የሉቃስ ወንጌል 15
15
የጠፋው በግ ምሳሌ
(ማቴ. 18፥12-14)
1 #
ሉቃ. 5፥29፤30። ቀራጮችና ኀጢአተኞችም ሁሉ ሊሰሙት ወደ እርሱ ይቀርቡ ነበር። 2ፈሪሳውያንና ጻፎችም “ይህስ ኀጢአተኞችን ይቀበላል፤ ከእነርሱም ጋር ይበላል፤” ብለው እርስ በርሳቸው አጉረመረሙ።
3ይህንንም ምሳሌ እንዲህ ሲል ነገራቸው 4“ከእናንተ መቶ በግ ያለው ከእነርሱም አንዱ ቢጠፋ፥ ዘጠና ዘጠኙን በበረሃ ትቶ የጠፋውን እስኪያገኘው ድረስ ሊፈልገው የማይሄድ ማን ነው? 5ባገኘውም ጊዜ ደስ ብሎት በጫንቃው ይሸከመዋል፤ 6ወደ ቤትም በመጣ ጊዜ ወዳጆቹንና ጐረቤቶቹን በአንድነት ጠርቶ ‘የጠፋውን በጌን አግኝቼዋለሁና ከእኔ ጋር ደስ ይበላችሁ፤’ ይላቸዋል። 7እንዲሁ ንስሓ ከማያስፈልጋቸው ከዘጠና ዘጠኝ ጻድቃን ይልቅ ንስሓ በሚገባ በአንድ ኀጢአተኛ ምክንያት በሰማይ ደስታ ይሆናል እላችኋለሁ።
የጠፋው ድሪም ምሳሌ
8“ወይም ዐሥር ድሪም#15፥8 አነስተኛ የብር ሳንቲም ያላት አንድ ድሪም ቢጠፋባት፥ መብራት አብርታ ቤትዋንም ጠርጋ እስክታገኘው ድረስ አጥብቃ የማትፈልግ ሴት ማን ናት? 9ባገኘችውም ጊዜ ወዳጆችዋንና ጐረቤቶችዋን በአንድነት ጠርታ ‘የጠፋውን ድሪሜን አግኝቼዋለሁና ከእኔ ጋር ደስ ይበላችሁ፤’ ትላቸዋለች። 10እንዲሁ ንስሓ በሚገባ በአንድ ኀጢአተኛ ምክንያት በእግዚአብሔር መላእክት ፊት ደስታ ይሆናል እላችኋለሁ።”
የጠፋው ልጅ ምሳሌ
11እንዲህም አለ “አንድ ሰው ሁለት ልጆች ነበሩት። 12ከእነርሱም ታናሹ አባቱን ‘አባቴ ሆይ! ከገንዘብህ የሚደርሰኝን ክፍል ስጠኝ፤’ አለው። ገንዘቡንም አካፈላቸው። 13ከጥቂት ቀንም በኋላ ታናሹ ልጅ ገንዘቡን ሁሉ ሰብስቦ ወደ ሩቅ አገር ሄደ፤ ከዚያም እያባከነ ገንዘቡን በተነ። 14ሁሉንም ከከሰረ በኋላ በዚያች አገር ጽኑ ራብ ሆነ፤ እርሱም ይጨነቅ ጀመር። 15ሄዶም ከዚያች አገር ሰዎች አንዱ ጋር ተጠጋ፤ እርሱም ዐሣማ እንዲያሰማራ ወደ ሜዳ ላከው። 16ዐሣማዎችም ከሚበሉት ፍልፋይ ለመጥገብ ይመኝ ነበር፤ የሚሰጠውም አልነበረም። 17ወደ ልቡም ተመልሶ እንዲህ አለ ‘ምግብ የሚተርፋቸው የአባቴ ተቀጣሪዎች ስንት ናቸው? እኔ ግን ከዚህ በራብ እጠፋለሁ። 18ተነሥቼም ወደ አባቴ እሄዳለሁና “አባቴ ሆይ! በሰማይና በፊትህ በደልሁ፤ 19ወደፊትም ልጅህ ልባል አይገባኝም፤ ከተቀጣሪዎችህ እንደ አንዱ አድርገኝ፤”’ እለዋለሁ። 20ተነሥቶም ወደ አባቱ መጣ። እርሱም ገና ሩቅ ሳለ አባቱ አየውና አዘነለት፤ ሮጦም አንገቱን አቀፈውና ሳመው። 21ልጁም ‘አባቴ ሆይ! በሰማይና በፊትህ በደልሁ፤ ወደፊትም ልጅህ ልባል አይገባኝም፤’ አለው። 22አባቱ ግን አገልጋዮቹን እንዲህ አላቸው ‘ፈጥናችሁ ከሁሉ የተሻለ ልብስ አምጡና አልብሱት፤ በጣቱ ቀለበት በእግሩም ጫማ አጥልቁለት፤ 23የሰባውን ፍሪዳ አምጥታችሁ እረዱት፤ እንብላም ደስም ይበለን፤ 24ይህ ልጄ ሞቶ ነበርና ደግሞም ሕያው ሆኖአል፤ ጠፍቶም ነበር ተገኝቶአልም።’ ደስ ይላቸውም ጀመር።
25“ታላቁ ልጁ በእርሻ ነበረ፤ መጥቶም ወደ ቤት በቀረበ ጊዜ የሙዚቃና የውዝዋዜ ድምፅ ሰማ፤ 26ከአገልጋዮቹም አንዱን ጠርቶ ‘ይህ ምንድነው?’ ብሎ ጠየቀ። 27እርሱም ‘ወንድምህ መጥቷል፤ በደኅና ስላገኘውም አባትህ የሰባውን ፍሪዳ አረደለት፤’ አለው። 28እርሱም ተቈጣ፤ ሊገባም አልፈለገም፤ አባቱም ወጥቶ ለመነው። 29እርሱ ግን መልሶ አባቱን ‘እነሆ፥ ይህን ያህል ዓመት አገለገልኩህ፤ ከትእዛዝህም ከቶ አልተላለፍሁም፤ ከወዳጆቼ ጋር እንድደሰት ለእኔ አንድ ጥቦት እንኳን ሰጥተኸኝ አታውቅም፤ 30ነገር ግን ይህ ልጅህ ገንዘብህን ከአመንዝራ ሴቶች ጋር አባክኖ በመጣ ጊዜ፥ የሰባውን ፍሪዳ አረድህለት፤’ አለው። 31እርሱ ግን እንዲህ አለው፦ ‘ልጄ ሆይ! አንተ ሁልጊዜ ከእኔ ጋር ነህ፤ ለእኔም የሆነ ሁሉ የአንተ ነው፤ 32ዳሩ ግን ይህ ወንድምህ ሞቶ ነበረ፤ ሕያው ስለ ሆነ ጠፍቶም ነበር፤ ስለ ተገኘ ደስ እንዲለን ፍሥሐም እንድናደርግ ይገባናል’።”
Dewis Presennol:
የሉቃስ ወንጌል 15: መቅካእኤ
Uwcholeuo
Rhanna
Copi
Eisiau i'th uchafbwyntiau gael eu cadw ar draws dy holl ddyfeisiau? Cofrestra neu mewngofnoda