YouVersion Logo
Search Icon

የማቴዎስ ወንጌል 15

15
ስለ አባቶች ወግ
(ማር. 7፥1-13)
1ከዚህ በኋላ፥ ከኢየሩሳሌም የመጡ ፈሪሳውያንና የሕግ መምህራን ወደ ኢየሱስ ቀርበው እንዲህ ሲሉ ጠየቁት፦ 2“ደቀ መዛሙርትህ የሽማግሌዎችን ወግ ስለምን ያፈርሳሉ? እነሆ! ምግብ የሚበሉት እጃቸውን ሳይታጠቡ ነው!”
3ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “እናንተስ ወጋችሁን ለመጠበቅ ብላችሁ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ስለምን ታፈርሳላችሁ? 4እግዚአብሔር ‘አባትህንና እናትህን አክብር፤ በአባቱ ወይም በእናቱ ላይ የስድብ ቃል የተናገረ በሞት ይቀጣል’ ብሎ አዞአል። #ዘፀ. 20፥12፤ 21፥17፤ ዘዳ. 5፥16፤ ዘሌ. 20፥9። 5እናንተ ግን አንድ ሰው አባቱን ወይም እናቱን ‘ከእኔ የምታገኙትን ርዳታ ለእግዚአብሔር መባ አድርጌ አቅርቤአለሁ’ ቢላቸው፥ 6‘ያ ሰው አባቱን [ወይም እናቱን] ማክበር አያስፈልገውም’ ትላላችሁ፤ ስለዚህ ወጋችሁን ለማጥበቅ ብላችሁ የእግዚአብሔርን ሕግ ታፈርሳላችሁ፤ #15፥6 አባቱን፦ አንዳንድ የብራና ጽሑፎች “አባቱን ወይም እናቱን” ይላሉ። 7እናንተ ግብዞች! ኢሳይያስ ስለ እናንተ እንዲህ ሲል የተናገረው ትንቢት ልክ ነው፤
8‘ይህ ሕዝብ በአፉ ያከብረኛል፤
ልቡ ግን ከእኔ የራቀ ነው፤
9ሰው ሠራሽ ወግና ሥርዓትን፥
እንደ ሕግ አድርጎ እያስተማረ በከንቱ ያመልከኛል።’ ” #ኢሳ. 29፥13።
ሰውን የሚያረክስ ነገር
(ማር. 7፥14-23)
10ቀጥሎም ኢየሱስ ሰዎቹን ወደ እርሱ ጠርቶ እንዲህ አላቸው፦ “ስሙ! አስተውሉም! 11ሰውን የሚያረክሰው ከአፍ የሚወጣው ነው እንጂ ወደ አፍ የሚገባው አይደለም!”
12ከዚህ በኋላ ደቀ መዛሙርቱ ወደ እርሱ ቀርበው፦ “ፈሪሳውያን ይህን የተናገርከውን ሰምተው እንደ ተሰናከሉ ዐውቀሃልን?” ሲሉ ጠየቁት። 13እርሱ ግን እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “የሰማዩ አባቴ ያልተከለው ተክል ሁሉ ይነቀላል፤ 14እነርሱ ዕውሮችና ዕውሮችን የሚመሩ ስለ ሆኑ ተዉአቸው፤ ዕውር ዕውርን ቢመራ ሁለቱም በጒድጓድ ውስጥ ይወድቃሉ።” #ሉቃ. 6፥39።
15ጴጥሮስ ግን ኢየሱስን “የምሳሌውን ትርጒም አስረዳን” አለው። 16ኢየሱስም እንዲህ አለ፦ “እናንተም እስከ አሁን ገና የማታስተውሉ ናችሁን? 17ወደ አፍ የሚገባ ሁሉ ወደ ሆድ ወርዶ ወደ ውጪ እንደሚወጣ አታስተውሉምን? 18ከአፍ የሚወጣው ግን ከልብ ይወጣል፤ ሰውን የሚያረክሰውም እርሱ ነው። #ማቴ. 12፥34። 19ክፉ ማሰብ፥ ሰው መግደል፥ ማመንዘር፥ ዝሙት ማድረግ፥ መስረቅ፥ በሐሰት መመስከር የሰውን ስም ማጥፋት፥ ይህ ሁሉ ከሰው ልብ ይወጣል። 20ሰውን የሚያረክሱ እነዚህ ናቸው እንጂ ባልታጠበ እጅ መብላትስ አያረክሰውም።”
የአንዲት ሴት እምነት
(ማር. 7፥24-30)
21ኢየሱስ ከዚያ ወጥቶ ወደ ጢሮስና ወደ ሲዶና ከተሞች ሄደ፤ 22ከዚያም አንዲት ከነዓናዊት ሴት ወደ ኢየሱስ መጥታ፥ “የዳዊት ልጅ ጌታ ሆይ! ልጄ በርኩስ መንፈስ ተይዛ ትሠቃያለችና እባክህ ራራልኝ!” እያለች ጮኸች።
23እርሱ ግን አንድም ቃል ሳይመልስላት ዝም አለ፤ በዚያን ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ወደ እርሱ ቀርበው፥ “ይህች ሴት እየተከተለችን ስለምትጮኽ እባክህ አሰናብታት!” ሲሉ ለመኑት። 24እርሱም “እኔ የተላክሁት ከእስራኤል ቤት እንደ በጎች ለጠፉት ብቻ ነው” ሲል መለሰ።
25ሴትዮዋ ግን ቀርባ በእግሩ ሥር ተንበረከከችና “ጌታ ሆይ! እባክህ እርዳኝ!” አለችው።
26ኢየሱስም “የልጆችን እንጀራ ወስዶ ለውሾች መጣል የተገባ አይደለም” አለ።
27እርስዋም “ጌታ ሆይ! እርግጥ ነው፤ ነገር ግን ውሾችም ከጌቶቻቸው ማእድ የሚወድቀውን ፍርፋሪ ይበላሉ” አለች።
28በዚያን ጊዜ ኢየሱስ “አንቺ ሴት እምነትሽ! ትልቅ ነው፤ ስለዚህ እንደ ፍላጎትሽ ይሁንልሽ!” አላት። የሴትዮዋም ልጅ በዚያኑ ሰዓት ዳነች።
ኢየሱስ ብዙ ሕመምተኞችን መፈወሱ
29ኢየሱስ ከዚያ ተነሥቶ ወደ ገሊላ ባሕር አጠገብ መጣ፤ ወደ ተራራ ላይም ወጥቶ እዚያ ተቀመጠ። 30ብዙ ሰዎች አንካሶችን፥ ዕውሮችን፥ ሽባዎችን፥ ድዳዎችንና ሌሎችንም በሽተኞች ይዘው ወደ ኢየሱስ መጡ፤ በእግሩም ሥር አስቀመጡአቸው፤ እርሱም ፈወሳቸው። 31ስለዚህ ሕዝቡ ድዳዎች ሲናገሩ፥ ሽባዎች ሲድኑ፥ አንካሳዎች በደኅና ሲራመዱ፥ ዕውሮች ሲያዩ በተመለከቱ ጊዜ ተደንቀው የእስራኤልን አምላክ አመሰገኑ።
ኢየሱስ አራት ሺ ሰዎችን መመገቡ
(ማር. 8፥1-10)
32ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ጠርቶ፥ እንዲህ አላቸው፦ “ሰዎቹ ከእኔ ጋር ሦስት ቀናቸው ስለ ሆነና የሚበሉት ስለሌላቸው እራራላቸዋለሁ፤ ሲሄዱ በመንገድ ዝለው እንዳይወድቁ ምንም ሳይመገቡ ላሰናብታቸው አልፈቅድም።”
33ደቀ መዛሙርቱም “ታዲያ፥ ለዚህ ሁሉ ሰው የሚበቃ ምግብ በዚህ በረሓ ከየት እናገኛለን?” አሉት። 34ኢየሱስም “ስንት እንጀራ አላችሁ?” ሲል ጠየቃቸው። እነርሱም “ሰባት እንጀራና ጥቂት ትናንሽ ዓሣዎች አሉን” አሉት።
35ከዚያ በኋላ፥ ኢየሱስ ሕዝቡ በመሬት ላይ እንዲቀመጡ አዘዘ፤ 36ሰባቱን እንጀራና ዓሣውንም አንሥቶ የምስጋና ጸሎት አደረገ፤ ቈርሶም ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠ፤ ደቀ መዛሙርቱም ለሕዝቡ ዐደሉ። 37ሁሉም በልተው ጠገቡ፤ የተረፈውንም ደቀ መዛሙርቱ ሰብስበው ሰባት መሶብ ሙሉ ፍርፋሪ አነሡ። 38የበሉትም ሰዎች ሴቶችና ሕፃናት ሳይቈጠሩ አራት ሺህ ወንዶች ነበሩ።
39ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ሕዝቡን አሰናበተ፤ በጀልባም ተሳፍሮ ወደ መጌዶን ክፍለ ሀገር ሄደ።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in