የሉቃስ ወንጌል 8
8
ጌታችን የገሊላን አውራጃዎች ተዘዋውሮ ስለ ማስተማሩ
1ከዚህም በኋላ ጌታችን ኢየሱስ በየከተማዉና በየመንደሩ ተመላለሰ፤ የእግዚአብሔርንም መንግሥት ሰበከላቸው፤ አስተማራቸውም፤ ዐሥራ ሁለቱ ደቀ መዛሙርትም ከእርሱ ጋር ነበሩ። 2ከክፉዎች አጋንንትና ከደዌያቸው ያዳናቸው ሴቶችም አብረውት ነበሩ። እነርሱም፦ መግደላዊት የምትባለው ሰባት አጋንንት የወጡላት ማርያም፥ 3#ማቴ. 27፥55-56፤ ማር. 15፥40-44፤ ሉቃ. 23፥49። የሄሮድስ አዛዥ የነበረው የኩዛ ሚስት ዮሐና፥ ሶስናም፥ በገንዘባቸው ያገለግሉት#በግሪኩ “ያገለግሏቸው” ነበር ይላል። የነበሩ ብዙዎች ሌሎችም ነበሩ።
ስለ ዘሪው ምሳሌ
4ሕዝቡም ሁሉ፥ ከየከተማዉም ሁሉ ወደ እርሱ የመጡት ሲያዳምጡት እንዲህ ያለ ምሳሌ ነገራቸው። 5“ዘሪ ዘሩን ሊዘራ ወጣ፤ ሲዘራም አንዳንዱ በመንገድ ወደቀና ተረገጠ፤ የሰማይ ወፎችም በሉት። 6ሌላውም በጭንጫ መሬት ላይ ወደቀ፤ በበቀለም ጊዜ ወዲያው ደረቀ፤ ሥር አልነበረውምና። 7ሌላዉም በእሾህ መካከል ወደቀ፤ እሾሁም አብሮ አደገና አነቀው። 8በመልካም መሬት ላይ የወደቀ ዘርም ነበረ፤ በበቀለም ጊዜ መቶ እጥፍ አፈራ።” ይህንም ብሎ፥ “የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ” አላቸው።
9ደቀ መዛሙርቱም፥ “ይህቺ ምሳሌ ምንድን ናት?” ብለው ጠየቁት። 10#ኢሳ. 6፥9-10። እርሱም እንዲህ አላቸው፥ “የእግዚአብሔርን መንግሥት ምሥጢር ማወቅ ለእናንተ ተሰጥቶአችኋል፤ ለእነዚያ ግን አይተው እንዳያዩ፥ ሰምተውም እንዳይሰሙ፥ እንዳያስተውሉም በምሳሌ ነው። 11ምሳሌዉም ይህ ነው፤ ዘሩ የእግዚአብሔር ቃል ነው፤ 12በመንገድ የወደቀው ቃሉን የሚሰሙ ናቸው፤ አምነውም እንዳይድኑ ሰይጣን መጥቶ ቃሉን ከልባቸው ይወስድባቸዋል። 13በጭንጫም ላይ የወደቀው ሰምተው ነገሩን በደስታ የሚቀበሉት ናቸው፤ ነገር ግን ለጊዜው ያምናሉ እንጂ ሥር የላቸውም፤ መከራም በአገኛቸው ጊዜ ይክዳሉ። 14በእሾህም መካከል የወደቀው ቃሉን ሰምተው የባለጠግነት ዐሳብ፥ የኑሮም መቈርቈር የተድላና የደስታ መጣፈጥም የሚአስጨንቃቸውና ፍሬ የማያፈሩ ናቸው። 15በመልካም ምድር የወደቀው ግን ቃሉን በበጎና በንጹሕ ልብ የሚሰሙና የሚጠብቁት፥ ታግሠውና ጨክነውም የሚያፈሩ ናቸው።
16 #
ማቴ. 5፥15፤ ሉቃ. 11፥33። “መብራትን አብርቶ፥ ዕቃም ከድኖ ከአልጋ በታች የሚያኖራት የለም፤ ነገር ግን የሚመላለሱት ብርሃንን ያዩ ዘንድ በመቅረዝ ላይ ያኖራታል። 17#ማቴ. 10፥26፤ ሉቃ. 12፥2። የማይገለጥ የተሰወረ የለምና፤ የማይታይም ወደ ግልጥም የማይመጣ የተከደነ የለም፤ 18#ማቴ. 25፥29፤ ሉቃ. 19፥26። እንግዲህ እንዴት እንደምትሰሙ አስተውሉ፤ ላለው ይሰጠዋል፤ ከሌለው ግን ያው ያለው የሚመስለው እንኳ ይወሰድበታል።”
ወንድሞቹ ስለሚባሉት የተናገረው
19እናቱና ወንድሞቹም ወደ እርሱ መጡ፤ ነገር ግን ሕዝቡ ብዙ ነበርና ሊያገኙት አልቻሉም። 20“እናትህና ወንድሞችህ ከውጭ ቆመዋል፤ ሊያዩህም ይሻሉ” አሉት። 21እርሱም መልሶ፥ “እናቴና ወንድሞች የእግዚአብሔርን ቃል ሰምተው የሚያደርጉ እነዚህ ናቸው” አላቸው።
ባሕርን ስለ መገሠጹ
22ከዕለታት በአንዲት ቀንም እንዲህ ሆነ፤ እርሱ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደ ታንኳ ወጣና፥ “ኑ ወደ ባሕሩ ማዶ እንሻገር” አላቸው እነርሱም ሄዱ። 23ሲሄዱም አንቀላፋ፤ በባሕሩም ላይ ዐውሎ ነፋስ መጣ፤ ውኃዉም ታንኳቸውን ሞላው፤ እነርሱም ተጨነቁ። 24ቀርበውም፥ “መምህር ሆይ፥ መምህር ሆይ፥ ልንጠፋ ነው” ብለው ቀሰቀሱት፤ ተነሥቶም ነፋሱንና የውኃዉን ማዕበል ገሠጻቸው፤ እነርሱም ዝም አሉ፤ ታላቅ ፀጥታም ሆነ። 25እርሱም “እምነታችሁ ወዴት አለ?” አላቸው፤ እነርሱም ፈርተው ተደነቁ፤ እርስ በርሳቸውም፥ “ውኃም ነፋስም የሚታዘዙለት ይህ ማነው?” አሉ።
ጋኔን ያደረበትን ሰው ስለ ማዳኑ
26ከዚህ በኋላ በገሊላ ወደብ አቅጣጫ ወዳለችው ወደ ጌርጌሴኖን ሀገር በታንኳ ሄዱ። 27ወደ ምድርም በወረዱ ጊዜ ጋኔን ያደረበት ሰው ከከተማ ወጥቶ ተገናኘው፤ ልብሱንም ከጣለ ብዙ ዘመን ሆኖት ነበር፤ በመቃብር ብቻ ይኖር ነበር እንጂ ወደ ቤት አይገባም ነበር፤ 28ጌታችን ኢየሱስንም ባየው ጊዜ ጮኸ፤ ሮጦም ሰገደለት፤ “የልዑል እግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ሆይ፥ ካንተ ጋር ምን አለኝ?” እያለም በታላቅ ቃል ጮኸ፤ እንዳያሠቃየውም ማለደው። 29ክፉውን ጋኔን ከዚያ ሰው ላይ እንዲወጣ ያዝዘው ነበርና፤ ዘወትርም አእምሮዉን ያሳጣው ነበርና፤ ብላቴኖችም በእግር ብረት አስረው ይጠብቁት ነበር፤ እግር ብረቱንም ይሰብር ነበር፤ ጋኔኑም በምድረ በዳ ያዞረው ነበር። 30ጌታችን ኢየሱስም፥ “ስምህ ማነው?” ብሎ ጠየቀው፤ እርሱም፥ “ስሜ ሌጌዎን ነው” አለው፤ ብዙ አጋንንት ይዘውት ነበርና። 31ወደ ጥልቁም ይገቡ ዘንድ እንዳይሰድዳቸው ማለዱት። 32በዚያም ብዙ የእሪያ መንጋ በተራራ ላይ ተሰማርቶ ነበር፤ ወደ እሪያዎችም እንዲገቡባቸው ይፈቅድላቸው ዘንድ ማለዱት፤ እርሱም ፈቀደላቸው። 33እነዚያ አጋንንትም ከዚያ ሰው ላይ ወጥተው ወደ እሪያዎች ገቡ፤ የእሪያዎችም መንጋ አብደው ከገደሉ ወደ ባሕር ጠልቀው ሞቱ።
34እረኞችም የሆነውን ባዩ ጊዜ ሸሽተው ሄዱና ገብተው በከተማዉና በመንደሩ አወሩ። 35ሰዎችም የሆነውን ያዩ ዘንድ ወጡ፤ ሄደውም ወደ ጌታችን ወደ ኢየሱስ በደረሱ ጊዜ አጋንንት የወጡለትን ያን ሰው አእምሮዉ ተመልሶለት ልብሱን ለብሶ፥ ከጌታችን ከኢየሱስ እግር አጠገብ ተቀምጦ አገኙትና ፈሩ። 36ያዩትም ሰዎች ጋኔን አድሮበት የነበረው ሰው እንዴት እንደ ዳነ ነገሩአቸው። 37በጌርጌሴኖንም ዙሪያ ያሉ ሰዎች ከእነርሱ ዘንድ እንዲሄድላቸው ማለዱት፤ ጽኑ ፍርሀት ይዞአቸዋልና፤ ጌታችን ኢየሱስም በታንኳ ሆኖ ተመለሰ። 38ያም አጋንንት የወጡለት ሰው ከእርሱ ጋር ይሄድ ዘንድ ጌታችን ኢየሱስን ማለደው፤ 39እርሱ ግን፥ “ወደ ቤትህ ተመልሰህ እግዚአብሔር ያደረገልህን ታላቅ ነገር ሁሉ ተናገር” ብሎ አሰናበተው። እርሱም ሄዶ በከተማዉ ሁሉ ጌታችን ኢየሱስ ያደረገለትን ሁሉ ተናገረ። 40ጌታችን ኢየሱስም በተመለሰ ጊዜ ሕዝቡ በአንድነት ተቀበሉት፤ ሁሉ ይጠባበቁት ነበርና።
ስለ ምኵራቡ ሹም ልጅና ደም ይፈስስባት ስለ ነበረችው ሴት
41እነሆም ኢያኢሮስ የሚባል ሰው መጣ፤ እርሱም የምኵራብ ሹም ነበር፤ ከጌታችን ኢየሱስ እግር በታችም ሰገደ። ወደ ቤቱም ይገባ ዘንድ ለመነው። 42ዕድሜዋ ዐሥራ ሁለት ዓመት የሚሆናት አንዲት ልጅ ነበረችው፤ እርስዋም ልትሞት ቀርባ ነበረች።
43ከዚህም በኋላ ጌታችን ኢየሱስ ከእርሱ ጋር ሲሄድ ሰዎች ያጨናንቁት ነበር፤ ከዐሥራ ሁለት ዓመትም ጀምሮ ደም ይፈስሳት የነበረች ሴት መጣች፤ ገንዘብዋንም ሁሉ ለባለመድኀኒቶች ሰጥታ ጨርሳ ነበር፤ ነገር ግን ሊያድናት የቻለ ማንም አልነበረም። 44ቀርባም በጌታችን በኢየሱስ በስተኋላው ቆመችና የልብሱን ጫፍ ዳሰሰች፤ ያንጊዜም የደምዋ መፍሰስ ቆመ። 45ጌታችን ኢየሱስም፥ “ማን ዳሰሰኝ?” አለ፤ ሁሉም ካዱ፤ ጴጥሮስና ከእርሱ ጋር የነበሩትም፥ “መምህር ሆይ፥ ሰው ይጋፋህና ያጨናንቅህ የለምን? አንተ ግን ማን ዳሰሰኝ? ትላለህ” አሉት። 46ጌታችን ኢየሱስም፥ “የዳሰሰኝ አለ፤ ከእኔ ኀይል እንደ ወጣ ዐውቃለሁና” አላቸው። 47ሴቲቱም እንዳልተሰወረላት ባየች ጊዜ እየተንቀጠቀጠች ሄዳ ሰገደችለት፤ በሕዝቡም ሁሉ ፊት በምን ምክንያት ወደ እርሱ እንደ ቀረበችና የልብሱን ጫፍ እንደ ዳሰሰች ወዲያውም እንደ ዳነች ተናገረች። 48እርሱም፥ “ልጄ ሆይ፥ እምነትሽ አዳነችሽ፤ በሰላም ሂጂ” አላት። 49ይህንም ሲናገር አንድ ሰው ከምኵራቡ ሹም ቤት መጥቶ፥ “ልጅህስ ሞታለች እንግዲህ መምህሩን አታድክመው” አለው። 50ጌታችን ኢየሱስም በሰማ ጊዜ የምኵራቡን ሹም፥ “አትፍራ፥ ብቻ እመን፤ ልጅህስ ትድናለች” አለው። 51ወደ ቤትም በገባ ጊዜ ከጴጥሮስ፥ ከያዕቆብና ከዮሐንስ፥ ከብላቴናይቱም አባትና እናት በቀር ማንም ከእርሱ ጋር ሌላ ሰው ይገባ ዘንድ አልፈቀደም። 52ሁሉም እያለቀሱ ዋይ ዋይ ይሉላት ነበር፤ ጌታችን ኢየሱስ ግን፥ “አታልቅሱ፤ ብላቴናይቱ ተኝታለች እንጂ አልሞተችም” አላቸው። 53እንደ ሞተችም ዐውቀዋልና ሳቁበት። 54እርሱ ግን ሁሉን ወደ ውጭ አስወጣና እጅዋን ይዞ ጠራት፤ እንዲህም አላት፥ “ አንቺ ብላቴና ተነሺ።” 55ወዲያውም ነፍስዋ ተመልሶላት ፈጥና ቆመች፥ የምትበላውንም ይሰጡአት ዘንድ አዘዘ። 56አባቷና እናቷም አደነቁ፤ እርሱ ግን የሆነውን ለማንም እንዳይነግሩ ከለከላቸው።
Právě zvoleno:
የሉቃስ ወንጌል 8: አማ2000
Zvýraznění
Sdílet
Kopírovat
Chceš mít své zvýrazněné verše uložené na všech zařízeních? Zaregistruj se nebo se přihlas