የዮሐንስ ወንጌል 7
7
ወደ ገሊላ ስለ መሄዱ
1ከዚህ በኋላም ጌታችን ኢየሱስ በገሊላ ይመላለስ ነበረ፤ ወደ ይሁዳ ምድርም ሊሄድ አልወደደም፤ አይሁድ ሊገድሉት ይሹ ነበርና። 2#ዘሌ. 23፥34፤ ዘዳ. 16፥13። የአይሁድም የዳስ በዓላቸው ደርሶ ነበር። 3ወንድሞቹም ጌታችን ኢየሱስን እንዲህ አሉት- “ደቀ መዛሙርትህ የምትሠራውን ሥራህን እንዲያዩ ከዚህ ወጥተህ ወደ ይሁዳ ሀገር ሂድ። 4ሊገለጥ ወድዶ ሳለ በስውር አንዳች ነገር የሚያደርግ ማንም የለምና፤ አንተ ግን ይህን የምታደርግ ከሆነ ራስህን ለዓለም ግለጥ። 5ወንድሞቹ ገና አላመኑበትም ነበርና። 6ጌታችን ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፥ “ጊዜዬ ገና አልደረሰም፤ የእናንተ ጊዜ ግን ዘወትር የተዘጋጀ ነው። 7ዓለም እናንተን ሊጠላችሁ አይችልም፤ እኔን ግን ይጠላኛል፤ ሥራዉ ክፉ እንደ ሆነ እኔ እመሰክርበታለሁና። 8እናንተም ወደዚህ በዓል ውጡ፤ እኔ አሁን ወደዚህ በዓል አልወጣም፤ ጊዜዬ ገና አልደረሰምና።” 9እርሱም እንዲህ ብሎአቸው በገሊላ ቀረ።
ወደ በዓል ስለ መውጣቱ
10ወንድሞቹ ለበዓል ከወጡ በኋላ፥ እርሱም ያንጊዜ በግልጥ ሳይሆን ተሰውሮ ወጣ። 11አይሁድም፥ “ያ ወዴት ነው?” እያሉ በበዓሉ ይፈልጉት ጀመር። 12ሕዝቡም ስለ እርሱ ብዙ አንጐራጐሩ፥ “ደግ ሰው ነው” ያሉ ነበሩ፤ ሌሎች ግን፥ “አይደለም፤ ሕዝቡን ያስታል እንጂ” አሉ። 13ነገር ግን፥ አይሁድን በመፍራት የእርሱን ነገር ገልጦ የተናገረ አልነበረም።
በበዓሉ ላይ ስለ ማስተማሩ
14በበዓሉ ቀኖች እኩሌታም ጌታችን ኢየሱስ ወደ መቅደስ ወጥቶ ያስተምር ጀመረ። 15አይሁድም፥ “ይህ ሳይማር መጽሐፍን እንዴት ያውቃል?” እያሉ ትምህርቱን#“ትምህርቱን” የሚለው በግሪኩ የለም። አደነቁ። 16ስለዚህም ጌታችን ኢየሱስ መልሶ እንዲህ አላቸው፥ “ትምህርቴ የላከኝ ናት እንጂ የእኔ አይደለችም። 17ፈቃዱን ሊያደርግ የሚወድድ ግን ትምህርቴ ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደ ሆነች፥ የምናገረውም ከራሴ እንዳይደለ እርሱ ያውቃል። 18ከራሱ የሚናገር የራሱን ክብር ይሻል፤ የላከውን ያከብር ዘንድ የሚፈልግ ግን እውነተኛ ነው፤ ሐሰትም የለበትም። 19ሙሴ ኦሪትን ሰጥቶአችሁ የለምን? ከእናንተ አንዱ ስንኳ ኦሪትን የሚያደርግ የለም፤ እንግዲህ ልትገድሉኝ ለምን ትሻላችሁ?” 20ሕዝቡም፥ “ጋኔን አለብህን? ማን ሊገድልህ ይሻል?” ብለው መለሱለት። 21ጌታችን ኢየሱስም መልሶ አላቸው፥ “አንድ ሥራ ሠራሁ፤ ሁላችሁም አደነቃችሁ። 22#ዘፍ. 17፥10፤ ዘሌ. 12፥3። ስለዚህ ሙሴ ግዝረትን ሰጥቶአችሁ ነበር፤ ነገር ግን ከአባቶች ናት እንጂ ከሙሴ አይደለችም፤ በሰንበትም ሰውን ትገዝሩታላችሁ። 23#ዮሐ. 5፥9። የሙሴ ሕግ እንዳይሻር ሰው በሰንበት የሚገዘር ከሆነ እንግዲያ ሰውን ሁለንተናውን በሰንበት ባድነው ለምን ትነቅፉኛላችሁ? 24የእውነት ፍርድ ፍረዱ እንጂ ለሰው ፊት በማድላት አትፍረዱ።”
ስለ ሕዝቡ ዋይታ
25ከኢየሩሳሌም ሰዎችም እንዲህ የሚሉ ነበሩ፥ “ይህ አይሁድ ሊገድሉት የሚሹት አይደለምን? 26እነሆ፥ እርሱ በገሀድ ይናገራል፤ እነርሱ ግን ምንም የሚሉት የለም፤ ይህ በእውነት ክርስቶስ እንደ ሆነ ምናልባት አለቆች ዐውቀው ይሆን? 27ነገር ግን ይህን ከየት እንደ ሆነ እናውቃለን፤ ክርስቶስ በሚመጣበት ጊዜስ ከወዴት እንደ ሆነ ማንም አያውቅም”። 28ጌታችን ኢየሱስም በመቅደስ ሲያስተምር ቃሉን ከፍ አድርጎ እንዲህ አለ፥ “እኔን ታውቁኛላችሁ፤ ከወዴትም እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ፤ እኔ ራሴ የመጣሁ አይደለሁም፤ ነገር ግን እናንተ የማታውቁት የላከኝ እውነተኛ አለ። 29እኔ ግን አውቀዋለሁ፤ እኔ ከእርሱ ነኝና፥ እርሱም ልኮኛልና። 30ስለዚህም ሊይዙት ወደው ነበር፤ ነገር ግን እጁን በእርሱ ላይ ያነሣ የለም፤ ጊዜዉ ገና አልደረሰም ነበርና። 31ከሕዝቡም ብዙዎች አመኑበትና፥ “በውኑ ክርስቶስ በሚመጣበት ጊዜ ይህ ሰው ካደረገው ተአምራት የሚበልጥ ያደርጋልን?” አሉ።
ፈሪሳውያን ሊይዙት ሎሌዎችን እንደ ላኩ
32ፈሪሳውያንም ሕዝቡ በእርሱ ምክንያት እንደ አጕረመረሙ ሰሙ፤ የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያንም ይይዙት ዘንድ ሎሌዎቻቸውን ላኩ። 33ጌታችን ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፥ “ጥቂት ቀን አብሬአችሁ እኖራለሁ፤ ከዚህም በኋላ ወደ ላከኝ እሄዳለሁ። 34ትሹኛላችሁ፤ አታገኙኝምም፤ እኔ ወደምሄድበትም እናንተ መምጣት አትችሉም።” 35አይሁድም እርስ በርሳቸው እንዲህ አሉ፥ “እኛ ልናገኘው የማንችል ይህ ወዴት ይሄዳል? ወይስ የግሪክን ሰዎች ለማስተማር በግሪክ ሀገር ወደ ተበተኑት ይሄዳልን? 36‘ትሹኛላችሁ፤ አታገኙኝምም፤ እኔ ወደምሄድበት እናንተ መምጣት አትችሉም’ የሚለን ይህ ነገር ምንድን ነው?”
ስለ መንፈስ ቅዱስ
37 #
ዘሌ. 23፥36። በኋለኛዪቱ በታላቅዋ የበዓል ቀንም ጌታችን ኢየሱስ ቆመና ድምፁን ከፍ አድርጎ እንዲህ አለ፥ “የተጠማ ወደ እኔ ይምጣና ይጠጣ። 38#ሕዝ. 47፥1፤ ዘካ. 14፥8። በእኔም የሚያምን መጽሐፍ እንደ ተናገረ የሕይወት ውኃ ወንዝ ከሆዱ ይፈስሳል።” 39ይህንም የሚያምኑበት ሰዎች ይቀበሉት ዘንድ ስለ አላቸው ስለ መንፈስ ቅዱስ ተናገረ፤ ጌታችን ኢየሱስ ገና ስላልከበረ መንፈስ ቅዱስ ገና አልወረደም ነበርና።
በአይሁድ መካከል ስለ ሆነው መለያየት
40ከሕዝቡም ብዙ ሰዎች ይህን ነገር ሰምተው “በእውነት ይህ ነቢይ ነው” አሉ። 41“ክርስቶስ ነው” ያሉም አሉ፤ እኩሌቶቹም እንዲህ አሉ፥ “በውኑ ክርስቶስ ከገሊላ ይወጣልን? 42#2ሳሙ. 7፥12፤ ሚክ. 5፥2። መጽሐፍ ‘ክርስቶስ ከዳዊት ዘርና ከዳዊት ከተማ ከቤተ ልሔም ይመጣል’ ይል የለምን?” 43ስለ እርሱም ሕዝቡ እርስ በርሳቸው ተለያዩ። 44ከእነርሱም ሊይዙት የወደዱ ነበሩ፤ ነገር ግን በእርሱ ላይ እጁን ያነሣ የለም።
45ሎሌዎቹም ወደ ካህናት አለቆችና ወደ ፈሪሳውያን ተመለሱ፤ እነርሱም፥ “ያላመጣችሁት ለምንድን ነው?” አሉአቸው። 46ሎሌዎቻቸውም መልሰው፥ “ያ ሰው እንደ ተናገረው ያለ ከቶ ሰው አልተናገረም” አሉአቸው። 47ፈሪሳውያንም መልሰው እንዲህ አሉአቸው፥ “እናንተም ደግሞ ተሳሳታችሁን? 48ከአለቆች ወይም ከፈሪሳውያን ያመነበት አለን? 49ኦሪትን ከማያውቁ ከእነዚህ ስሑታን ሕዝብ በቀር፤ እነርሱም የተረገሙ ናቸው።” 50#ዮሐ. 3፥1-2። ከእነርሱም አንዱ ቀድሞ በሌሊት ወደ ጌታችን ኢየሱስ የሄደው ኒቆዲሞስ እንዲህ አላቸው። 51“ሕጋችን አስቀድሞ ሳይሰማ፤ የሠራውንም ሳያውቅ በሰው ይፈርዳልን?” 52እነርሱም መልሰው፥ “አንተም ደግሞ ከገሊላ ነህን? ከገሊላ ነቢይ እንደማይነሣ መርምርና እይ” አሉት። 53ሁሉም እያንዳንዳቸው ወደ ቤታቸው ሄዱ።
Zur Zeit ausgewählt:
የዮሐንስ ወንጌል 7: አማ2000
Markierung
Teilen
Kopieren
Möchtest du deine gespeicherten Markierungen auf allen deinen Geräten sehen? Erstelle ein kostenloses Konto oder melde dich an.