ሄደ፤ ያዝንና ይጨነቅም ጀመረ። 38እንዲህም አላቸው፦ “ለመሞት እስክደርስ ድረስ አዝኛለሁ፤ እናንተ እዚህ ቈዩ፤ ከእኔም ጋር ንቁ።” 39ከእነርሱ ጥቂት ራቅ ብሎ ሄደና፥ በመሬት ላይ በግንባሩ ተደፍቶ፥ እንዲህ ሲል ጸለየ፤ “አባት ሆይ! የሚቻል ከሆነ ይህ የመከራ ጽዋ ከእኔ ወዲያ ይለፍ! ነገር ግን የአንተ ፈቃድ ይሁን እንጂ የእኔ ፈቃድ አይሁን።”
40ከዚህ በኋላ ወደ ሦስቱ ደቀ መዛሙርት ተመልሶ በመጣ ጊዜ ተኝተው አገኛቸው፤ ስለዚህ፥ ጴጥሮስን እንዲህ አለው፦ “ከእኔ ጋር ለአንዲት ሰዓት እንኳ መንቃት አልቻላችሁምን? 41ወደ ፈተና እንዳትገቡ ተግታችሁ ጸልዩ፤ መንፈስ በእርግጥ ዝግጁ ነው፤ ሥጋ ግን ደካማ ነው።”
42እንደገናም ኢየሱስ ለሁለተኛ ጊዜ ርቆ ሄደና “አባቴ ሆይ! ይህ የመከራ ጽዋ ሳልጠጣው ሊያልፍ የማይቻል ከሆነ የአንተ ፈቃድ ይሁን” ሲል ጸለየ። 43ደግሞም ወደ ደቀ መዛሙርቱ ተመልሶ በመጣ ጊዜ ዐይኖቻቸው በእንቅልፍ ከብደው ነበርና ተኝተው አገኛቸው። 44እንደገናም ትቶአቸው ሄደና ያንኑ የፊተኛውን ቃል በመናገር ሦስተኛ ጊዜ ጸለየ። 45ከዚህ በኋላ ወደ ደቀ መዛሙርቱ ተመልሶ መጣና እንዲህ አላቸው፤ “አሁንም ገና ተኝታችኋልን? ዕረፍትም እያደረጋችሁ ነውን? እነሆ፥ የሰው ልጅ በኃጢአተኞች እጅ ተላልፎ የሚሰጥበት ሰዓቱ ደርሶአል፤ 46ተነሡ እንሂድ! እነሆ፥ አሳልፎ የሚሰጠኝ ቀርቦአል!”
የኢየሱስ ተላልፎ መሰጠትና መያዝ
(ማር. 14፥43-50ሉቃ. 22፥47-53ዮሐ. 18፥3-12)
47ኢየሱስ ገና ሲናገር ሳለ እነሆ፥ ከዐሥራ ሁለቱ ደቀ መዛሙርት አንዱ የሆነው ይሁዳ መጣ፤ ከእርሱም ጋር ሰይፍና ዱላ የያዙ ብዙ ሰዎች መጡ፤ እነርሱ ከካህናት አለቆችና ከሕዝብ ሽማግሌዎች የተላኩ ነበሩ። 48ኢየሱስን አሳልፎ የሚሰጠው ይሁዳ ለሰዎቹ “የምትፈልጉት እኔ የምስመው ነውና እርሱን ያዙት” ሲል ምልክት ሰጥቶአቸው ነበር።
49ይሁዳ ወዲያውኑ መጥቶ ወደ ኢየሱስ ቀረበና “መምህር ሆይ! ሰላም ለአንተ ይሁን!” ብሎ ሳመው። 50ኢየሱስም “ወዳጄ ሆይ! እንግዲህ የመጣህበትን ጉዳይ ፈጽም” አለው፤ ከዚህ በኋላ ሰዎቹ ወደ ኢየሱስ ቀረቡና ያዙት። 51በዚህ ጊዜ ከኢየሱስ ጋር ከነበሩት አንዱ እጁን ዘርግቶ ሰይፉን መዘዘና የካህናት አለቃውን አገልጋይ መትቶ ጆሮውን ቈረጠው። 52ኢየሱስ ግን እንዲህ አለ፤ “ሰይፍን የሚያነሡ በሰይፍ ይጠፋሉና ሰይፍህን ወደ ሰገባው መልሰህ ክተተው። 53ለመሆኑ እኔ አባቴን ብለምን እርሱ በብዙ ሺህ የሚቈጠሩ የመላእክት ሠራዊት ሊልክልኝ የማይችል ይመስልሃልን? 54እንዲህማ ቢሆን ኖሮ ‘መከራ መቀበል አለበት’ የሚለው የቅዱሳት መጻሕፍት ቃል እንዴት ይፈጸማል?”
55በዚያን ሰዓት ኢየሱስ በዚያ ለተሰበሰቡት ሕዝብ እንዲህ አለ፤ “ወንበዴን እንደምትይዙ እኔን ለመያዝ ሰይፍና ዱላ ይዛችሁ መጣችሁን? በየቀኑ በቤተ መቅደስ እያስተማርኩ ከእናንተ ጋር ሳለሁ አልያዛችሁኝም ነበር፤ #ሉቃ. 19፥47፤ 21፥37። 56ነገር ግን ይህ ሁሉ የሆነው በነቢያት የተጻፈው እንዲፈጸም ነው።” በዚያን ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ሁሉ ትተውት ሸሹ።
ኢየሱስ ወደ ፍርድ ሸንጎ መወሰዱ
(ማር. 14፥53-65ሉቃ. 22፥54-55፤ ዮሐ. 18፥13—14፥19-24)
57ከዚህ በኋላ ኢየሱስን የያዙት ሰዎች ወደ ካህናት አለቃው ወደ ቀያፋ ወሰዱት፤ በዚያም የሕግ መምህራንና ሽማግሌዎች ተሰብስበው ነበር። 58ጴጥሮስ ግን እስከ ካህናት አለቃው ግቢ ድረስ ኢየሱስን በሩቅ ተከተለው፤ ወደ ውስጥ ገብቶም የነገሩን ፍጻሜ ለማየት ከዘበኞች ጋር ተቀመጠ። 59የካህናት አለቆችና የአይሁድ ሸንጎ አባሎች ሁሉ በኢየሱስ ላይ የሞት ፍርድ ለማስፈረድ የሐሰት ምስክር ይፈልጉ ነበር። 60ብዙ የሐሰት ምስክሮች ቢቀርቡም፥ ሞት የሚያስፈርድበት ምስክርነት አላገኙም፤ በመጨረሻ ሁለት ምስክሮች ቀርበው፥ 61“ይህ ሰው ‘የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ አፍርሼ በሦስት ቀን ልሠራው እችላለሁ’ ብሎአል” ሲሉ ተናገሩ። #ዮሐ. 2፥19።
62የካህናት አለቃውም ተነሣና “እነዚህ ሰዎች ለሚመሰክሩብህ ሁሉ ምንም መልስ አትሰጥምን?” ሲል ጠየቀው። 63ኢየሱስ ግን ዝም አለ። የካህናት አለቃውም እንደገና ኢየሱስን “በሕያው እግዚአብሔር ስም ይዤሃለሁ! አንተ የእግዚአብሔር ልጅ መሲሕ እንደ ሆንክ ንገረን!” አለው። 64ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “አንተ እንዳልከው ነው፤ ነገር ግን ከእንግዲህ ወዲህ የሰው ልጅ በኀያሉ እግዚአብሔር ቀኝ ተቀምጦ ታዩታላችሁ፤ እንዲሁም በሰማይ ደመና ሆኖ ሲመጣ ታዩታላችሁ እላችኋለሁ።” #ዳን. 7፥13። 65በዚህ ጊዜ የካህናት አለቃው በብስጭት ልብሱን ቀደደና እንዲህ አለ፤ “እነሆ፥ በእግዚአብሔር ላይ የስድብ ቃል ተናግሮአል! እናንተም ስድቡን ሰምታችኋል! ከዚህ የበለጠ ምን ምስክር ያስፈልጋል! 66ታዲያ፥ ምን ይመስላችኋል?” እነርሱም “ሞት ይገባዋል!” ሲሉ መለሱ። #ዘሌ. 24፥16።
67በዚያን ጊዜ ምራቃቸውን ተፉበት፤ ጎሸሙት፤ በጥፊም እየመቱት፥ 68“መሲሕ ሆይ! ማን ነው የመታህ? እስቲ ትንቢት ተናገር” ይሉት ነበር።
ጴጥሮስ ኢየሱስን እንደ ካደ
(ማር. 14፥66-72ሉቃ. 22፥56-62ዮሐ. 18፥15—18፥25-27)
69ጴጥሮስ ከቤት ውጪ በሊቀ ካህናቱ ግቢ ውስጥ ተቀምጦ ነበር፤ በዚያን ጊዜ አንዲት ገረድ ወደ እርሱ ቀርባ “አንተም ከገሊላዊው ኢየሱስ ጋር ነበርክ!” አለችው። 70እርሱ ግን “የምትዪውን አላውቅም!” ሲል በሁሉም ፊት ካደ። 71ሊወጣ ወደ በሩ ሲሄድ አንዲት ሌላ ገረድ አየችውና እዚያ ለነበሩት ሰዎች “ይህ ሰው ከናዝሬቱ ኢየሱስ ጋር ነበር!” አለች። 72ጴጥሮስም “ይህን የምትዪውን ሰው አላውቀውም!” ሲል በመማል እንደገና ካደ። 73ከጥቂት ጊዜ በኋላ እዚያ ቆመው የነበሩ ሰዎች ወደ ጴጥሮስ ጠጋ ብለው፦ “አነጋገርህ ያስታውቃል፤ በእርግጥ አንተም ከእነርሱ አንዱ ነህ” አሉት። 74በዚያን ጊዜ ጴጥሮስ፦ “እኔ ይህን ሰው አላውቀውም!” እያለ ራሱን መራገምና መማል ጀመረ። ወዲያውኑ ዶሮ ጮኸ።
75ጴጥሮስም “ዶሮ ሳይጮህ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ” ብሎ ኢየሱስ የተናገረው ቃል ትዝ አለው። ወደ ውጭም ወጣና ምርር ብሎ አለቀሰ።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in